እርድ (Turmeric ) የሚሰጣቸው የጤና በረከቶች

Melat Geatchew
May 13, 2026
undefined

እርድ (Turmeric ) የሚሰጣቸው የጤና በረከቶች 

እርድ የዝንጅብል ዘር ሲሆን ብዙ ግዜ በቅመም መልክ ከምግብ ጋር ተዋህዶ ይዘጋጃል። የእርድ ቅመም ለመስራት የእርድ ተክል ስር ከ30-45 ደቂቃ ይቀቀላል። ከዛም ምድጃ ውስጥ ገብቶ እንዲደርቅ ይደረግና ቅመም ይዘት እስኪኖረው ይፈጫል። እርድ ከእኛ ሃገር አልፎ በህንድ እና ፓኪስታን ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው የምግብ አይነት ነው። እርድ በተለያዩ ምግቦች ላይ በቀለም ማሳመሪያነት እና በቅመምነት የሚገባ ሲሆን በሻይ መልኩ መጠጣትም ይመከራል። 

አንድ ሻይ ማንኪያ እርድ 29 ካሎሪ፣ 0.9 ግራም ፕሮቲን፣ 0.3ግራም ፋት እና 6.3ግራም ካርቦሃይድሬት ይይዛል። የአይረን፣ ቫይታሚን ሲ፣ ፖታሲየም እና ማንጋኒስ ይዘትም አለው።

እርድ መብላት ለጤና የሚሰጠው ጥቅም

የእርድ በርካታ ጤና ጥቅሞች ውስጡ የሚገኙ ከርኪውሚን ተብለው የሚጠሩ ንጥረነገሮች ውጤት ነው። ለእርድ ጣእም የሚሰጡት እነዚህ ከርኪውሚን የተባሉ ንጥረነገሮች ናቸው።

በየቀኑ መውሰድ ከሚገባን እርድ ውስጥ በሻይ መልኩ መጠጣታችን የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስገኛል።

1. የመገጣጠሚያ ህመምን ይቀንሳል። የተለያዩ የመገጣጠሚያ ህመሞች የሚከሰቱት መገጣጠሚያዎች ላይ በሚኖር ብግነት የሚከሰት ህመምን በእጅጉ ይቀንሳል። 

2. የበሽታ መከላከል አቅምን ይጨምራል።

እርድ በውስጡ በያዘው የፀረ መርዛማነት፣ የፀረ ቫይረስ፣ እና የፀረ ባክቴሪያ ንጥረ ነገር አማካኝነት የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም ያሳድጋል።

3. ለልብ ጤና ፋይዳው የላቀ ነው፤ እርድ ሰውነት ውስጥ የሚፈጠርን የደም መርጋት ይከላከላል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በደም ቧንቧ የሚፈጠርን የፕላክ(ስብ) ክምችት ይቀንሳል። እንስሶች ላይ በተደረገ ሙከራ እርድ የኮሌስትሮል መጠን እንደሚቀንስ ማየት ተችሏል።

4. የካንሰር ህመምን ይከላከላል።

ቅድመ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የእርድ ጸረ-ብግነት  እና ጸረ-ኦክሲዳንት ባህሪዎች ካንሰር ከመፈጠሩ በፊት ለመከላከል እንደሚረዳ ይናገራሉ።

እርድ በውስጡ የፀረ ካንሰር ንጥረነገር ያለው በመሆኑ በቫይረስ አማካኝነት የሰውነት ህዋሳት እንዳይጎዱ ይከላከላል።

5. ለምግብ መፈጨት ያገለግላል፡ 

ከርኪውሚን የሃሞት ቀረጢት ሃሞት እንዲያመነጭ በማድረግ ምግብ መፍጨትን ይረዳል ተብሎ ይታመናል። እርድ በሆድ መፍጨት ችግር መነፋት እና ፈስ የሚያስቸግራቸውን ሰዎች እንደሚረዳ አንድ ጥናት ይናገራል።

6. ለአእምሮ ጤና

ከፍተኛ የመርሳት ችግርን ለመከላከል እና ስጋቱን ለመቀነስ ያስችላል።እርድ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች የአእምሮ ብቃት ከሚያዳክሙ በሽታዎች ለመከላከል ይረዳል። ዲሜንሺያ በሽታ በታየባቸው 1000 አዛውንቶች ላይ በተሰራ ጥናት በህይወታቸው እርድ ይመገቡ የነበሩት አዛውንቶች የአእምሮ ጤንነታቸው ከሌሎቹ ታካሚዎች የተሻለ ሁኖ ተገኝቷል።የተለያዩ ጥናቶች እርድ ከተለያዩ አዕምሯዊ ጉዳቶች እንደሚከላከል እና የማስታወስ አቅምን እንደሚጨምር ያሳያሉ።

7. ጉበት እንዳይጎዳ ያደርጋል።

8. ከስኳር ህመም ይታደጋል

ኦክሲዴቲቭ ጭንቀት እና የሰውነት ብግነት መጨመር የስኳር በሽታ እንዲጀምር ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። እርድ ውስጥ የሚገኘው ከርኪውሚን ጣፊያ ኢንሱሊን እንዲያመርት በማድረግ የስኳር በሽታ ህመምን ያስታግሳል።

240 የቅድመ-ስኳር ህመም የጀመራቸው ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት እርድ እይንም  ከርኪውሚን የተመገቡት ታካሚዎች በንጽጽር ለስኳር በሽታ ተጋላጭነታቸው ቀንሶ ታይቷል።

ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎችን የጤና ጥቅምች የሚያስገኘውን የእርድ ሻይ ለማዘጋጀት የሚከተለውን አሰራር ይጠቀሙ።

አዘገጃጀት

  • አራት ብርጭቆ ውሃ ማፍላት፣
  • አንድ ወይም ሁለት የሻይ ማንኪያ የተፈጨ እርድን መጨመር፣
  • ውሃውን እና የተፈጨውን እርድ ለ10 ደቂቃዎች እንዲዋሃድ እና አብሮ እንዲፈላ ማድረግ፣

 

ከ10 ደቂቃ በኋላ አውርደን እንዲቀዘቅዝ እናደርጋለን፡፡ ሻዩ ከበረደ በኋላ አጥልለን መጠጣት፡፡ ሻዩን ለማጣፈጥ በተቻለ አቅም ከስኳር ይልቅ ማር ብንጠቀም ይመረጣል፡፡  

  • ካስፈለኝ እንደ ሎሚ፣ ዝንጅብል፣ ወተት፣ ክሬም እና የኮኮናት ዘይትም ከእርድ ጋር ማዋሃድ መጠጣት ይቻላል ። ይህን ማድረግ ደግሞ የእርድ  ሻይ ለማዘውተር  በእጅጉ ያግዛል።

 

እርድ የሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች

እርድን በአግባቡ መጠቀም የጤና ችግር አያመጣም። ነገር ግን በከፍተኛ መጠን መመገብ ሆድን ሊያስቆጣ ይችላል። በጣም ከከፋ የሆድ መቁሰል ሊያስከትል ይችላል። እርድ ደምን ስለሚያቀጥን ቀዶ ጥገና በሚደረግበት ሁለት ሳምንት ውስጥ መወሰድ የለበትም። 

ሌሎች ያልተለመዱ እና በብዙ ሰዎች ላይ የማይከሰቱ የእርድ የጎኞሽ ጉዳቶች 

  • ማቅለስለሽ 
  • ማስመለስ
  • ድርቀት
  • የአለርጂ ምልክቶች
  • የሰውነት ላይ ሽፍ

በተጨማሪም እርድ አብዝቶ መጠቀም ለሰውነታችን የደም ሴሎች አስፈላጊ የሆነው አይረን ወደ ሰውነታችን እንዳይገባ ያደርገዋል።  እርጉዝ ሴቶች እና የሚያጠቡ ሴቶች ላይ ያለው ጉዳት እስካሁን በጥናት አልተረጋገጠም ነገር ግን ባያዘወትሩት ይመከራል።

እርድ በውስጡ የኩላሊት ጠጠር ሚያስከትሉት ኦክዛሌት (oxalates) የተሰኙ ንጥረ ነገሮችን በብዛት ይዟል፣እነዚህ ንጥረነገሮች በብዛት በሰውነታችን ካሉ የኩላሊት ጠጠርን ሊያስከትሉ ይችላሉ። 

 

እርድ ለውበት 

እርድ ለብዙ ሺ ዘመናት በእስያ በተለይ በህንድ እና ፓኪስታን ውስጥ ለመድሃኒትነት እና ለውበት ይውል የነበረ ቅመም ነው፡፡ በምድራችን ላይ ብዙ ጥናቶች በእርድ ላይ ተደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ እርድን መመገብ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ የምናየው እርድን እንዴት ለውበታችን መጠቀም እንደምንችል ነው፡፡ 

 

  •  እርድ ብጉርን ይከላከላል/ያጠፋል

 አንድ የሻይ ማንኪያ እርድ፤ አንድ የሻይ ማንኪያ ማር እና አንድ የሾርባ ማንኪያ እርጎ በአንድ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ በደንብ እንቀላቅላለን፡፡ 

 ፊታችንን ከታጠብን በኋላ በንፁህ እና ደረቅ ፊት ላይ ውህዱን እንቀባዋለን፡፡ ውህዱን ስንቀባ ጣቶቻችን በተለይ ጥፍራችን እንዳይበልዝ ጓንት ወይም ላስቲክ መጠቀም እንችላለን፡፡ 

 ከ20-30 ደቂቃ ውህዱ ፊታችን ላይ እስኪደርቅ ድረስ እንጠብቃለን፡፡ 

 ፊታችንን ለብ ባለ ውሃ ብቻ በደንብ መለቅለቅ፡፡ ይሄንን ውህድ በሳምንት ለሶሰት ቀን ለአራት ሳምንታት ብንጠቀም ጥሩ ውጤት ማየት እንችላለን፡፡ 

 

  •  እርድ የተሰነጣጠቀ ተረከዘን ያስተካክላል

 ሶስት የሾርባ ማንኪያ የጉሎ (ካስተር) ዘይት እና ግማሽ የቡና ማንኪያ እርድ በአንድ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ በደንብ እንቀላቅላለን፡፡

 እግራችንን ከታጠብን በኋላ የተሰነጣጠቀ ተረከዛችንን ላይ ውህዱን እንቀባዋለን፡፡ 

 ከ30 ደቂቃ በኋላ እግራችንን በቀዝቃዛ ውሃ በደንብ መለቅለቅ

           

  •  እርድ ፀጉር ለማሳደግ እና ለማጠንከር ይጠቅማል 

 3 የሻይ ማንኪያ እርድ፤ 4 የሾርባ ማንኪያ ኮኮናት ዘይት ወይንም የወይራ ዘይት፤ 3 የሻይ ማንኪያ ሮዝመሪ (የጥብስ ቅጠል) ዘይት በአንድ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ በደንብ እንቀላቅላለን፡፡

 ውህዱን የታጠበ ፀጉር ላይ እንቀባዋለን፡፡ ከ15- 20 ደቂቃ በኋላ ፀጉራችንን በሻምፖ/በሳሙና በደንብ መታጠብ፡፡ 

 ይሄንን ትሪትመንት በየወሩ መጠቀም እንችላለን፡፡

ማስጠንቀቂያ : 

ለወጥ የምንጠቀመው እርድ ሌላ ቅመም አብሮት ስለሚኖር ከወጥ እርድ ይልቅ ንፁህ እርድ አዘጋጅተን መጠቀም ይኖርብናል ፡፡

Comments (0)