የቆጮ የጤና ጥቅም

Melat Geatchew
Jul 9, 2026
undefined

የቆጮ የጤና ጥቅም

ቆጮ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በደቡብ ክልል በስፋት የሚመረትና የሚበላ የእንሰት ተክል ተዋጽኦ ነው። ይህ ባህላዊ ምግብ በውስጡ እጅግ አስደናቂ የጤና በረከቶች እና በርካታ የአመጋገብ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ ከጤና ጥቅም በተጨማሪ  ለምግብ ዋስትናም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ነገር ግን ስለ እንሰት ምርቶች እና ቆጮ ጥቅም የተሰሩ ጥናቶች አነስተኛ በመሆናቸው ለጤና ሊያበረክቱት ስለሚችሉት አስተጽኦ በዝርዝር ማወቅ አልተቻለም።  

የእንሰት ምግብነት

በምግብነት የሚታወቁት ሶስቱ የእንሰት ዋና ዋና የምግብ ምርት ዐይነቶች ቆⶐ፥ ቡላና አሚቾ ናቸው። ቆጮ ከእንሰት የሚገኘው ዋናውና በብዛት ለምግብነት የሚውለው ነው።

ቆጮ ምንድን ነው ?

ቆጮ ከእንሰቱ የግንድ ሽፋን ተፍቆ የሚገኘው ውጤት ነው። ጭማቂው በኮባ (የእንሰት ቅጠል) በጉድጓድ እንዲቦካ (fermented) ተጠቅልሎ ይቀመጣል። ቆጮው ቶሎ እንዲብላላ (fermented) አሚቾ ተከታትፎ ይጨመርበታል። ውሃውን በመጭመቅና በውስጡ ተቀላቅሎ የሚገኘውን ቃጫ ለማስወገድ በመክተፍና በማፅዳት ይዘጋጃል። ከጊዜ በኋላ ተቆፍሮ ከተቀበረው ቆጮ እየተቆነጠረ በመውሰድ በተለያየ መንገድ ለምግብነት ተዘጋጅቶ ይቀርባል። ቆጮው እንደ ቂጣ/ዳቦ ፥ ፍርፍር  ፥ እንደ እንጀራ መልክ ተዘጋጅቶ ለምግብነት ይውላል።

ቡላ

ከግንዱ ከተፋቀው ፍሳሽና ከአሚቾ ተቀላቅሎ ለብቻው እንደ ውሃ ኩል ብሎ ወጥቶ፤ ዝቃጩ ተጣርቶ የሚገኘው ንጹህ የእንሰት ዱቄት ቡላ ይባላል። ቡላ ጠቃሚነቱን ለመግልጥ በጉራጌ “የእንሰት ቅቤ” በመባል ይታወቃል። ለምግብነት በሚውልበት ጊዜ በተለያየ መልኩ ተዘጋጅቶ ይቀርባል።  ቡላ በቂጣነት፥ በፍርፍር፥ በገንፎ፥ በአጥሚት መልክ በቅቤ፥ በአይብ፥ በክትፎ  አልያም ብቻውን ተዘጋጅቶ ይበላል። ቡላ ጥሩ ገንቢ ምግብ ነው። ለዚህም ነው በጉራጌ ባህል ለደም ማነስ፤ ለአራስ እናት ወገብ፣ ለጨቅላ ህጻናት ምግብነት እና ክብደትን ለመቆጣጠር ያግዛል በተጨማሪም ትኩስ ቡላ በቅቤ ተሰርቶ ሳል ለማቆም ፥ ፍርፍሩም በቅቤና ሚጥሚጣ ለተቅማጥ ማቆምያ ይረዳል ተብሎ ይታመናል።

አሚቾ  

አሚቾው የእንሰቱ ስር እንደ ዋልታ ሆኖ የሚያቆመው ድንች መሰሉ ክፍል ነው።  ለቆጮ፤ ለቡላና መሰል ምግቦች መሥሪያነት ወይም እርሾነት ያገለግላል። ስሩ በሰሎና ተቆራርጦ እንደ ድንች ይበላል።  ካልስየምና አይረን  (calcium and iron) እንዲሁም አርጂኒን (arginine) የሚባለው አሚኖአሲድ (amino acid) በብዛት ስላለው በአብዛኛው ጊዜ የአጥንት ስብራትና ለወላድ እናት እንክብካቤ እና ተመሳስይ ችግሮችን ለማከም ይረዳል።

አሚቾ ከምግብነቱና (እንደ ድንች) እና መድኃኒትነቱ በተጨማሪ የእንሰት ችግኞችንም የማፍያ/ማራቢያ መንገድ ነው። አሚቾው ሁለት ሶስት ቦታ ተከፍሎ ሲቀበር እስከ 200 መቶ ያህል ችግኞች ይፈላሉ፤ እነዚህ እንደገና ራቅ ራቅ ተደርገው በተደጋጋሚ እንዲተከሉ በማድረግ አዳዲስ እንሰቶች ለማባዛት ያገለግላል ። አሚቾ  ለምግብነትም እንደችግኝ ማፍያም ስለሚውል ተፈላጊነቱን ከፍ ያደርገዋል።

 

በእንሰት ምግቦች ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ንጥረነገሮች

ሰፋ ያለ ሳይንሳዊ ጥናት ቢያስፈልገውም የእንሰት ተክል የተለያዩ ውጤቶች ጥሩ የጉልበት ሰጭ ካርቦሃይድሬት (carbohydrate) ምንጭ ናቸው። ለሰውነታችን በጣም ጠቃሚ የሆኑ መዓድናት (minerals) እንደ  ካልስየም፤ ፖታስየም፥ አይረን፤ ማንጋኒዝ፥ ዚንክ፤ መዳብ  ፎስፎረስ (calcium, potassium, iron, manganese, zinc, copper, phosphorus) ያሉ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ይገኙበታል።  የተላያዩ የፕሮቲን መሰረቶች የሆኑ አሚኖአሲዶች (amino acid)፤ መጠነኛ ቪታሚኖችና (vitamins)፤ በተጨማሪም  ከፍተኛ ፋይበር (fiber) ይገኙበታል። በተጨማሪም ፋይቶኬሚካሎች (phytochemicals) እንደ አልካሎይዶች (alkaloids)፤ ፊኖሎች (phenols)፤ ፍላቪኖይዶች (flavonoids) ወዘተ ያሉ ጠቃሚ ንጥረ ነግሮች ስላላቸው ለጤና በጣም ጠቃሚ ናቸው።

የአመጋገብ ጥቅሞች

  • በካርቦሃይድሬት የበለጸገ: ቆጮ በዋነኝነት የካርቦሃይድሬት ምንጭ በመሆኑ ለሰውነት ጥሩ የኃይል አቅርቦት ይሰጣል።
  • የማዕድን ምንጭ: ከፍተኛ መጠን ያለው ካልሲየም እና ብረት ይዟል፤ እነዚህም ለአጥንት ጤንነት እና ለደም ማነስ መከላከል ጠቃሚ ናቸው።
  • ምግብን ማዋሃድ ያሻሽላል: በእንሰት ላይ የተመሰረቱ ምግቦች (እንደ ቆጮ) ከፍተኛ የፋይበር ይዘት ስላላቸው፣ ጤናማ የምግብ መፈጨትን ያበረታታሉ።
  • የቫይታሚን ምንጭ: ቆጮ ቫይታሚን B2 (ራይቦፍላቪን) እና ሌሎች ጥቃቅን ንጥረ ምግቦችንም ይዟል።
  • ዝቅተኛ ፕሮቲንና ቅባት: ቆጮ ጥሩ የኃይል ምንጭ ቢሆንም፣ በፕሮቲን እና በቅባት ይዘቱ ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ፣ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ከሚሰጡ ሌሎች ምግቦች ጋር ተቀላቅሎ ይበላል።መጠነኛ ፕሮቲን (protein) ስላለው በሰውነት ገንቢነቱ እምብዛም አይታወቅም:: ነገርግን በርካታ አሚኖአሲዶች (amino acids) ይገኙበታል። 

የእንሰት ምርቶች መድኃኒትነት 

የእንሰት አስተዋጽኦዎች ለአጥንትና ተዛማጅ ሁኔታዎች (ስብራት፥ ውልቃት፥ እብጠት፥ ቁርጥማት ወዘተ)፤ ክብደት ለመቀነስ፥ ለደም ማነስ፥ ፤ ለጉበት በሽታ፤ ለጥርስ ህመም፤ ወዘት ጠቀሜታ እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

 

በአሚቾ ውስጥ በብዛት የሚገኙት እንደ ካልሲየም፥ ፖታስየም፥ ብረት፥ መዳብ፥ ዚንክ፥ ማንጋኒዝ፥ ማግኒዚየም፥ ፎስፎረስ ያሉት መዓድናትና  እንደየጠባያቸው የተጠቀሱትን የጤና ችግሮች ለማስወገድ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።  አርጂኒን የሚባለው አሚኖአሲድ በከፍተኛ መጠን አሚቾው ውስጥ ስለሚገኝ ለአጥንትና ጅማት ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

Comments (0)