የመንጋጋ ቆልፍ ክትባት (Tetanus shots)
የመንጋጋ ቆልፍ ሕመም (Tetanus)
የመንጋጋ ቆልፍ ሕመም የነርቭ ስርአትን እና ጡንቻዎችን የሚጎዳ ከባድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሲሆን በተለይም መንጋጋን እና አንገትን ይጎዳል። ክሎስትሪዲየም ቴታኒ (Clostridium tetani) በሚባል ባክቴሪያ የሚከሰት ሲሆን የዚህ ባክቴርያ ዱኬዎች (ስፖሮች) በአፈር ፣ በቆሻሻ እና በእንስሳት አይነምድር ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። ስፖሮች አንዳንድ ፍጥረታት ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ የመራቢያ አካላት ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ስፖሮች ከፍተኛ ሙቀትን እና ከባድ የአካባቢ ተጽዕኖዎችን መቋቋም ይችላሉ።
እነዚህ የባክቴሪያው ስፖሮች ቀላል ወይም ጥልቅ ቁስል በሚኖርበት ጊዜ በቁስሉ አማካኝነት ወደ ደም በመግባት ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ከዚያም ባክቴሪያው ወደ ነርቭ ስርአት በመሰራጨት ቴታኖስፓስሚን (tetanospasmin) የተባለ መርዝ ያመነጫል። ይህ መርዝ በ ኖርማል ጊዜ ከ ህብረሰረሰር ወደ ጡንቻዎቻችን የሚሄደውን የነርቭ መልእክት እንዳይተላለፍ በመከልከል ከባድ የጡንቻ መኮማተር እንዲፈጠር ያደርጋል።
የመንጋጋ ቆልፍ ሕመም ከሚከተሉት ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል ፦
- ሰውነታችን ላይ ቁስል እንዲፈጠር የሚያደርጉ አደጋዎች ከደረሱብን
- ቁስላችን የሞተ የሰውነት ህዋስ (dead tissue) ካለው
- የመቃጠል አደጋ (burn)
- በተበከለ መሳሪያ መበሳት ፣ መነቀስ፣ አደንዛዥ እጽ በመርፌ መውሰድ ፣ በተበከለ ሚስማር እና በመሳሰሉት ጉዳት ከደረሰብን
- በቆሻሻ ፣ በአፈር፣ በሰገራ እና በምራቅ የተበከለ ቁስል
አልፎ አልፎ ከሚከተሉት ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ይችላል
- በእንስሳ ከተነከስን
- የጥርስ ኢንፌክሽን ካጋጠመን
- በነፍሳት ከተነከስን
- ስር ከሰደደ ቁስሎች እና ኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ይችላል
የመንጋጋ ቆልፍ ሕመም ምልክቶች ምን ምን ናቸው?
የመንጋጋ ቆልፍ ሕመም ምልክቶች የሚከተሉትን ይመስላሉ ፦
- አንገታችንን እና መንጋጋችንን ለማንቀሳቀስ አዳጋች የሚያደርግ የአንገት ወይም የመንጋጋ ጡንቻዎች መገተር
- አፋችንን ልንሰበስብ ብንሞክርም የማይጠፋ እንግዳ ፈገግታ
- ጡንቻዎቻችንን ልናፍታታ ብንሞክርም የማይለቀን ህመም ያለው መኮማተር
- ለመተንፈስ ወይንም ለመዋጥ መቸገር
- የመረበሽ ወይንም የመቁነጥነጥ ስሜት
- ሙቀት ሳይኖር ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሳናደርግ ማላብ መኖር
- ከተለመደው ፈጣን የሆነ የልብ ምት ወይም ኖርማል ያልሆነ የልብ ምት መኖር እና
- ትኩሳት ናቸው
አንዳንድ ሰዎች ላይ የጡንቻዎቹ መኮማተር ሰውነታቸው የተለያየ ቅርጽ እንዲይዝ ያስገድዳቸዋል ከእነዚህም መካከል
- እጅን ጨብጦ መቀመጥ
- ጀርባን ከአልጋ ወይም ከወለል ላይ ማንጠራራት
- እግርን ዘርግቶ አለማጠፍ
- ክንዳችን ከቁጥጥራችን ውጪ ወደ ፊት እና ኋላ መወዛወዝ
- ለመተንፈስ መቸገር አንዳንዴም የጡንቻ መኮማተር በሚኖርበት ጊዜ መተንፈስ ማቆም
አንዳንድ ቴታነስ ያለባቸው ሰዎች አንድ የሰውነት ክፍል ላይ ብቻ የጡንቻዎች መኮማተር ሊኖራቸው ይችላል ለምሳሌ የሆድ ጡንቻዎች ብቻ ሊገተሩ እና ሊጠነክሩ ይችላሉ። ቴታነስ ከጭንቅላት እና ከ አንገት ጋር ተያይዞ የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል
- ለመዋጥ መቸገር
- የመንጋጋ ወይም የአንገት ጡንቻ ብቻ ተለይቶ መጠንከር ወይም መኮማተር
- የፊት ወይም የጭንቅላት ከፍተኛ ህመም መኖርን ያካትታል።
የመንጋጋ ቆልፍ ሕመም የሚያስከትለው ባክቴሪያ ወደ ደማችን ውስጥ ከገባ በኋላ በስንት ጊዜ ውስጥ የሕመሙ ምልክቶችን ማሳየት እንጀምራለን?
የክሎስትሪዲየም ቴታኒ (Clostridium tetani) ባክተሪያ ደማችን ውስጥ ከገባ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ በ 8 ቀናት ውስጥ የመንጋጋ ቆልፍ ምልክቶች ይታዩብናል ነገር ግን በነዚህ ቀናት ውስጥ ብቻ ማለታችን አይደለም ከ 3 እስከ 21 ቀናት ባለው ውስጥም ምልክቶችን ልናሳይ እንችላለን። ከነርቭ ስርአት (nervous system) ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ለምሳሌ እጅ ወይም እግር ላይ የባክተሪያው ስፖሮች ወደ ሰውነታችን ከገቡ ረዘም ካለ ጊዜ በኋላ ምልክቶችን እናሳያለን ለነርቭ ስርአትም ቅርብ በሆኑ ቦታዎች ለምሳሌ በጭንቅላታችን ወይም በአንገታችን ውስጥ ስፖሮቹ ከገቡ ቶሎ ብሎ ምልክቶቹ ሊታዩብን ይችላሉ።
የመንጋጋ ቆልፍ (tetanus) ክትባት በህጻናት
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የክትባት ፕሮግራም (EPI) ፖሊሲ እንዳስቀመጠው ህጻናት ከተወለዱ በ
- 6ተኛው ሳምንታቸው
- 10ተኛው ሳምንታቸው እና
- 14ተኛው ሳምታቸው DPT የሚባል ክትባት እንዲሰጣቸው ያዛል።
ይህ DPT የሚባለው ክትባት የዲፍቴርያ (diphtheria) ፣ የፐርቲውስስ (pertussis) እና የመንጋጋ ቆልፍ(tetanus) ክትባቶችን በውስጡ ይይዛል።
ለህጻኑ በ 6ተኛው ሳምንት የ DPT ክትባት በተለያዩ ምክንያቶች መስጠት ካልተቻለ ህጻኑ በመጣበት ቀን ወዲያውኑ ክትባቱ ሊሰጠው ይገባል። ከዚያም የሚቀጥሉት ሁለት ክትባቶች በ 4 ሳምንት ልዩነት መሰጠት አለባቸው። ሶስቱንም ክትባቶች ህጻኑ 6 ወር ሳይሞላው ሰጦ መጨረስ እድሜው ከፍ ብሎ ክትባቱ ሲሰጠው ከሚያጋጥመው ተጓዳኝ ጉዳቶች(side effects) እንዲጠበቅ ይረዳናል።
የወላነት ዘመን (child bearing age) ላይ ያሉ እድሜአቸው ከ15 እስከ 49 የሆኑ ሴቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የክትባት ፕሮግራም (EPI) መሰረት 5 ክትባቶችን መውሰድ እንዳለባቸው ያስቀምጣል።
የሚሰጠው ክትባት ቴታነስ ቶክሶይድ (tetanus toxoid(TT)) የሚባለው ክትባት ነው።
- የመጀመሪያው ክትባት (TT1) በተቻለ መጠን በቶሎ እንዲሰጥ ይመክራል
- ሁለተኛው ክትባት (TT2) የመጀመሪያው ክትባት (TT1) ከተሰጠ ቢያንስ ከ 4 ሳምንት በኋላ እንዲሰጥ ያዛል
- ሶስተኛው ክትባት (TT3) ሁለተኛው ክትባት (TT2) ከተሰጠ ቢያንስ ከ 6 ወር በኋላ መሰጠት አለበት
- አራተኛው ክትባት (TT4) ሶስተኛው ክትባት (TT3) ከተሰጠ ቢያንስ ከ 1 አመት በኋላ ወይም ካልተቻለ በቀጣይ እርግዝና ላይ መስጠት ይቻላል
- አምስተኛው ክትባት (TT5) አራተኛው ክትባት (TT4) ከተሰጠ ቢያንስ ከ 1 አመት በኋላ ወይም ካልተቻለ በተመሳሳይ መልኩ በቀጣይ እርግዝና ላይ መስጠት ይቻላል
የ መንጋጋ ቆልፍ (Tetanus) ክትባት በእርግዝና ወቅት
- አንዲት እርጉዝ ሴት ከዚህ በፊት የቴታነስ ክትባት ወስዳ ከጨረሰች ማለትም ቢያንስ ሶስት የቴታነስ ክትባቶችን ከወሰደች በእርግዝና ወቅት አንድ የቴታነስ ክትባት እንዲሰጣት ይመከራል። ክትባቱም ከ 27-36 ሳምንታት ባሉት የእርግዝና ጊዜያት ቢሰጣት ተጠቃሚ ትሆናለች።
- ቀደም ሲል የቴታነስ ክትባት ወስዳ ካልጨረሰች ማለትም ሶስት የቴታነስ ክትባት ካልወሰደች ወይም የቴታነስ ክትባት መውሰዷን እንግጠኛ ካልሆነች በእርግዝና ወቅት ሶስት የቴታነስ ክትባቶችን እንድትወስድ ይደረጋል። የመጀመሪያው ክትባት የእንግዝና ክትትል ስትጀምር ይሰጣል። የሚቀጥሉት ክትባቶች የመጀመሪያው ክትባት ከተሰጠ ከ 4 ሳምንት በኋላ እና ከ 6-12 ወራት በኋላ ይሰጣል።
የ መንጋጋ ቆልፍ (Tetanus) ክትባት በአዋቂዎች
- ከ 11-18 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ጎልማሶች አንድ የቴታነስ አጎልባች (booster) ክትባት እንዲሰጣቸው ይመከራል። ከዚያም በህይወት ዘመናቸው በየ 10 አመቱ ይህ ክትባት እንዲሰታቸው ይደረጋል።




