የወሲብ ፍላጎትዎን እና ብቃትዎን የሚያግዙ 8 ምግቦች
ጤናማና ደስተኛ የወሲብ ሕይወት እንዲኖርዎት የእለት ተእለት አመጋገብዎ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ የወሲብ ፍላጎትዎን ለመጨመር፣ የደም ዝውውርዎን ለማሻሻል፣ የኃይል መጠንዎን እና ብቃትዎን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም አጠቃላይ አካላዊና ስሜታዊ ጤናዎን ለመደገፍ ይረዳዎታል።
በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሙሉ ጥራጥሬዎች (Whole grains) እና አነስተኛ ስብ ባላቸው ፕሮቲኖች (Lean proteins) የበለጸገ የተመጣጠነ አመጋገብ፣ እንደ ሆርሞን መዛባትና የሜታቦሊዝም (የምግብ መፈጨትና ወደ ኃይል የመቀየር ዑደት) እክሎች ያሉ የወሲብ ጤናን የሚያስተጓጉሉ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል።
አጠቃላይ ጤናዎን እያሻሻሉ የወሲብ ሕይወትዎን ስኬታማ ለማድረግ የሚረድዎት 8 ምግቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
1. ሐብሐብ
ሐብሐብ በሰውነታችን ውስጥ ወደ ኤል-አርጂኒን (L-arginine) በሚለወጠው ኤል-ሲትሩሊን (L-citrulline) በተባለ አሚኖ አሲድ የበለጸገ ነው። ኤል-አርጂኒን ደግሞ የደም ሥሮችን ዘና በማድረግ ወደ ብልት የሚሄደውን የደም ፍሰት የሚያሳልጠውን ናይትሪክ ኦክሳይድ (Nitric oxide) ለማምረት ይረዳል። ይህ ተፅዕኖው ሐብሐብ "የተፈጥሮ ቪያግራ" (nature's Viagra) የሚለውን ስያሜ እንዲያገኝ አድርጎታል።
ከዚህም በተጨማሪ በሐብሐብ ውስጥ የሚገኙት አንቲኦክሲዳንቶች (Antioxidants) የሚከተሉትን ጥቅሞች ይሰጣሉ፦
- የወንድ የዘር ፍሬ (Sperm) ጥራትን ያሻሽላሉ
- የዘር ፍሬ ማምረቻ እጢዎች (Testicles) ጤናማ አሰራር እንዲኖራቸው ይደግፋሉ
- በወንዶች ላይ የስንፈተ ወሲብ (የብልት መቆም ችግር) ምልክቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ይረዳሉ
2.የዱባ ፍሬ እና ሌሎች በዚንክ የበለፀጉ ምግቦች
በዚንክ (zinc) የበለፀገ በመሆኑ ወደ መራቢያ አካላት የሚኖረውን የደም ፍሰት ይጨምራል። ዚንክ የቴስቶስትሮን ሆርሞን መመረትንም በመደገፍ እና የዘር ፍሬን ጤናማ በማድረግ በወንዶች የመውለድ ብቃትን ይደግፋል።
የዚንክ እጥረት ለቴስቶስትሮን ሆርሞን መቀነስ አንዱ ምክንያት ነው። የዱባ ፍሬ ደግሞ ከዕፅዋት ከሚገኙ ምርጥ የዚንክ ምንጮች አንዱ ሲሆን 28 ግራም የዱባ ፍሬ በቀን ማግኘት ከሚገባን የዚንክ ፍላጎት ውስጥ 20% ያህሉን በቀላሉ ይሸፍናል።
በተጨማሪም የሚከተሉትን በዚንክ የበለጸጉ ምግቦች በአመጋገብዎ ውስጥ ማካተት ይችላሉ፦
- የባሕር ምግቦች፦ ኦይስተር፣ ሎብስተር እና ክራብ (ሽርጣን)
- የበሬ ሥጋ
- የተቀቀለ ባቄላ
- በዚንክ የተጠናከሩ የቁርስ እህሎች (Cereals)
3. አፕል እና ሌሎች በፍላቮኖይድ የበለፀጉ ፍራፍሬዎች
አፕል በውስጡ የደም ግፊትን ለማስተካከል የሚረዳ ‘ፍላቮኖይድ’ (Flavonoids) የተባለ አንቲኦክሲዳንት ይዟል። ከፍተኛ የደም ግፊት የደም ሥሮችን በመጉዳት ወደ ብልት የሚሄደውን የደም ፍሰት ስለሚያስተጓጉል፣ ለስንፈተ ወሲብ (Sexual dysfunction) መከሰት አንዱ መንስኤ ሊሆን ይችላል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ፍራፍሬዎችን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች ለስንፈተ ወሲብ የመጋለጥ ዕድላቸው በ14% ያህል ይቀንሳል። ይህ ሊሆን የቻለው በፍራፍሬዎቹ ውስጥ በሚገኘው ከፍተኛ የፍላቮኖይድ ይዘት ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። ከዚህም በላይ አፕል ‘ኬርሰቲን’ (Quercetin) በተባለ ሌላ ጠቃሚ ንጥረ ነገር የበለጸገ ሲሆን ይህ ንጥረ ነገር በቀን ከ500 ሚሊግራም በላይ በሚወሰድበት ጊዜ የደም ግፊትን ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።
ከአፕል በተጨማሪ የሚከተሉት ፍራፍሬዎች በፍላቮኖይድ የበለጸጉ በመሆናቸው የወሲብ ሕይወትን ለማነቃቃት ይረዳሉ፦
- እንጆሪ (Strawberries) እና ብሉቤሪ (Blueberries)
- ወይን እና ቼሪ (Cherries)
- እንደ ሎሚ፣ ብርቱካን እና መንደሪን ያሉ ኮምጣጣ ፍራፍሬዎች
4. ቀይ ስር እና ሌሎች በናይትሬት የበለፀጉ ምግቦች
ቀይ ስር በተፈጥሮው ከፍተኛ የናይትሬት (nitrates) መጠን የያዘ ሲሆን ይህ ንጥረ ነገር በሰውነታችን ውስጥ ወደ ናይትሪክ ኦክሳይድ (nitric oxide) ይለወጣል። ናይትሪክ ኦክሳይድ የደም ሥሮችን እንዲዝናኑ እና እንዲሰፉ በማድረግ ሰውነት ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር ያሻሽላል። የደም ዝውውር መሻሻል ደግሞ የወሲብ ስሜትን በማነቃቃት እና የብልት የመቆም አቅምን በማጠናከር የወሲብ ህይወትዎን ይደግፋል።
ከቀይ ሥር በተጨማሪ የሚከተሉት ምግቦች በናይትሬት የበለጸጉ ናቸው፦
- ቆስጣ
- ጀርጂር /ሮኬት/ (Arugula)
- ፌጦ (Garden cress)
- ሰላጣ (Lettuce)
- ሴለሪ (Celery)
- ራዲሽ /ፍጅል / (Radishes)
5. ቀይ ወይን
በመጠኑ ሲወሰድ ቀይ ወይን ለወሲባዊ ተግባር አስፈላጊ የሆነውን የደም ዝውውር የሚያሻሽሉ እንደ ኩዌርሰቲን (quercetin) እና ሬስቬራትሮል (resveratrol) ያሉ ፀረ-ኦክሳይደንቶችን ያቀርባል። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ መጠጣት በስሜት መነሳሳት እና በወሲብ ብቃት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
6. ጥቁር ቸኮሌት (Dark Chocolate)
ጥቁር ቸኮሌት የደም ሥሮች በተሻለ ሁኔታ እንዲሠሩና ወደ ብልት የሚሄደው የደም ፍሰት እንዲሻሻል የሚያደርግ ‘ፍላቮኖይድ’ የተባለ ጠቃሚ የዕፅዋት ውህድን በውስጡ ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ በአንጎል ውስጥ የደስታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ እንደ ሴሮቶኒን (Serotonin) እና ኢንዶርፊን (Endorphins) ያሉ ኬሚካሎች እንዲመነጩ በማድረግ አጠቃላይ የስሜት መነቃቃትን እና የወሲብ ፍላጎትን (Libido) በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል።
7. ለውዝ እና በዚንክ ፣ በአሚኖ አሲድ እና በኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ የዘር ፍሬዎች (Nuts and Seeds)
እነዚህ ምግቦች የወሲብ ጤናን ለመደገፍ ከሚረዱ ምርጥና ጤናማ መክሰሶች (Snacks) መካከል ይመደባሉ። ለውዝ እና የዘር ፍሬዎች በዚንክ (Zinc)፣ በኤል-አርጂኒን (L-arginine) እና በኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ (Omega-3 fatty acids) የበለጸጉ በመሆናቸው የደም ፍሰትን ለማሻሻል፣ የልብ ጤናን ለመደገፍ እና የደም ሥሮች በአግባቡ እንዲሠሩ ለማገዝ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። የብልት መቆም ሂደትም በቀጥታ ከደም ዝውውር ጥራት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ እነዚህ ንጥረ ነገሮች የወሲብ ብቃትን ለማሳደግ በእጅጉ ይረዳሉ።
የወሲብ ሕይወትዎን ለማነቃቃት በአመጋገብዎ ውስጥ ሊያካቷቸው ከሚችሏቸው ምርጥ አማራጮች፦
- ዋልነት (Walnuts)
- አልመንድ (Almonds)
- ፒስታቺዮ (Pistachios)
- ሄዘልነትስ (Hazelnuts)
- ካሼው (Cashews)
- ኦቾሎኒ (Peanuts)
- የሱፍ ፍሬ (Sunflower seeds) እና
- ፒካንስ (Pecans)
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከእነዚህ አማራጫች መካከል ፒስታቺዮን በቀን ከ60–90 ግራም መመገብ የብልት መቆም አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽላል።
ስለሆነም በፋብሪካ ከተዘጋጁ የታሸጉ መክሰሶች ይልቅ በቀን አንድ እፍኝ የተፈጥሮ ለውዝ በመመገብ የልብዎን ጤና እና የወሲብ ሕይወትዎን በአንድ ላይ ይደግፉ።
8. አቮካዶ (Avocados)
አቮካዶ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ የወሲብ እና የስነ-ተዋልዶ ጤናን የሚደግፉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል። ይህ ፍሬ በጤናማ ስቦች (monounsaturated fats)፣ በዚንክ፣ ብቪታሚን ኢ፣ በኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ፣ በፎሌት እና በአንቲኦክሲዳንቶችየበለጸገ በመሆኑ ለሆርሞን ምርት፣ ለመውለድ አቅም (Fertility) እና ለተስተካከለ የደም ዝውውር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ለወንዶች የሚሰጠው ጥቅም
- የቴስቶስትሮን ሆርሞን መመጣጠን
በውስጡ የያዘው ዚንክ ለወንዶች የወሲብ ብቃት እና የመውለድ አቅም አስፈላጊ የሆነው የቴስቶስትሮን ሆርሞን መመረትን ሲደግፍ ጤናማ ስቦቹ ደግሞ የሆርሞኑን መመጣጠን ያግዛሉ።
- የወንድ የዘር ፍሬ (Sperm) ጥራት
በአቮካዶ ውስጥ የሚገኙት አንቲኦክሲዳንቶች፣ ቪታሚን ኢ እና ኦሜጋ-3 የዘር ፍሬን ጥራት፣ እንቅስቃሴ እና ብዛት ለማሻሻል በእጅጉ ይረዳሉ።
ለሴቶች የሚሰጠው ጥቅም
- የስነ-ተዋልዶ ጤና
ጤናማ ስቦቹ እና አንቲኦክሲዳንቶቹ የእንቁላል መለቀቅን (Ovulation) እና የእንቁላል ጥራትን በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋሉ።
- የስሜት ጣሪያ (Orgasm)
አቮካዶ በውስጡ የያዘው ፎሌት በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ለስሜት ጣሪያ (Orgasm) መድረስ ወሳኝ ሚና ያለውን ‘ሂስታሚን’ (Histamine) የተባለ ተፈጥሯዊ ኬሚካል በሰውነት ውስጥ እንዲመነጭ ያግዛል።
- የፅንስ ዕድገት
እነዚህ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች በእርግዝና ወቅት ጤናማና የፅንስ ዕድገትን ይደግፋሉ።


