ማያስቴኒያ ግራቪስ ምንድን ነው?
ማያስቴኒያ ግራቪስ የነርቭ እና የጡንቻ ግንኙነት መዛባት ህመም ሲሆን በሰውነታችን የሚመነጩት የበሽታ ተከላካይ ህዋሳት (ነጭ የደም ህዋሳት) በስህተት የነርቭ እና የጡንቻ መገናኛን ሲያጠቁ የሚፈጠር ከባድ የጡንቻ ድካም ነው። የሚያጠቃውም የአይን ፣ የፊት እንዲሁም በሰውነታችን ላይ ያሉትን የአጥንት ጡንቻዎች ነው።
በዚህም መሰረት ማያስቴኒያ ግራቪስ የአይን ማያስቴኒያ (Ocular myasthenia gravis) እና አጠቃላይ ማያስቴኒያ (Generalized myasthenia gravis) ተብሎ በሰፊው ይከፈላል።
መንስኤውስ ምንድን ነው?
ጤናማ በሆነ ሰውነት ውስጥ ጡንቻዎቻችን ሊንቀሳቀሱ (ሊኮማተሩ ወይም ሊላሉ) የሚችሉት ከአንጎላችን በነርቭ አማካኝነት ትዕዛዝ ሲደርሳቸው ነው። አንጎላችን ጡንቻዎቻችን እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ የነርቭ ፋይበር ጫፎች 'አሲታይልኮሊን’ (Acetylcholine) የሚባል ኬሚካል ያመነጫሉ። ይህ 'አሲታይልኮሊን’ የተባለ ንጥረ ነገር በጡንቻው ላይ ካለው የአሲታይልኮሊን መቀበያ (Receptor) ጋር በመቆራኘት ጡንቻው እንዲኮማተርና እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል።
በማያስቴኒያ ግራቪስ የተጠቃ ሰውነት ውስጥ ያሉት የበሽታ ተከላካይ/ነጭ የደም ህዋሳት ግን ኢሚዩኖ-ግሎቡሊን ጂ (Immunoglobulin G ; IgG) በመባል የሚጠሩ ፀረ-እንግዳ አካላትን በማመንጨት ከአሲታይልኮሊን መቀበያ (Receptor) ጋር እንዲቆራኙ ስለሚያደርጉ የአሲታይልኮሊን ኬሚካሎች የሚያያዙበት ቦታ እንዲያጡ ያደርጓቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ የነርቭ መልዕክቱን ከሚቀበሉት አካላት ጋር የተቆራኙት የፀረ-እንግዳ አካላት የመቀበያ ቦታዎችን በማጥቃት ጉዳት ያደርሱባቸዋል።
በፀረ-እንግዳ አካላት ጉዳት የደረሰባቸው የአሲታይልኮሊን ተቀባይ ቦታዎች ከአንጎል የሚመጣውን መልእክት መቀበል ስለማይችሉ ጡንቻው በቀላሉ እንዲደክም እና በተገቢው መጠን እንዳይንቀሳቀስ ያደርገዋል።
በማያስቴኒያ ግራቪስ የሚጠቁት እነማን ናቸው?
- ዕድሜ እና ጾታ፦ በሽታው በብዛት የሚከሰተው ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች በሆኑ ሴቶች ላይ እና ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ በሆኑ ወንዶች ላይ ነው።
- የታይመስ ዕጢ (Thymus) እክል፦የታይመስ ዕጢ ያለአግባብ ማደግ ወይም በዕጢው ላይ ዕብጠት (thymoma) ያለባቸው ሰዎች ለማያስቴኒያ ግራቪስ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ይህ የሆነበትም የታይመስ እጢ ፀረ-እንግዳ አካላትን የሚያመነጩ ነጭ የደም ህዋሳት እንዲፈጠሩና እንዲያድጉ ስለሚረዳ ነው።
- የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት መዛባት ከሚያመጡ በሽታዎች መካከል ሩማቶይድ አርትራይተስ (Rheumatoid arthritis) ፣ ሉፐስ (Lupus) እንዲሁም አንዳንድ የታይሮይድ እጢ(Thyroid) በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች በተጓዳኝ ማያስቴኒያ ግራቪስ ሊያጋጥማቸው ይችላል።
የማያስቴኒያ ግራቪስ ምልክቶች ምን ምን ናቸው?
የማያስቴኒያ ግራቪስ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።
- የጡንቻ ድካም/መስነፍ (Muscle weakness)
- ከፍተኛ ዝለት/የሰውነት ድካም (Fatigue)
- የዓይን ሽፋሽፍት መውረድ (Droopy eyelids)
- የደበዘዘ ወይም ድርብ ዕይታ (Blurry or double vision)
- የተገደበ የፊት ገጽታ (Limited facial expressions)
- የመራመድ ችግር (Trouble walking)
- ለመናገር፣ ለመዋጥ ወይም ለማኘክ መቸገር (Difficulty speaking, swallowing or chewing)
እነዚህ የማያስቴኒያ ግራቪስ ምልክቶች ቀኑ በገፋ እና አካላዊ እንቅስቃሴ በጨመረ ቁጥር የመባባስ ባህሪይ አላቸው ። ሆኖም ግን የደከሙት ጡንቻዎች በተወሰነ መጠን እረፍት በማድረግ ጥንካሬያቸውን መልሰው ማግኘት ስለሚችሉ፣ የማያስቴኒያ ግራቪስ ታካሚዎች አጫጭር እረፍቶችን በመውሰድ በሽታውን መቋቋም ይችላሉ።
ማያስቴኒያ ግራቪስ መድኃኒት አለው?
ከማያስቴኒያ ግራቪስ ሙሉ በሙሉ የሚያድን ፍጹም ፈውስ እስካሁን ባይኖርም፣ የታካሚዎችን የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴና ጤንነት በእጅጉ የሚያሻሽሉ ልዩ ልዩ መድኃኒቶች እና የሕክምና አማራጮች አሉ።
የመድኃኒት ሕክምናዎች
- የኮሊኒስተሬዝ ኢንሂቢተር (Cholinesterase inhibitors) : የነርቭ እና የጡንቻ ግንኙነትን የሚያሻሽሉ እንደ ፓሪዶስቲግሚን (Pyridostigmine) የመሳሰሉት መድኃኒቶችን ያካትታል።
- የሰውነት በሽታ መከላከያ ሥርዓትን የሚያስተካክሉ/የሚቀንሱ መድኃኒቶች (Immunosuppressive): በተለይም እንደ ኮርቲኮስቴሮይድ (Corticosteroid) ለማያስቴኒያ ግራቪስ ሕክምና ይሰጣሉ።
የአጭር ጊዜ እና የድንገተኛ ጊዜ ሕክምናዎች
- በደም ሥር የሚሰጥ ኢሚውኖግሎቡሊን (Intravenous Immunoglobulin - IVIG): ጤናማ የሆኑ ፀረ-እንግዳ አካላት በደም ሥር ለታካሚው በመስጠት፣ የበሽታ መከላከል ሥርዓቱ የሚያደርሰውን ጥቃት ለጊዜው እንዲያቆም ያደርጋሉ።
- ሞኖክሎናል አንቲቦዲ (Monoclonal Antibodies): እንደ ሪቱክሲማብ (Rituximab) እና ኤኩሊዙማብ (Eculizumab) ያሉ መድኃኒቶች በደም ሥር የሚሰጡ ሲሆኑ፣ በሽታውን የሚያባብሱ የተወሰኑ የበሽታ መከላከያ ሕዋሳትን ለይተው ያጠቃሉ።
- ፕላዝማፌሬሲስ /የደም ፕላዝማ ማጣራት/ (Plasmapheresis/Plasma Exchange): ይህ የሕክምና ሂደት ደምን ማጣሪያ ማሽን ውስጥ በማሳለፍ ጡንቻዎችን የሚያዳክሙትን ጎጂ ፀረ-እንግዳ አካላትን ከደም ውስጥ ለይቶ ያስወግዳል።
የቀዶ ጥገና ሕክምና
- የታይመስ ዕጢን በቀዶ ጥገና ማስወገድ (Thymectomy) ፡ በተጓዳኝ የታይመስ ዕጢ እክል ባለባቸው የማያስቴኒያ ግራቪስ ታካሚዎች የታይመስ ዕጢን በቀዶ ጥገና ማስወገድ የጡንቻ ድካም ምልክቶችን ይቀንሳል፣ የመድኃኒት አስፈላጊነትንም የመቀነስ እድል አለው። በተለይም አጠቃላይ (Generalized) ማያስቴኒያ ግራቪስ ባለባቸው ታካሚዎች ውስጥ ከህመሙ የማገገም እና የረጅም ጊዜ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ይሰጣቸዋል።
የማያስቴኒያ ግራቪስ ምልክቶችን ለመቀነስ ምን ማድረግ ይቻላል?
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አዘውትረው ያድርጉ፦ ይህ የጡንቻን ጥንካሬ ለመጨመር፣ ስሜትን ለማሻሻል እና ተጨማሪ ጉልበት ለማግኘት ይረዳል። ነገር ግን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም ከመጀመርዎ በፊት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ የሕክምና ባለሙያዎን ያማክሩ ።
- ሙቀት የበሽታውን ምልክቶች ስለሚያባብስ በጣም ሞቃት በሆነ የቀኑ ሰዓት ወደ ውጭ መውጣትን ይቀንሱ። ሙቀት ሲሰማዎት በአንገትዎ እና በግንባርዎ ላይ ቀዝቃዛ ጨርቅ (Cold compress) ያድርጉ።
- በምግብዎ ውስጥ በቂ ፕሮቲን (Protein) እና ካርቦሃይድሬት ያግኙ ፦ ይህም ተጨማሪ ጉልበት ይሰጥዎታል።
- በጣም አድካሚ የሆኑ ሥራዎችን ቀደም ብለው ያከናውኑ ፦ ሰውነትዎ ከፍተኛ ጥንካሬ በሚሰማው በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከባድ ሥራዎችን አስቀድመው ያጠናቅቁ።
- ቀኑን ሙሉ አጫጭር እንቅልፎችን ወይም የእረፍት ጊዜያትን ይውሰዱ ፦ በየመካከሉ ማረፍ የጡንቻን ኃይል ለመመለስ በእጅጉ ይረዳል።




