ቬኒር ወይም "የሆሊውድ ፈገግታ" (Hollywood Smile)
የጥርስ ቬኒር (Veneers) ፈገግታዎን ለማሳመር በጥርስዎ ላይ የሚለጠፍ በጣም ቀጭን እና በትክክል እንዲገጥም ተደርጎ የሚዘጋጅ ሽፋን ነው። ይህ ሽፋን የተሰነጠቁ፣ የተሸረፉ፣ የበለዙ፣ ያልተስተካከሉ ወይም ክፍተት ያላቸውን ጥርሶች ገጽታ ለማሻሻል ይረዳል።
ቬኒር እንደ ፖርሲሌን (porcelain) ወይም ከጥርስ ቀለም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ኮምፖዚት (composite) ካሉ ጥራት ያላቸው ቁሳቁሶች የሚሠራ ሲሆን ተፈጥሯዊ እንዲመስል እና ከፈገግታዎ ጋር እንዲዋሃድ ተደርጎ በጥንቃቄ ይዘጋጃል።
ቬኒር በጣም ተወዳጅነትን እያተረፉ ካሉ የጥርስ ውበት ሕክምናዎች አንዱ ነው። ብዙ ሰዎች የሚመኙትን እና በራስ መተማመን የሚሰጠውን የተወለወለ "የሆሊውድ ፈገግታ" ለማግኘትም በጣም ቀላል እና ውጤታማ መንገድ ነው።
የጥርስ ቬኒር ለማን ያስፈልጋል?
የፈገግታውን ገጽታ ማሻሻል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ቬኒር ማሰራት ይችላል። ቬኒር የሚከተሉትንም የጥርስ እክሎች ለመሸፈን ይረዳል፦
- የተሸረፉ ወይም የተሰበሩ ጥርሶች
- በጥርሶች መካከል ያሉ ክፍተቶች (ዲያስተማ)
- በጥርስ ማንጫ (Whitening) አለቅም ያሉ እድፎች
- በጣም ትናንሽ የሆኑ ጥርሶች እና
- የተዛነፉ ጥርሶችን ለመሸፈን ያግዛል ።
እዚህ ላይ ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር ቬኒርን መጠቀም የሚችሉት ጥርስዎ ከከፍተኛ የጥርስ መቦርቦር (ካቪቲ) እና ከድድ በሽታ ነፃ ከሆነ ብቻ ነው። ከባድ የአፍ ውስጥ ጤና ችግር ካለብዎት ማንኛውም ጥርስዎን ለማስዋብ የሚደረግ ህክምናን ከማድረግዎ በፊት ችግሩ መታከም ይኖርበታል።
ቬኒር እና ክራውን ልዩነታቸው ምንድን ነው?
ሁለቱም የጥርስዎን ገጽታ ለማሻሻል የሚረዱ ቢሆንም ህክምናዎቹ የሚደረጉበት ዓላማ ግን ይለያያል።
ቬኒር (Veneer) ፈገግታዎን ለማሳመር እና ጥርስዎ ላይ የሚኖሩ የቀለም፣ ቅርጽ እና የውበት ጉድለቶችን ለመሸፈን የሚረዳ በጥርስዎ የፊት ለፊት ክፍል ላይ ብቻ የሚለጠፍ ቀጭን የፖርሲሌን ሽፋን ሲሆን ክራውን (Crown) ግን መላውን ጥርስ የሚሸፍን እንደ ኮፍያ የሚጠለቅ የጥርስን ገጽታ ከማሻሻል ባለፈ የተጎዱ፣ የላሉ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ የተቦረቦሩ ጥርሶችን ለማጠንከር የሚያገለግል የጥርስ ህክምና ነው።
ስንት አይነት የቬኒር ዓይነቶች አሉ?
በርካታ የቬኒር ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ለርስዎ የተሻለ የሆነው አማራጭ የሚወሰነው ማግኘት በሚፈልጉት የፈገግታ ደረጃ ነው።
- ኮምፖዚት ቬኒር (Composite veneers)
ኮምፖዚት ቬኒር መጠነኛ የሆኑ የጥርስ ውበት ጉድለቶችን ለመሸፈን ይረዳል። የጥርስ ሐኪምዎ የሚፈልጉትን ውጤት እንዲያገኙ በጥርስ ጥገና ህክምና (dental bonding) ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለውን ከጥርስ ቀለም ጋር የሚመሳሰል ኮምፖዚት ሬዚን (composite resin) የተባለ ቁስ ይጠቀማል።
- ፖርሲሌን ቬኒር (Porcelain veneers)
ይህ ቬኒር ከጥርስዎ ቅርጽና አቀማመጥ ጋር እንዲገጥም ተደርጎ ለርስዎ ታስብዎ የሚሰራ (custom-made) የጥርስ ማስተካከያ ነው። ፖርሲሌን ቬኒር በርካታ የጥርስ ውበት ጉድለቶችን ለማስተካከል ቢረዳም ቬኒሮቹ ከመለጠፋቸው በፊት ግን ሐኪምዎ ተፈጥሯዊ ጥርስዎን በመሞረድ የጥርስ ሽፋንዎን (enamel) መቀነስ ይኖርበታል።
- ዝግጅት የማያስፈልገው (No-prep) ቬኒር
ይህ ልክ እንደ ፖርሲሌን ቬኒር ለርስዎ ታስብዎ በርስዎ ልክ የሚዘጋጅ ሲሆን የጥርስዎን ሽፋን ግን እንደ ፓርሲሌን ቬኒር ብዙም መሞረድ ሳያስፈልግ ጥቂት በመቀነስ ብቻ ይለጠፋል።
ዝግጅት የማያስፈልገው (No-prep) ቬኒር ለሁሉም ሰው ተስማሚ ስላልሆነ ይህን አማራጭ ከመምረጦ በፊት ሐኪምዎን ማማከር ያስፈልጋል።
- መውለቅ የሚችል (Removable) ቬኒር
"ስናፕ-ኦን" (snap-on) ተብሎ የሚጠራም ሲሆን በጥርስ ላይ የሚደረግ ጊዜያዊ ሽፋን ነው። ይህ የጥርስዎን ገጽታ ቢያሻሽልም ምግብ በሚመገቡበት እና በሚናገሩበት ጊዜ ግን እንደ ተፈጥሯዊ ጥርስ ምቾት ላይሰጥዎት ይችላሉ።
የቬኒር ህክምና ምን ይመስላል ?
የጥርስ ቬኒር ከመለጠፉ በፊት ምን ይከናወናል?
በመጀመሪያው ቀጠሮዎ የጥርስ ሐኪምዎ ጥርስዎን እና ድድዎን በመመርመር ለቬኒር ብቁ መሆንዎን ይወስናል። ብቁ ከሆኑም ጥርስዎን በመሞረድ እና ጥቂት የጥርስ ሽፋን (enamel) በመቀነስ ጥርስዎን ያዘጋጃል። በመቀጠልም የጥርስዎን ቅርጽ አሻራ (impression) በመውሰድ ወደ ላብራቶርይ ይልካል። የጥርስ ላብራቶሪ ባለሙያ ይህንን አሻራ በመጠቀም ለርስዎ የሚስማማ ቬኒር ያዘጋጃል። ኮምፖዚት ቬኒርን ከመረጡ ግን ሐኪሞ የጥርስዎን ቅርጽ አሻራ መውሰድ አያስፈልገውም።
የላብራቶሪ ባለሞያው ቬኒሮቹን አዘጋጅቶ ለመጨረስ ጥቂት ሳምንታት ሊወስድበት ይችላል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ሐኪምዎ እስከዚያው የሚቆዩ ጊዜያዊ ቬኒሮችን ሊያደርግልዎ ይችላል።
ቬኒር በሚለጠፍበት ወቅት ምን ይከናወናል?
በሁለተኛው የሕክምና ቀጠሮዎ ሐኪምዎ በላብራቶሪ የተዘጋጁትን የቬኒሮች ቅርጽ፣ ቀለም እና አገጣጠም ይፈትሻል። ከዚያም ልዩ የጥርስ ማጣበቂያ (cement) በመጠቀም በቋሚነት ጥርስዎ ላይ ይለጥፋቸዋል። ለጥፎ ከጨረሰ በኋላም የጥርስዎን አነካከስ በመፈተሽ አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን ያደርጋል።
ከሕክምናው በኋላ
ቬኒር ካስለጠፉ በኋላ የእረፍት ጊዜ መውሰድ ወይም ከስራ መቅረት አያስፈልጎትም። ቬኒሮን ባሰሩበት በዚያው ቀን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዎ መመለስ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከሕክምናው በኋላ ማደንዘዣው ሲለቆት ወዲያውኑ መብላት ወይም መጠጣት ይችላሉ።
የጥርስ ቬኒር ልዩ እንክብካቤ ያስፈልገዋል?
ቬኒርዎ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲቆይ ጥርስን መቦረሽ፣ በጥርስ ክር (flossing) ማጽዳት እና መደበኛ የጥርስ ህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። ጥርስዎን ሲቦርሹም ለስላሳ የጥርስ ብሩሽ እና ጥርስን የማይቧጭር (non-abrasive) የፍሎራይድ የጥርስ ሳሙና መጠቀምዎን ያረጋግጡ። ቬኒርዎን ሊቧጭሩ ስለሚችሉ ማንኛውም የጥርስ ማንጫ (whitening) ምርቶችን አይጠቀሙ።
ከዚህ በተጨማሪ ቬኒርዎ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉዎት እንደ አፕል፣ ጠንካር ያለ ሥጋ እና ካሮት ያሉ ደረቅ ምግቦችን በቀጥታ በጥርስዎ በመንከስ ከመቁረጥ ይቆጠቡ። ይልቁንም እነዚህን ምግቦች በሚመገቡበት ጊዜ ምግቦቹን ቆራርጠው በኋለኛው ጥርስዎ ያኝኩ።
ቬኒርዎ የፖርሲሌን ቬኒር ከሆነ እንደ እንጆሪ (berries)፣ ቀይ ወይን፣ ቡና እና ሻይ ያሉ ጥቁር ቀለም ያላቸው ምግቦችን እና መጠጦችን ባይወስዱ ይመከራል። እነዚህ ምግቦችና መጠጦች በጊዜ ሂደት በቬኒርዎ ላይ የማይለቅ እድፍ ሊያመጡ ይችላሉ።
የጥርስ ቬኒር የሚሰጣቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
የጥርስ ቬኒር ከሚሰጣቸው በርካታ ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
- የፈገግታዎን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽላል
- ከተፈጥሯዊ ጥርስ ጋር የተጣጣመ ውጤት ይሰጣል
- ከተፈጥሮ ጥርስ ሽፋን (enamel) ጋር ሲነፃፀር እድፍን የመያዝ እድሉ ዝቅተኛ ነው።
- ሁል ጊዜ ለጥርስዎ ከሚያደርጉት እንክብካቤ የተለየ ተጨማሪ ጥበቃ ወይም እንክብካቤ አያስፈልገውም
- ተገቢውን እንክብካቤ ከተደረገለት ከ10 እስከ 15 ዓመታት ሊቆዩ ይችላል
የቬኒር ጉዳቶች ምንድን ናቸው?
ቬኒር የተወሰኑ ጉዳቶችንም ሊያስከት ይችላል። ከእነዚህም ውስጥ ፦
- ቢያንስ የተወሰነውን የጥርስዎን ተፈጥሯዊ ሽፋን (enamel) እንዲያጡ ያደርጋል
- ብዙዎቹ የቬኒር ዓይነቶች አንዴ ከተለጠፉ በኋላ ጥርስዎ ወደ ነበረበት ገፅታው መመለስ አይችልም
- ሙቅ እና ቀዝቃዛ ነገሮችን ሲወስዱ የጥርስ ህመም ሊሰማዎት ይችላል
- ቬኒሩ ሊላቀቅ ወይም ሊወልቅ የሚችልበት አጋጣሚ አለ
ከዚህም በተጨማሪ ቬኒር ተገቢውን እንክብካቤ ካልተደረገለት ከቬኒሩ በታች ያለው የተፈጥሮ ጥርስ ሊበሰብስ ወይም ሊቦረቦር ይችላል።
የጥርስ ቬኒር ቋሚ የጥርስ ማስተካከያ ነው?
አብዛኛዎቹ የጥርስ ቬኒሮች ቋሚ ናቸው፤ ይህም ማለት አንዴ ከተደረጉ በኋላ ወደ ነበርዎት ተፈጥሯዊ ጥርስ መመለስ አይችሉም። ነገር ግን ያሰሩት የቬኒር አይነት "no-prep" ወይም "minimal prep" ቬኒር ከሆነ ጥርስዎ ወደ ነበረበት ገጽታ ሊመለስ ይችላል።
በአማካይ የጥርስ ቬኒሮች ተገቢው ጥበቃ እና እንክብካቤ ከተደረገላቸው ከ10 እስከ 15 ዓመታት ይቆያሉ።
ቬኒሮቼን በጥሩ ሁኔታ ለማቆየት ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
ቬኒሮችዎ ውበታቸው ሳይቀንስ በጥሩ ሁኔታ እንዲቆዩ ለማድረግ፦
- ለስላሳ የጥርስ ብሩሽ እና ጥርስን የማይቧጭር የፍሎራይድ የጥርስ ሳሙና በመጠቀም በቀን ሁለት ጊዜ ይቦርሹ
- በቀን አንድ ጊዜ በጥርስዎ መካከል ያለውን ክፍተት በክር (floss) ያጽዱ
- በቀን ሁለት ጊዜ ባክቴሪያን የሚከላከል የአፍ ማጠቢያ (mouthwash) ይጠቀሙ
- ጥርስዎን ነገሮችን ለመክፈት ወይም ለመቁረጥ ከመጠቀም ይቆጠቡ
- ለመደበኛ ምርመራ እና የጥርስ ጽዳት የጥርስ ሐኪምዎን ይጎብኙ
በአጠቃላይ ጥሩ የአፍ ንጽህና እና መደበኛ የጥርስ ሕክምና ክትትል የቬኒርዎን ዕድሜ ለማርዘም እንዲሁም ተፈጥሯዊና ጤናማ ፈገግታ እንዲኖርዎት ይረዳል።


