የጉበት ስብ | Fatty Liver

Melat Geatchew
Jun 10, 2026
undefined

የጉበት ስብ | Fatty Liver

ጉበታችን ከሰውነታችን ክፍል ውስጥ ሁለተኛ ትልቁ አካል ሲሆን የምንመገበውንም ፣የምንጠጣውን አና ማንኛውንም ለሰውነት ጠቃሚ ያልሆነ ነገረን ከደማችን ያጣራል።ጉበት ከ500 በላይ ሥራዎችን የሚያከናውን ዋነኛ እና ሁለገብ የሰውነታችን አካል ነው የጉበት ይህን የማከናወን ስራ በጉበት ስብ መብዛት ሊዛባ ይችላል።

 

የጉበት ተግባራት በአራት ዐቢይ ክፍሎች ይመደባል

  • የመጀመሪያው ተግባሩ፤ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ከደም ውስጥ ማጽዳት፣ ቆሻሻ ምርቶችን ማስወገድ፣ የመድኃኒቶችን ሜታቦሊዝም ማከናወን፣ ከምንበላው፣ ከምንጠጣው እና ከምንተነፍሰው ሁሉ መርዞችን ማስወገድ ነው ይላሉ።
  • እንዲሁም ሁለተኛው ተግባሩ፤ ቫይታሚኖችን፣ ማዕድናትን እና ኃይልን ማከማቸት መሆኑን ገልጸው፤ ለሰውነታችን ማበረታቻ ኃይል በሚያስፈልግበት ጊዜ ዝግጁ ማድረግ ነው ብለዋል።
  • ሦስተኛው ተግባር ደግሞ፤ ለደም መርጋት እና ኢንፌክሽኖችን ለመዋጋት ፕሮቲኖችን ማመንጨት መሆኑን ያስረዳሉ።
  • አራተኛው ተግባሩን ሲያብራሩም፤ ‘Bile’ የሚባል ንጥረ ነገር በማምረት ከሚወዷቸው (ከሚመገቧቸው) ምግቦች ውስጥ የሚገኘውን ስብ እንዲፈጭ ያደርጋል

 የጉበት ስብ ምንድነው?

የጉበት ስብ የምንለው በጉበት ውስጥ የሚገኘው የስብ መጠን ከ 5-10 በመቶ (ከ 5-10 %) የሚሆነውን የጉበት ክፍል ከያዘ ነው። በአሁኑ ጊዜ በጣም እየተለመደ የመጣ ቢሆንም፤ የጉበት ስብ ይህ ነው የሚባል የራሱ የሆነ ምልክት ላያሳይ ስለሚችል ብዙ ሰዎች በደማቸው ውስጥ ስብ መኖሩን እንኳ ሳያውቁት ይኖራሉ። የጉበት ስብ በራሱ ሁልጊዜ ከባድ የጉበት ጉዳት ማለት አይደለም። ነገር ግን በአንዳንድ ሰዎች ስብ ከመከማቸት በላይ የጉበት እብጠትና የሴሎች ጉዳት ሊከሰት ይችላል።

 

ለጉበት ስብ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

  • ከልክ ያለፈ ውፍረት
  • የስኳር ህመም
  • የአልኮል መጠጥ አብዝቶ መጠጣት
  • እርግዝና
  • ከፍተኛ የኮሌስቴሮል መጠን
  • ከፍተኛ የትራይግላይሴራይድ መጠን ናቸው።

የጉበት ስብ አይነቶች

በሽታው በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ይከፈላል፦

  1. ከአልኮል ጋር የተያያዘ (Alcohol-associated liver disease) 

    ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት በጉበት ውስጥ ስብ እንዲከማች፣ እብጠት እንዲፈጠርና በኋላም ጠባሳ እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።

  2. ከአልኮል ውጭ የሚከሰት MASLD 

    — Metabolic dysfunction-associated steatotic liver disease ተብሎ ይጠራል።ይህ በዓለም ላይ በጣም የተለመደው የጉበት በሽታ ነው። ይህ 10% በሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚታይ ሲሆን ጉበታችን በጤናማ ሁኔታ ስብን ማቅልውጥ ሲያቅተው በሚከማች ስብ ምክንያት ነው።

በተለይ ፦

  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት በተለይ በሆድ አካባቢ የሚከማች ስብ
  • በአይነት 2 የስኳር በሽታ
  • ከከፍተኛ ኮሌስትሮል
  • የሜታቦሊክ ሲንድሮም ባላቸው ሰዎች ላይ
  • ኢንሱሊን በአግባቡ ስራውን ካልሰራ ስብ በጉበት ውስጥ ይከማቻል።

     

  • በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የጉበት ስብ

ይህ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል አይነት የጉበት ስብ ሲሆን ምልክቱ በሶስተኛው የእርግዝና ክፍለ ጊዜ ማለትም ከ 28ኛው ሳምንት በኋላ የሚከሰት ነው።

 

የበሽታው ደረጃዎች

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሽታው አራት አደገኛ ደረጃዎች አሉት።

 

  • በመጀመሪያ በቀላል የስብ ክምችት (Steatosis) የሚጀምር ሲሆን፣
  • ካልታከመ ግን ወደ ጉበት መቆጣት (MASH)(20% of NAFLD Patients, cell ballooning , inflammation and cell damage)
  • ከዚያም ወደ ጉበት ጠባሳ (Fibrosis) እና
  • በመጨረሻም ወደማይመለስ የጉበት መጥፋት ወይም ሲሮሲስ (Cirrhosis) ይሸጋገራል።

ለየጉበት ስብ የሚያጋልጡ ነገሮች

  • ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ መጠጣት
  • የሆድ አካባቢ ውፍረት (Belly Fat) እና ከመጠን በላይ ክብደት/ውፍረት
  • የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል በተለይ ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት
  • ጣፋጭ መጠጦች እና ቅባት የበዛባቸው ምግቦች ማዘውተር
  • የ2ኛው አይነት ስኳር በሽታ (Type 2 Diabetes)
  • ከፍተኛ የደም ግፊት
  • ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን
  • ሲጋራ ማጨስ
  • በቤተሰብ ታሪክ

ምልክቶቹ ምን ምን ናቸው? 

የጉበት ስብ መጥፎ ባህሪ ምንም አይነት ግልጽ ምልክት አለማሳየቱ ነው። ነገር ግን ህመሙ እየጨመረ ሲሄድ የሚከተሉት ሊታዩ ይችላሉ፦

  •  ሁልጊዜ የድካም እና የመዝልፍልፍ (የመዛል) ስሜት መሰማት። 
  • በሆድ የላይኛው ቀኝ ክፍል አካባቢ የህመም ወይም የመጨምደድ ስሜት። 

     

    ከባድ የጉበት ስብ በሽታ ሲኖር ሊታዪ የሚችሉ ምልክቶች ፦

  • ማስመለስ ፣ ማቅለሽለሽ ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • የዓይን እና የቆዳ ቢጫ መሆን
  • የሽንት ቀለም መጥቆር
  • የሆድ እብጠት
  • የእግር ወይም የእጅ እብጠት
  • የሰገራ ቀለም መጥቆር
  •  ያለምንም ምክንያት የክብደት መቀነስ 

እንዴት ይታወቃል (ምርመራ) | Diagnosis? 

ምልክቶቹ ግልጽ ስላልሆኑ፤ አብዛኛውን ጊዜ በሽታው የሚታወቀው ለሌላ ምርመራ በሚደረግ የደም ምርመራ ላይ የጉበት ኢንዛይሞች ከፍ ብለው ሲገኙ ነው። 

 በተጨማሪም የሚከተሉት ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ፡-

  • የደም ምርመራ (Blood Test)፦ የጉበት ኢንዛይም መጨመር ወይም የጉበት ስራ ጤናማ አለመሆኑን ያሳያል።
  • የምስል ምርመራ (Imaging Tests)፦ አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን (CT scan)፣ ወይም የጉበት ምርመራ (Fibro Scan) በጉበት ውስጥ ስብ መከማቸቱን ለማወቅ ይረዳሉ
  • የጉበት ባዩፕሲ (Liver Biopsy)፦ አልፎ አልፎም የጉበቱን ጉዳት መጠን ለማወቅ ከጉበት ላይ ጥቂት ቁራጭ ተወስዶ የሚደረግ ምርመራ ነው።

የጉበት ስብ እንዴት ይታከማል?

እስካሁን ድረስ የጉበት ስብ ይህ ነው የሚባል ህክምና ፣መድሀኒትም ሆነ ቀዶ ጥገና ስለሌለው የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ፣ መቀየር እና ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮችን መቆጣጠር ተቀዳሚ ተግባራት መሆን አለባቸው  ።

 እነዚህም:-

  • አልኮልን ማስወገድ፦ ለማንኛውም ዓይነት የጉበት ስብ በሽታ አልኮልን ማቆም ወሳኝ ነው። 
  • ክብደትዎን መቀነስ ፦ ከሰውነት ክብደት ላይ ከ5-10% መቀነስ በጉበት ጤና ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።  
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ በሳምንት ቢያንስ ለ150 ደቂቃዎች ያህል መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ። 
  • ሌሎች ተያያዥ በሽታዎችን መቆጣጠር፦  የኮሌስቴሮል እና የስኳር መጠንዎን መቆጣጠር እና መጠንን በአግባቡ መከታተል ናቸው።
  • ጤናማ አመጋገብ፦ እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም አነስተኛ ስብ ያላቸው ፕሮቲኖች ላይ ያተኩሩ። ጣፋጭ መጠጦችንና ምግቦችን ያስወግዱ። በተለይ ፋይበር ያላቸውን ምግቦች (አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ) ማዘውተር፤ ስኳርና ነጭ ዱቄት የበዛባቸው ምግቦችን መቀነስ፤ ብዙ የተጠበሱ ምግቦች እና processed foods ማስወገድ
  • ያለ ሐኪም ምክር የሚወሰዱ መድሃኒቶችን ወይም የባህል መድሃኒቶችን አይጠቀሙ።
  • መደበኛ ምርመራ፦ የጉበት ኢንዛይሞችን በየጊዜው መመርመር።

Comments (0)