ዶፓሚን እና የስልክ ሱስ - ከስክሪን ጀርባ ያለውን አንጎል መረዳት

Eyasu Yebeltal
Jun 29, 2026
undefined

                 ዶፓሚን እና የስልክ ሱስ - ከስክሪን ጀርባ ያለውን አንጎል መረዳት

አንድ መልእክት ለማየት ብለው ስልክዎን አንስተው ራስዎን ለ30 ደቂቃ ተዘፍቀው አግኝተውት ይውቃለሉ? 

ስማርት ስልኮች የዘመናዊ ህይወት ወሳኝ አካል በመሆን ሰዎችን እንድናገኝ፣ እንድንግባባ፣ እንድንሰራ፣ እንድንማር እና እንድንዝናና ይረዱናል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከልክ በላይ በነዚህ ስልኮች ሱስ በመጠመድ ስልካቸውን ለማስቀመጥ ይቸገራሉ።

ይህ ችግር እርስዎም ላይ ካለ፣ ብቻዎን ስላልሆኑ እራስዎን አይውቀሱ! ምክንያቱም የዚህ ሱስ መንስኤ የአላማ ጽናት ስለሌልዎት ሳይሆን አንጎልዎ ዶፓሚን ለተባለው በሰው ልጅ ውስጥ ካሉ ኬሚካሎች በጣም ኃይለኛ ኬሚካላዊ መልእክተኛ በቀላሉ ምላሽ እየሰጠ ስለሆነ ነው።

የጤና ባለሙያዎች ከምን ጊዜውም በበለጠ በስክሪን ጊዜ ከልክ በላይ መብዛት ምክንያት ታካሚዎች ላይ የጭንቀት፣ የሃሳብ መበታተን እና የአካላዊ ድካም ከፍተኛ ጭማሪን እያስተዋሉ ይገኛሉ። ስልክዎ ኬሚካሎችን በመጠቀም አንጎልዎን እንዴት እንደሚጠልፍ መረዳት ይህን ተመጋጋቢ ዑደት መስበሪያ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።

       ዶፓሚን ምንድን ነው?

ሰዎች ዶፓሚንን "የደስታ ኬሚካል" ብለው ቢጠሩትም ይህ ሃሳብ ከእውነት የራቀ ነው። እውነታው ግን ዶፓሚን የመጠባበቅያ እና የመነሳሻ ኬሚካል ነው። እንድንፈልግ ይገፋፋናል እንጂ የፈለግነውን ስናገኝ አይከፍለንም። ቅድመ አያቶቻችን ሚዳቋን ለማደን ሲከታተሉ ወይም የጫካ ፍራፍሬዎችን ሲያገኙ አንጎል ዶፓሚን ኬሚካልን በመልቀቅ ለአእምሮ "ይህ ተግባር ለህልውና መቀጠል አስፈላጊ ነው። እንዳይረሳ!” የሚል መልእክትን ያስተላልፋል። ስለዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ዶፓሚን ሰዎች ከተፈጥሮ እና ልዩ ልዩ አደጋዎች እንዲተርፉ ረድቷቸዋል። አሁን ላይ ግን ይህ ትክክለኛ የአዕምሮ መቋቋሚያ ዘዴ ኪስ ውስጥ ባለ ትንሽዬ ሃይለኛ ኮምፒውተር ተጠልፏል።

      ስልክዎ አዕምሮዎን እንዴት መጥለፍ ይችላል?

የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች፣ የሞባይል ጨዋታዎች እንዲሁም የጽሁፍ መልእክቶች የአይምሯችንን ኬሚካላዊ የዶፓሚን መንገድ ለመጠቀም በጥንቃቄ የተሰሩ ናቸው። ይህንን የሚያደርጉት የተቆራረጠ ሽልማት በመባል በሚታወቅ የስነ-ልቦና ፅንሰ-ሀሳብ ነው። ይህ ፅንሰ-ሀሳብ በተመሳሳይ ዘዴ የቁማር ማሽኖች ሱስን ለማስያዝ በተግባር ላይ ይውላል።

ስልክዎን ባነሱ ቁጥር ምን እንደሚፈጠር እነሆ፡-

  • ማሳወቂያ (ቀስቃሽ)፡- የስልካችን ድምጽ፣ ብልጭ ብልጭ የሚል መብራት ወይም ንዝረት አንጎላችን በመቀስቀስ ወደ ስልካችን ይጠራል። ይህ ማስታወቂያ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ በሚመጣ ጉጉት ምክንያት ዶፓሚን በአንጎል ውስጥ ከፍ ይላል።
  • ፍለጋ (አደን)፡- የስልክ መተግበሪያን በመክፈት መፈለግ እንጀምራለን። ምናልባት የመጀመሪያውን ጽሁፍ ወይም ቪዲዮ ትንሽ እንዳየን ሊሰለቸን ይችላል፣ ወደ ሁለተኛው እንሄዳለን። ምናልባትም ሁለተኛውም እንዲሁ አሰልቺ ሊሆብን ይችላል፣ ወደ ሶስተኛው እንሄዳለን። ስለዚህም ሳናስተውል ረጅም ጊዜን በስልካችን ተጠምደን ደስታን መፈለግ እንቀጥላለን። ምክንያቱም አንጎል የሆነ የተሻለ አስቂኝ ቪዲዮ ወይም አስደሳች የዜና ዘገባ እንደሚያገኝ መገመት እና መጠበቅ ስለሚቀጥል ነው።
  • ሽልማት፡- ከተወሰነ ጊዜ ፍለጋ በኋላ ያን የተሻለ አስቂኝ ቪዲዮ ወይም የአስደሳች ዜና ዘገባ ስናገኝ አእምሮ ኬሚካል በመልቀቅ የእርካታ ፍንዳታን ያገኛል። ይህም የልምድ ምልልሱን በማጠናከር ወጥመድ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል። 

ቀጣዩ ምርጥ ቪዲዮ መቼ እንደሚመጣ ስለማናውቅ፣ አእምሮአችን በጉጉት በድጋሚ በመፈለግ እና በመጠበቅ የእርካታ ፍንዳታን ለማደስ ይፈልጋል።

      የዶፓሚን ዑደት ብልሽት እና የአእምሮ ጤና

የዶፓሚን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ማድረግ ችግሩ ምንድነው?

ችግሩ ሚዛን ነው። አንጎል መዝናናትን እና ህመምን በማመጣጠን በሚዛናዊነት ይሰራል። ለብዙ ሰዓታት በስልካችን በማሸብለል አንጎላችንን ከፍተኛ መጠን ባለው ዶፓሚን ስናጥለቀልቅ እራሱን ወደ ሚዛናዊነት ለመመለስ መሞከሩ የማይቀር ነው። ይህንን ሚዛናዊነት የሚመልሰው የአእምሮን ዶፓሚን ተቀባዮች በጊዜያዊነት በማውረድ ወይም በመቀነስ ነው። ይህም ወደ "ዶፓሚን ዑደት ብልሽት" ይመራል። በመጨረሻም ስልክዎን አስቀምጠው ወደ ዕለት ተዕለት ተግባርዎ ሲመለሱ ህይወት በሚያስደንቅ ሁኔታ አሰልቺ እና የሚያበሳጭ ሊመስልዎ ይችላል።

      ስልክዎ ዶፓሚንዎን እየጠለፈ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች

  • ጭንቀት፡- ስልክዎ በእጅዎ ወይም በኪስዎ ውስጥ በማይኖርበት ጊዜ እረፍት ማጣት ወይም መደናገጥ ሊያጋጥምዎ ይችላል።
  • የውሸት ንዝረት፡- ስልክዎ በትክክል ሳይነዝር እንደነዘረ ማሰብ።
  • የአንጎል ጭጋግ፡- ለጥቂት ደቂቃዎች እንኳን በመጽሐፍ፣ በውይይት ወይም በስራ ተግባሮች ላይ ማተኮር እጅግ በጣም ከባድ ይሆንብዎታል።
  • የእንቅልፍ መዛባት፡- ለሊት ለሊት ስልክን ከመጠን በላይ በመጠቀም አእምሮዎ ስለሚነቃቃ ለመተኛት ይቸገራል።

      አንጎልዎን እንደገና ለማደስ የሚረዱ መንገዶች

ይህንን ሱስ ለማስተካከል የዶፓሚን ተቀባይዎችዎ እንደገና እንዲስተካከሉ የሚፈቅዱ ድንበሮችን ማበጀት እንጂ ስልክዎን መጣል አያስፈልግዎትም። አራት በጥናት የተደገፉ ስልቶች እነሆ፡-

1. የስክሪን-ጊዜ መከታተያ መሳሪያዎችን ይጠቀሙ:- ብዙዎቹ ዘመናዊ ስልኮች ዕለታዊ አጠቃቀምን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን ስለሚያቀርቡ ማስተካከል የሚያስፈልጋቸውን ልማዶች ለመለየት ይረዳዎታል።

2. ስክሪንዎን ወደ ግራጫ ሚዛን ይቀይሩ፦ ቀለም ትልቁ የዶፓሚን ቀስቃሽ ነው። ደማቅ ቀይ እና ደማቅ ሰማያዊ ቀለሞችን ከስክሪንዎ ማስወገድ እንደ ኢንስታግራም ወይም ቲክቶክ ያሉ መተግበሪያዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ አሰልቺ እንዲመስሉ ያደርጋቸዋል። ይህም ለረጅም ጊዜ ስልክዎን የመጠቀም ፍላጎትዎን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

3. "ከእይታ ውጭ" የሚለውን ህግ ይለማመዱ፦ ስራ በሚሰሩበት ጊዜ ስልክዎ በጠረጴዛዎ ላይ ከሆነ አእምሮዎ ከራሱ ጋር ስልኩን ላለማንሳት በመታገል ብዙ ሃይልን በንቃት ያጠፋል። በሌላ ክፍል፣ መሳቢያ ውስጥ ወይም ቦርሳዎ ውስጥ ያስቀምጡት። ስልክዎን ለማግኘት ከተቀመጡበት መነሳት ካለብዎ ተጨማሪ መሰናክልን በመፍጠር የአእምሮን የልምድ ምልልስ ሰንሰለት ይሰብራሉ።

4. ከቴክ-ነጻ ቀጠናዎችን ይፍጠሩ፦ ስልክ በጥብቅ የተከለከለባቸውን የተወሰኑ ሰዓቶች እና ቦታዎች ይወስኑ። ለምሳሌ:-

  • የእራት ጠረጴዛ፡- ከቤተሰብዎ ጋር በቀጥታ በመገናኘት በህብረት መመገብን ይለማመዱ።
  • መኝታ ቤት፡- ስልክዎን ሙሉ በሙሉ ከመኝታ ክፍሎ ውጪ ያቆዩት። ስልክዎ ማታ ማታ የሚያዩት የመጨረሻው እና ጠዋት ጠዋት የሚነኩት የመጀመሪያው ነገር እንዳይሆን የማንቂያ ሰዓትን ብቻ በመኝታ ቤትዎ ውስጥ ይጠቀሙ።

5. ዲጂታል ሽልማቶችን በእውነተኛ ዓለም ሽልማቶች ይቀይሩ፡- አእምሮዎ በትክክል እንዲሰራ ትክክለኛ ዶፓሚን ያስፈልገዋል። ነገር ግን ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም፣ አጫጭር ቪዲዮዎችን በብዛት በመመልከት ወይም ሱስ የሚያስይዙ የሞባይል ጨዋታዎችን በመጫወት ዝቅተኛ ጥረት እና ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው የዶፓሚን ሽልማቶችን ያስወግዱ። በምትኩ ትንሽ ተጨማሪ ጥረትን በሚጠይቁ እና ዘላቂ እርካታን በሚሰጡ የእውነተኛው ዓለም ተግባራዊ ሽልማቶች ዘላቂ እና ጤናማ ዶፓሚን በመገንባት ላይ ያተኩሩ። ለዚህ ምርጥ አማራጮች የ20 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ምግብ ማብሰል፣ እንደ እደጥበብ ያሉ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችን መማር እና የተዋቀረ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ወይም የዮጋ ክፍለ ጊዜን ማጠናቀቅን ያካትታሉ።

6. ጥንቃቄ የተሞላ የስልክ አጠቃቀምን ይለማመዱ:- ስልክዎን ከመክፈትዎ በፊት እራስዎን "አሁን ምን ለማድረግ እየተጠቀምኩበት ነው?" ብለው ይጠይቁ። ይህ ቀላል ጥያቄ የደመ-ነፍስ ልምዶችን ሊያቋርጥ እና ሆን ብሎ መጠቀምን ሊያበረታታ ይችላል።

ስልክዎ መሳሪያዎ እንጂ አለቃዎ አይደለም። እነዚህን ምክሮች ሞክረው አሁንም ከሱሰኛ የስልክ አጠቃቀም ጭንቀት ወይም ከባድ መዘናጋት ጋር እየታገሉ ከሆነ የህክምና እርዳታን ያግኙ። ትኩረታችን እንዲከፋፈል ለማድረግ በተሰራ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ እርዳታ መፈለግ ምንም የሚያሳፍር ነገር የለውም።

Comments (0)