የስኳር በሽታ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች (Diabetic Blisters) ምንድን ናቸው? መቼስ ሊያሳስቡን ይገባል?

Elsabet Azezew
Jun 10, 2026
undefined

 

                   የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ውሃ የቋጠረ ቁስል  (Diabetic Blisters)

የስኳር በሽታ ካለብዎ እና በድንገት በቆዳዎ ላይ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች ከወጣብዎ በስኳርዎ ምክንያት ሊሆን ይችላሉ። በሕክምናው እነዚህ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች (Diabetic Blisters) ቡሎሲስ ዲያቤቲኮረም (bullosis diabeticorum) ወይም ዲያቤቲክ ቡሌ (diabetic bullae) ተብለው ይጠራሉ።

እነዚህን ቁስሎች መጀመሪያ ላይ ሲያስተውሏቸው የሚያስደነግጡ ቢሆኑም ምንም ዓይነት ሕመም የሌላቸው እና አብዛኛውን ጊዜ ጠባሳ ሳይጥሉ በራሳቸው የሚድኑ ናቸው።

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የቆዳ ችግሮች መካከል የስኳር በሽታ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች እምብዛም የማይከሰቱ ሲሆኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ 0.16 - 0.5% በሚሆኑት የስኳር በሽተኞች ላይ ብቻ ይከሰታሉ ።

በዚህ ጽሑፍ በስኳር ታማሚዎች ላይ ስለሚከሰቱ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች መንስኤ፣ ሕክምና እና መከላከያ መንገዶች በዝርዝር እናያለን።

          የስኳር በሽታ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች/ዲያቤቲክ ብሊስተርስ ምን ይመስላሉ? 

ዲያቤቲክ ብሊስተር በብዛት ከጉልበት በታች በታፋ፣ በእግር እና በእግር ጣቶች ላይ ይወጣል። አንዳንዴ ግን በእጅ፣ በእጅ ጣቶች እና በክንድ ላይ ሊከሰት ይችላል።

እነዚህ ቁስሎች እስከ 15 ሴንቲ ሜትር ሊደርሱ የሚችሉ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን መጠናቸው አነስተኛ ነው። እነዚህ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች እሳት ሲያቃጥል ከሚወጡ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ ምንም ዓይነት ሕመም ግን የላቸውም።

ዲያቤቲክ ብሊስተር ብዙ ጊዜ እንደ ነጠላ ቁስል ከመከሰት ይልቅ ብዙ ቁስሎች በአንድ ላይ ተከማችተው ይወጣሉ።እነዚህ ቁስሎች በውስጣቸው ንጹህ ፈሳሽ የሚይዙ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም የማሳከክ ስሜት ይኖራቸዋል። 

በቁስሎቹ ዙሪያ ያለው ቆዳ አብዛኛውን ጊዜ አይቀላም ወይም አያብጥም ነገር ግን ቆዳው ከቀላ ወይም ካበጠ ኢንፌክሽን መኖሩን ሊያመለክት ስለሚችል ወዲያውኑ ሐኪምዎን ያማክሩ።

          የዲያቤቲክ ብሊስተርስ (Diabetic Blisters) መንስኤው ምንድን ነው?

የዲያቤቲክ ብሊስተር ትክክለኛ መንስኤ ሙሉ በሙሉ አይታወቅም። አብዛኛውን ጊዜም ያለምንም ግልጽ ጉዳት ወይም ምክንያት በቆዳ ላይ ሊወጣ ይችላል።

ይሁን እንጂ የሚከተሉት ሁኔታዎች እነዚህ ቁስሎች የመፈጠር እድላቸውን ሊጨምሩ ይችላሉ፦

  • በትክክል ያልተቆጣጠሩት ከፍተኛ የደም ስኳር መጠን
  • በስኳር በሽታ ምክንያት የሚከሰት የነርቭ ጉዳት (ዲያቤቲክ ኒውሮፓቲ)፦ ቆዳ ላይ ያሉ የስሜት ህዋሳትን አቅም የሚቀንስ እና ጉዳቶች ሲደርሱ ለማስተዋል አስቸጋሪ የሚያደርግ የነርቭ ጉዳት ዓይነት ነው
  • ደካማ የደም ዝውውር፦ ይህ ብዙውን ጊዜ ፐሪፈራል አርተርይ ዲዝዝ (peripheral artery disease) በሚባል የደም ቧንቧ ችግር ምክንያት የሚከሰት ነው። 
  • ጠበብ ወይም ልክዎ ያልሆኑ ጫማዎችን ሲያደርጉ በሚፈጠር ግጭት
  • የፈንገስ ኢንፌክሽኖች ለምሳሌ ካንዲዳ አልቢካን (Candida albicans) በተባለ የፈንገስ ዓይነት የሚመጣ ኢንፌክሽን

የነርቭ ጉዳት ወይም የደም ዝውውር ችግር ያለባቸው የስኳር ታማሚዎች በተለይም በተረከዝ እና በታችኛው የእግራቸው ክፍል ላይ እነዚህ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች የመፈጠር ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ የደም የስኳር መጠንዎን በመቆጣጠር እና እግርዎን ዘወትር በማየት እና በመፈተሽ ተጋላጭነትዎን ይቀንሱ።

       ለዲያቤቲክ ብሊስተርስ የሚደረገው ሕክምና ምን ይመስላል?

ዲያቤቲክ ብሊስተርዎች ብዙውን ጊዜ ከ2 እስከ 6 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ በራሳቸው ጊዜ የሚድኑ በመሆናቸው ልዩ ሕክምና አያስፈልጋቸውም።

ቁስሎቹ እስኪድኑ ድረስ የኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚከተሉትን ያድርጉ፦

  • ውሃ የቋጠሩትን ቀስሎች በራስዎ አይፈንዱ 
  • ቁስሎቹን በንጽህና በመያዝ በፋሻ (bandage) ይሸፍኑ
  • ውሃ የቋጠረው ቀስል ትልቅ፣ ህመም ያለው ወይም ለመራመድ እና ጫማ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር  ከሆነ ሐኪምዎን በማማከር ቁስሉ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ በጥንቃቄ እንዲያስወግድሎት ማድረግ ይችላሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ሐኪምዎ የአንቲባዮቲክ ክሬሞች ወይም ቅባቶች ሊያዝሎት ይችላል። ማሳከኩ ከባድ ከሆነም የስቴሮይድ ክሬም ይታዘዝሎታል። 

ከሁሉም በላይ ግን የደም የስኳር መጠንዎን በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ዲያቤቲክ ብሊስተር በፍጥነት እንዲድን እና ወደፊት የሚወጣበትን ዕድል ለመቀነስ የሚረዳ እጅግ በጣም አስፈላጊው እርምጃ ነው።

     ዲያቤቲክ ብሊስተርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የስኳር ሕመም ካለብዎ ለቆዳዎ እና ለእግርዎ ጥሩ እንክብካቤ ማድረግ ዲያቤቲክ ብሊስተር እንዳይወጣ ለመከላከል እና ለኢንፌክሽን የሚኖርን ተጋላጭነት ለመቀነስ ይረዳል።

ሊወስዷቸው የሚችሏቸው አንዳንድ ቀላል እርምጃዎች የሚከተሉት ያካትታሉ

  • እግርዎ ላይ ማንኛውም ቁስል ፣ የቆዳ መቆጣት ወይም ሌሎች ለውጦች አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ በየቀኑ እግርዎን በደንብ ይፈትሹ 
  • እግርዎን ከጉዳት እና ከግጭት ለመከላከል ልክዎ የሆኑ ጫማዎችን እና ንጹህ ካልሲዎችን ያድርጉ
  • በቆዳ ላይ የሚፈጠርን ፍትጊያ እና ጫና ለማስወገድ አዳዲስ ጫማዎችን ሲገዙ ቀስ በቀስ እያለማመዱ ይጫሟቸው
  • መቀስ ፣ የእጅ መሳሪያዎችን እና ውሃ የቋጠረ ቁስል ሊይስከትሉ የሚችሉ የአትክልተኝነት እቃዎችን ሲጠቀሙ ጓንት ያድርጉ
  • የፀሐይ መከላከያ ክሬም በመጠቅም እና ፀሐይ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ በመቀነስ በፀሐይ  ጨረር ምክንያት በአንዳንድ ሰዎች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ውሃ የቋጠረ ቁስል ይከላከሉ። 

     ለዲያቤቲክ ብሊስተርዎ ሐኪም ማማከር መቼ ያስፈልጋል?

አብዛኛዎቹ ዲያቤቲክ ብሊስተርዎች በራሳቸው ጊዜ የሚድኑ እና ህክምና የማያስፈልጋቸው ቢሆንም የኢንፌክሽን ምልክቶች አለመኖራቸውን ግን መከታተል ያስፈልጋል።

የሚከተሉትን ካስተዋሉ ሐኪምዎን ያማክሩ፦

  • በቁስሉ ዙሪያ መቅላት
  • ማበጥ
  • በቁስሉ አካባቢ ያለው ቆዳ ላይ የሙቀት ስሜት መኖር
  • ህመም ወይም 
  • ትኩሳት 

እነዚህ ምልክቶች የኢንፌክሽን መኖርን ሊያሳዩ ስለሚችሉ በአስቸኳይ በሐኪም መታየትና መመርመር ይኖርብዎታል።

Comments (0)