ጥርስዎን ካስነቀሉ በኋላ ህመሙ አልቆመሎትም ?
ጥርስዎን ሲያስነቅሉ በመደበኛ ሁኔታ የተነቀለው ጥርስ ቦታ ላይ የረጋ ደም ይፈጠራል። ይህ የረጋ ደም በውስጥ በኩል ያሉትን አጥንት እና ነርቮች ክፍት እንዳይሆኑ እንዲሁም ቁስሉ ቶሎ እንዲድን ይረዳል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን መፈጠር የነበረበት የረጋ ደም ሳይፈጠር ሊቀር ፣ያለጊዜው ሊላቀቅ ወይም ቁስሉ ሳይድን ሊሟሟ ይችላል። ይህም ከስር ያለው አጥንት እና ነርቮች ለውጭ አየር እና ለምግብዎች በቀላሉ ተጋላጭ እንዲሆኑ በማድረግ ለከፍተኛ ሕመም ይዳርጋል።
ይህ ሁኔታ በሕክምናው ድራይ ሶኬት (Dry socket) በመባል ይታወቃል። ከ2 እስከ 5 በመቶ በሚሆኑ የጥርስ ነቀላዎች ላይም የሚያጋጥም ክስተት ሲሆን በተለይም የመንጋጋ ጥርስ (wisdom tooth) ከተነቀለ በኋላ በብዛት ይታያል።
ድራይ ሶኬት (Dry socket) እንዳለብዎት እንዴት ማወቅ ይችላሉ?
ድራይ ሶኬት አብዛኛውን ጊዜ ጥርሱ በተነቀለበት ቦታ ላይ ባዶ ክፍት ቦታ ሆኖ ይታያል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በክፍት ባታው ግርጌ ላይ ነጣ ያለ ነገር ሊታይ ይችላል። ይህ ነጣ ያለ ነገር የረጋ ደም ያልሸፈነው ክፍት አጥንት ነው።
የድራይ ሶኬት ምልክቶች ምንድን ናቸው ?
ድራይ ሶኬት የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስከትል ይችላል
- በአፍ ወይም በፊት ላይ የሚኖር የማያቋርጥ ሕመም
- ከመንጋጋ ተነስቶ ወደ ራስ እና አንገት የሚሰራጭ የሕመም ስሜት
- ጥርስ በየተነቀለበት አካባቢ የሚከሰት የጥርስ ወይም የድድ ኢንፌክሽን
- በአፍ ውስጥ ደስ የማይል ጣዕም መኖር ወይም የማያቋርጥ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያስገትል ይችላል።
የድራይ ሶኬት ሕመም አብዛኛውን ጊዜ ጥርስ ከተነቀለ ከ1 እስከ 3 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጀምራል።
ለድራይ ሶኬት መንስኤው ምንድን ነው?
የድራይ ሶኬት ትክክለኛ መንስኤ በግልፅ ባይታወቅም ለችግሩ ተገላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች ግን አሉ ። እነዚህም
- ሆርሞን ያላቸው የወሊድ መከላከያዎች
ኤስትሮጅን (Estrogen) ያላቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒኖች ቁስል የሚድንበትን ሂደት በማዘግየት ለድራይ ሶኬት የመጋለጥ እድልን ይጨምራሉ።
- የአፍ ንጽህና ጉድለት
የአፍ ንጽህና ጉድለት ካለ ጥርሱ በተነቀለበት ቦታ ዙሪያ ባክቴሪያዎች ሊከማቹና የቁስሉን መዳን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ።
- ማጨስ
አጫሾች ከማያጭሱ ሰዎች ይልቅ ለድራይ ሶኬት የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
- የመምጠጫ ቱቦ ወይም ስትሮ (Straw) መጠቀም
ስተሮ በሚጠቀሙበት ጊዜ የሚፈጠረው የመምጠጥ ኃይል ጥርሱ ላይ የተፈጠረውን የረጋ ደም ሊያላቅቀው ይችላል ፤ ስለዚህ ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ስተሮ ከመጠቀም ይቆጠቡ።
- አፍን በኃይል መጉመጥመጥ
አፍን በኃይል በማወዛወዝ መጉመጥመጥ የረጋውን ደም ሊረብሸው ይችላል። ስለዚህ መጉመጥመጥ ካስፈለገዎት ጭንቅላትዎን ቀስ አድርገው ወደ ጎን በማዘንበል ፈሳሹ የቆሰለውን አካባቢ እንዲያርሰው ያድርጉ።
የድራይ ሶኬት ምርመራ ምን ይመስላል ?
ጥርስዎን ከተነቀሉ በኋላ ከፍተኛ ሕመም ሲያጋጥሞ የጥርስ ሐኪምዎ ብዙውን ጊዜ ድራይ ሶኬት እንደሆነ ይጠረጥራል። ይህን ለማረጋገጥ ጥርሱ በተነቀለበት ቦታ ላይ ሊኖር የሚገባው የረጋ ደም መኖሩን ወይም አለመኖሩን ያያል። በአንዳንድ ሁኔታዎችም የቀረ የጥርስ ስብርባሪ አለመኖሩን ለማረጋገጥ የኤክስሬይ (X-ray) ምርመራ ሊደረግሎት ይችላል።
ድራይ ሶኬት እንዴት ይታከማል?
ሕክምናው ትኩረት የሚያደርገው ሕመምን በማስታገስ እና ቁስሉ እንዲድን በመርዳት ላይ ሲሆን የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፦
- ማጠብ (Irrigation)
ሐኪምዎ ጥርሱ በተነቀለበት ቦታ ውስጥ የተጠራቀሙ የምግብ ፍርፋሪዎችን ለማስወገድ ቁስሉን በጨው ውሃ (saline) ወይም በፀረ-ባክቴሪያ ፈሳሽ ቀስ አድርጎ ያጥብሎታል።
- መድኃኒትነት ያላቸው ቁስል መሸፈኛዎች (Medicated dressings)
ሐኪምዎ እንደ ሊዶኬይን (lidocaine) ወይም ዩጂኖል (eugenol) ያሉ ሕመምን የሚያስታግሱ እና የሚያደነዝዙ መድኃኒቶችን ክፍት በሆነው ቁስል ውስጥ ሊያደርግልዎት ይችላል።
- የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች
የሚሰማዎትን ህመም ለመቆጣጠር እንደ ፓራሲታሞል ወይም አይቡፕሮፌን ያሉ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ መድኃኒቶችን መጠቀም ይችላሉ።
- የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች (Antibiotics)
የጥርስ ሐኪምዎ ኢንፌክሽን እንዳለ ከጠረጠረ የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን ሊያዝሎት ይችላል።
የማገገሚያ ጊዜ
ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገ ድራይ ሶኬት አብዛኛውን ጊዜ ከ7 እስከ 10 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ይድናል። በዚህ ጊዜ የተጋለጠውን አካባቢ የሚሸፍን አዲስ ህብረ ሕዋስ (tissue) ቀስ በቀስ ይፈጠራል። ስለዚህ ቁስሉ ቶሎ እንዲድን እና ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር ለመከላከል ዘወትር ጥርስን በቀስታ መቦርሽ እንዲሁም የጥርስ ማፅጃ ክርን (floss) መጠቀም ያስፈልጋል።
ለድራይ ሶኬት መቼ የጥርስ ሐኪም ማማከር ይኖርቦታል?
ሕመሙ የማያቋርጥ፣ እየባሰ የሚሄድ ወይም እንቅልፍ የሚነሳዎት ከሆነ ፤ በተለይም ደግሞ በህመም ማስታገሻ መድኃኒት የማይሻሻል ከሆነ በአስቸኳይ የጥርስ ሐኪምዎን ያማክሩ።
ድራይ ሶኬትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ድራይ ሶኬትን ሁልጊዜ መከላከል ባይቻልም ተጋላጭነትዎን ግን መቀነስ ይችላሉ። ጥርስ የተነቀለበት ቦታ እንዲድን እንዲሁም እንዳይጎዳ ለመከላከል የሚከተሉትን ያድርጉ፦
- ቁስሉ በሚድንበት ወቅት ሲጋራ ከማጨስ ወይም ማንኛውንም የትምባሆ ምርት ከመጠቀም ይቆጠቡ
- አፍዎ እስኪድን ድረስ ትኩስ ወይም ጋዝ ያላቸውን (ካርቦኔትድ) መጠጦች አይጠጡ
- የመምጠጫ ቱቦ ወይም ስትሮ አይጠቀሙ ፤ የመምጠጥ ኃይሉ የረጋውን ደም ሊያላቅቀው ስለሚችል
- ለስላሳ ምግቦችን ብቻ ይመገቡ
- ከጥርስ ሐኪምዎ የተሰጡዎትን መመሪያዎች በጥንቃቄ ይከተሉ
በአጠቃላይ
በቅርቡ ጥርስዎን አስነቅለው ከፍተኛ ሕመም እየተሰማዎት ከሆነ ፣ ችግሩ ድራይ ሶኬት (Dry socket) ሊሆን ስለሚችል ችላ አይበሉት። ሕመሙ እንዲቀንስልዎትና ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት በተቻለ ፍጥነት የጥርስ ሐኪምዎን ያማክሩ። መልካሙ ዜና ችግሩ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይድናል።




