ብሮንኮስኮፒ ምንድን ነው?

Eyasu Yebeltal
Apr 27, 2026
undefined

                                ብሮንኮስኮፒ  

ሃኪምዎ ብሮንኮስኮፒ የተሰኘ ምርምርራን ሲያዝልዎ በምንነቱ ግራ መጋባት ወይም መጨነቅ ሙሉ በሙሉ የተለመደ ነው። ይህ መመሪያ ብሮንኮስኮፒ ለተሰኘው የምርመራ ሂደት በራስ በመተማመን እና ግልጽ መረዳት ባለው መልኩ መቅረብ እንዲችሉ ምርምርራው ምን እንደሆነ፣ ለምን እንደሚሰራ፣ ምን መጠበቅ እንዳለብዎ እና ለምርመራው እንዴት መዘጋጀት እንዳለብዎ ያብራራል።

      ብሮንኮስኮፒ ምንድን ነው?

ብሮንኮስኮፒ ሃኪሞች ወደ መተንፈሻ ቱቦዎ እና ሳንባዎ ውስጥ በቀጥታ እንዲመለከቱ የሚያስችል የሕክምና ሂደት ሲሆን ብሮንኮስኮፕ በሚባል ጫፉ ላይ ማብራት እና ካሜራ ያለው ቀጭን ተጣጣፊ ቱቦን በመጠቀም ይከናወናል። ይህ ቱቦ በቀስታ በአፍንጫዎ ወይም በአፍዎ ውስጥ እንዲገባ በመደረግ ወደ መተንፈሻ ቱቦዎ እና ሳንባዎ ውስጥ ይተላለፋል። ይህ ሂደት ሃኪሞች ምንም ቀዶ-ጥገና ሳያስፈልጋቸው በመተንፈሻ አካላትዎ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ እንዲያዩ ይረዳቸዋል።

      ለምን ሊያስፈልግ ይችላል?

ሐኪምዎ የብሮንኮስኮፒ ምርመራን በተለያዩ ምክንያቶች ሊመክር ሲችል፣ ከነዚህም ውስጥ፡-

  • የማያቋርጥ ሳል ወይም የማይታወቅ የመተንፈስ ችግርን ለመመርመር
  • በሳንባዎች ውስጥ ያለ ኢንፌክሽኖችን ለመመርመር
  • በደረት ኤክስሬይ ወይም በሲቲ ስካን የታዩ ያልተለመዱ ግኝቶችን ለመመርመር
  • የመትንፈሻ ቱቦን የዘጉ እንደ ዕጢዎች ወይም ንፍጥን ያሉ አጋጆችን ለመፈለግ
  • ለተጨማሪ ምርመራ ትናንሽ የቲሹ ናሙናዎችን (ባዮፕሲዎችን) ለመውሰድ
  • የመትንፈሻ ቱቦ ውስጥ የገቡ ባእድ ነገሮችን ወይም ፈሳሾችን ለማስወገድ

     እንዴት መዘጋጀት ያስፈልጋል?

ለዚህ ምርምራ የሚደረግ ዝግጅት አብዛኛውን ጊዜ ቀላል ሲሆን ነገር ግን በጣም አስፈላጊ ነው።

  • ጾም፡- ምርመራው ከመደረጉ ከ6-8 ባለው ሰአታት በፊት እንዳይበሉ ወይም እንዳይጠጡ ይጠየቃሉ።
  • መድሃኒቶች፡- ከዚህ በፊት ስለሚወስዷቸው መድሃኒቶች (በተለይም የደም ማከሚያዎች) በሙሉ ለሀኪምዎ በግልጽ ያሳውቁ። 
  • መጓጓዣ፡- ብዙ ጊዜ ማደንዘዣ እና ማስታገሻዎች ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ወደ ቤት የሚመልስዎ ሰው ያዘጋጁ።
  • የሕክምና ታሪክ፡- ስለ አለርጂዎችዎ ወይም ስላለዎት የጤና ሁኔታዎች እንክብካቤ ቡድንዎን በሚገባ ያሳውቁ።

     ሂደቱ እንዴት ይከናወናል?

ብሮንኮስኮፒ በብዛት በሆስፒታል ወይም በተመላላሽ ታካሚ ክሊኒክ ከ 30-60 ደቂቃ ባለ ጊዜ ውስጥ ይከናወናል።

ሂደቱ የሚከተለውን ይመስላል፦

  1. በምርመራው ወቅት ዘና ለማለት እንዲረዳዎ በባለሙያዎች የሰመመን መድሃኒት ይሰጥዎታል።
  2. ጉሮሮዎ ላይ ምንም የህመም ስሜት እንዳይሰማዎ በአካባቢያዊ ማደንዘዣ ጉሮሮዎ እንዲደነዝዝ ይደረጋል።
  3. የብሮንኮስኮፒ ቀጭን ቱቦ በአፍንጫዎ ወይም በአፍዎ በኩል በቀስታ እንዲገባ ይደረጋል። 
  4. ሐኪምዎ የአየር መተላለፊያ መንገዶችዎን በካሜራው በመታገዝ በሚገባ ይመረምራል እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ ለተጨማሪ ምርመራ ናሙና ሊወስድ ይችላል።

መጠነኛ ጫና ወይም ምቾት ማጣት ሊሰማዎት ሲችል ሂደቱ በአጠቃላይ ህመም የለውም።

     ማገገም

ከሂደቱ በኋላ፣

  • የተሰጥዎ የሰመመን መድሃኒት ተጽእኖ እኪለቅዎ ድረስ ክትትል ይደረግልዎታል
  • ለጥቂት ሰዓታት ጉሮሮዎ ሊደነዝዝ ወይም ትንሽ ህመም ሊሰማው ይችላል
  • መለስተኛ ሳል ወይም የድምጽ መጎርነን ሊኖርዎ ይችላል
  • ቋቅ የማለት ተፈጥሮዎ (gag reflex) እስኪመለስ ድረስ ከመብላትና ከመጠጣት እንዲቆጠቡ ይደረጋል።

ብዙ ሰዎች ምርምራው በተደረገላቸው በተመሳሳይ ቀን ወደ ቤት በመሄድ በ 24 ሰዓታት ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎቻቸውን መቀጠል ይችላሉ።

      ለሃኪምዎ ማሳወቅ ያልብዎት ጉዳዮች

የሚከተሉት ካጋጠመዎት ሐኪምዎን ያሳውቁ:-

  • የማያቋርጥ ትኩሳት
  • የትንፋሽ ማጠር
  • የደረት ሕመም
  • ደም የቀላቀለ አክታ

ከምርመራው በኋላ እነዚህ ምልክቶች ያልተለመዱ ቢሆኑም ካጋጠሙዎት ወዲያውኑ በባለሙያ መገምገም አለባቸው።

ብሮንኮስኮፒ ሃኪሞችዎ አንዳንድ ጊዜ ያለ ወራሪ ቀዶ ጥገና የሳንባ በሽታዎችን ለመመርመር እና ለማከም የሚረዳቸው ጠቃሚ መሳሪያ ሲሆን ምን እንደሆነ መረዳት ጭንቀትን ሊያቃልል እና የጤና እንክብካቤ ጉዞዎ ላይ የበለጠ እርግጠኝነት እንዲሰማዎት ያግዝዎታል። ስጋቶች ወይም ጥያቄዎች ካለዎት ከሐኪምዎ ጋር ለመወያየት አያመንቱ።

Comments (0)