ሩማቶይድ አርትራይተስ እና 4ቱ ደረጃዎቹ

Eyasu Yebeltal
Jun 8, 2026
undefined

              ሩማቶይድ አርትራይተስ እና 4ቱ ደረጃዎቹ

ሩማቶይድ አርትራይተስ በመገጣጠሚያዎች ላይ የሚከሰት ሥር የሰደደ በሽታ ነው። ሩማቶይድ አርትራይተስ የሚከሰተው እንደ ኦስቲዮ አርትራይተስ በማርጀት፣ በመዳከም እና በመቀደድ ምክንያት ሳይሆን የሰውነት በሽታ መከላከል ስርዓት በስህተት የራሱን የመገጣጠሚያዎች ሽፋን ሲያጠቃ እና እብጠት እንዲሁም ህመም ሲያመጣ ነው። በአግባቡ ካልታከመ በጊዜ ሂደት ይህ እብጠት መገጣጠሚያዎችን ሊጎዳ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ሊጎዳ ይችላል።

የሩማቶይድ አርትራይተስን ደረጃዎች መረዳት ሕመምተኞች ምልክቶችን አስቀድመው እንዲያውቁ፣ ወቅታዊ ህክምና እንዲፈልጉ እና የበሽታውን እድገት ለመቀነስ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ስለሚረዳ በዚህ ጽሁፍ በዝዝርዝር እናያለን።

      የሩማቶይድ አርትራይተስ መንስኤ ምንድን ነው?

ሩማቶይድ አርትራይተስ የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ስርዓት በስህተት ሳይኖቪየም የተሰኘ በመገጣጠሚያዎች ላይ ያለ የሕብረ ሕዋስ ሽፋንን ሲያጠቃ ይከሰታል። የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ስርዓት መገጣጠሚያን የሚያጠቃበት ትክክለኛው መንስኤ ባይታወቅም በርካታ ምክንያቶች የዚህ ህመም መከሰት አደጋን ሊጨምሩ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል:-

  • በቤተሰብዎ ውስጥ የሩማቶይድ አርትራይተስ ታሪክ መኖር
  • ሲጋራ ማጨስ
  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት
  • አንዳንድ ኢንፌክሽኖች
  • ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በብዛት ይጠቃሉ

በሽታው በጀመረበት ጥቂት ጊዜ ውስጥ የመገጣጠሚያ ጉዳት ሊጀምር ስለሚችል በጊዜ ምርመራ እና ሕክምና ማድረግ በጣም አስፈላጊ ናቸው።

     ደረጃ 1: ቀደምት የሩማቶይድ አርትራይተስ

በደረጃ 1 የበሽታ መከላከያ ስርዓት የመገጣጠሚያውን ሽፋን ማጥቃት ሲጀምር የሰውነት መቆጣት እና እብጠትን መገጣጠሚያው ላይ ያስከትላል። በዚህ የሩማቶይድ አርትራይተስ ደረጃ የተለመዱ ምልክቶች:-

  • የመገጣጠሚያ ህመም እና ርህራ
  • ጠዋት ጠዋት ከ 30 ደቂቃ በላይ የሚቆይ የመገጣጠሚያ ግትርነት
  • በመገጣጠሚያዎች አካባቢ መጠነኛ እብጠት
  • ድካም
  • አጠቃላይ የሰውነት ሕመም ስሜት 

ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ እንደ የእግር እና የእጅ የጣቶች፣ የእጅ አንጓዎች እና ቁርጭምጭሚት ያሉ ትናንሽ መገጣጠሚያዎች በዚህ ይጠቃሉ። በዚህ ደረጃ የመገጣጠሚያዎች መጎዳት በ ኤክስ.ሬይ ላይ ገና ላይታይ ሲችል የደም ምርመራዎች ከሩማቶይድ አርትራይተስ ጋር የተዛመዱ ፀረ እንግዳ አካላትን ሊያሳዩ ይችላሉ። በጊዜ በዚህ ደረጃ ህክምናን መጀመር ዘላቂ ጉዳትን ለመከላከል እና የህይወት ጥራትን ለመጠበቅ ጥሩ እድልን ይሰጣል።

      ደረጃ 2: መካከለኛ የሩማቶይድ አርትራይተስ

የበሽታ መከላከል ስርዓት መገጣጠሚያዎችን ማጥቃት በሚቀጥልበት ጊዜ መገጣጠሚያ ውስጥ ያሉ የአጥንት ጫፎችን የሚሸፍን ካርቲሌጅ የተሰኘ የአካል ክፍልን ይጎዳል። የተቆጣው ሳይኖቪየም እየወፈረ በመሄድና ካርቲሌጅን በመጉዳት ታካሚዎች የተከደነ እቃ እንደ መክፈት፣ መፃፍ ወይም መራመድ የመሳሰሉ ቀላል ተግባሮችን ለማከናወን የበለጠ ፈታኝ ይሆንባቸዋል። በዚህ ደረጃ የተለመዱ ምልክቶች:-

  • የመገጣጠሚያ ህመም መባባስ እና የእብጠት መጨመር
  • የእንቅስቃሴ እና የመተጣጠፍ ብቃት መቀነስ
  • ጠዋት ጠዋት የማያቋርጥ የመገጣጠሚያ ግትርነት
  • የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን መቸገር
  • የድካም መባባስ 

በዚህ ደረጃ የሚደረግ የህክምና ግብ በመድሃኒት፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና በመደበኛ የሕክምና ክትትል እብጠትን መቆጣጠር እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ነው።

      ደረጃ 3: ከባድ የሩማቶይድ አርትራይተስ

በደረጃ 3 ሩማቶይድ አርትራይተስ የመገጣጠሚያ ብግነት ሁለቱንም ካርቲሌጅ እና አጥንትን ይጎዳል። የአጥንት መበላት ከፍተኛ በመሆን መገጣጠሚያዎችን ደካማ ሲያደርግ እንደ ኤክስ.ሬይ ወይም ኤም.አር.አይ ስካን ባሉ የምስል ምርመራዎች ላይ ጉዳቱ ይታያል። በዚህ ደረጃ የተለመዱ ምልክቶች:-

  • ከባድ ህመም እና እብጠት
  • የመገጣጠሚያ ተግባርን በከፍተኛ ሁኔታ ማጣት
  • የሚታይ የመገጣጠሚያ ጥመት
  • በተጎዱ መገጣጠሚያዎች ዙሪያ ያሉ ጡንቻዎች መድከም
  • የአካል ጉዳት

በዚህ የህመም ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በስራ፣ በቤት ለቤት ስራዎች እና በእንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ችግር ሲያጋጥማቸው፣ በከባድ ህመም እና ራስ በራስ የመቻል ችግር ምክንያት እንደ ጭንቀት ወይም ድብርት ያሉ ስሜታዊ ተግዳሮቶች ሊከሰቱባቸው ይችላሉ።

     ደረጃ 4፡ የመጨረሻ ደረጃ የሩማቶይድ አርትራይተስ

ደረጃ 4 የሩማቶይድ አርትራይተስ የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን አንዳንዴ የመገጣጠሚያ ብግነት ሊቀንስ ቢችልም ከባድ የስካል ጉዳት በቋሚነት ይቀራል። ካርቲሌጅ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እና የመገጣጠሚያ ጫፍ ላይ ያሉ አጥንቶች አንድ ላይ ሊዋሃዱ ስለሚችሉ የመገጣጠሚያውን እንቅስቃሴ በእጅጉ ይገደባል። በዚህ ደረጃ ላይ የተለመዱ ምልክቶች:-

  • ከባድ የመገጣጠሚያ ግትርነት
  • የመገጣጠሚያ ተግባርን ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፍተኛ ደረጃ ማጣት
  • ሥር የሰደደ ሕመም
  • ጉልህ የሆነ የአካል ጉዳት
  • ከባድ የመገጣጠሚያ መጣመም

በዚህ የህመም ደረጃ ላይ የሚደረግ ህክምና ህመምን በመቆጣጠር፣ ተንቀሳቃሽነትን በመጠበቅ እና የህይወት ጥራትን በማሻሻል ላይ ሲያተኩር አንዳንድ ሕመምተኞች የመገጣጠሚያ ንቅለ ተከላት ቀዶ-ጥገና ወይም ሌሎች የአጥንት ህክምና ሂደቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።

     ሩማቶይድ አርትራይተስ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ሊጎዳ ይችላል?

አዎ። ሩማቶይድ አርትራይተስ ሥርዓታዊ በሽታ ነው። ይህም ማለት በመገጣጠሚያዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰውነት ክፍሎችንም ሊጎዳ ይችላል። ሊከሰቱ ከሚችሉ የሌላ አካል ክፍል ህመሞች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  • የዓይን ብግነት
  • የሳንባ በሽታ
  • የልብ በሽታ
  • የደም ቧንቧ ብግነት
  • የአጥንት መሳሳት
  • የደም ማነስ

መደበኛ የሆነ አጠቃላይ የሕክምና ምርመራ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።

     የሩማቶይድ አርትራይተስ እንዴት ይታከማል?

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ለሩማቶይድ አርትራይተስ ምንም ዓይነት ሙሉ በሙሉ ፈውስ የሚሰጥ መድሃኒት ባይኖርም፣ ዘመናዊ ሕክምና የበሽታውን ምልክቶች እና እድገት በእጅጉ ይቀንሳሉ። የሩማቶይድ አርትራይተስ ዋና ዋና ሕክምናዎች:- 

  • በሽታ አስተካካይ ፀረ-ሩማቶይድ መድኃኒቶች (DMARDs)
  • ባዮሎጂካል መድሃኒቶች
  • ፀረ-ብግነት መድኃኒቶች
  • የአካል እና የሙያ ህክምና
  • መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
  • ሲጋራ ማጨስ ማቆም
  • ጤናማ ክብደትን መጠበቅ 

ቀድሞ በጊዜ ህክምና መጀመር የረጅም ጊዜ መባባስ እና ችግሮችን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ ነው።

Comments (0)