አፍን መለጠፍ (Mouth taping) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዋወቀ የመጣ ልምድ ሲሆን አፍን መለጠፍ (Mouth taping) ማለት አንድ ሰው በሚተኛበት ጊዜ ለዚህ አገልግሎት የሚሆኑ በአፍ ላይ የሚለጠፉ ፕላስተሮችን አፍ ላይ በማድረግ አፍን ዘግቶ በአፍንጫ መተንፈስን የሚያበረታታ የጤና ዘይቤ ነው።
በአፍ የምንተነፍስበት ምክንያት
በአፍ መተንፈስ በድንገተኛ ወይም በፍርሃት ጊዜ እንደምንተነፍሰው ከላይ ከላይ እንድንተነፍስ የሚያደርገን ሲሆን የምንተነፍሰው አየር በላይኛው የደረታችን ክፍል የሚቀር በመሆኑ በቂ አየር ለማግኘት በፍጥነት እና በተደጋጋሚ እንድንተነፍስ ያደርገናል። በአፍ መተንፈስ አንዳንድ ጊዜ በልማድ የመጣ ቢሆንም የሚከተሉት የጤና እክል በሚኖሩበት ጊዜም በአፍ መተንፈስ ወይም በአፍንጫ አለመተንፈስ ሊከሰት ይችላል።
- የአፍንጫ አለፍጂ (Allergic rhinitis) ወይም ጉንፋን
- የአፍንጫ መካከለኛ ግድግዳ መጣመም (Deviated nasal septum)
- ለረጅም ጊዜ የቆየ የሳይነስ ኢንፌክሽን (Chronic Sinusitis)
- የአፍንጫ ውስጥ እጢ/ፓሊፕ (Nasal Polyp)
- በእንቅልፍ ጊዜ የመተንፈሻ መዘጋት (Obstructive sleep apnea)
እነዚህ ህመሞች በአፍ ከመተንፈስም በተጨማሪ በእንቅልፍ ጊዜ የማንኮራፋትም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
በአፍንጫ የመተንፈስ ጥቅሞች
በአፍንጫ መተንፈስ ከአፍ መተንፈስ የበለጠ ጥቅሞች ያስገኛል። በተፈጥሮ አፍንጫ አየር የሚገባበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ፤ አየር የሚጣራበት ፣ የሚሞቅበት ፣ የሚረጥብበት እና ሳንባ ውስጥ ለመድረሱ በሚገባ የሚዘጋጅበት መንገድ ነው። ስለሆነም በአፍንጫ መተንፈስ የሚከተሉትን ተጨማሪ ጥቅሞች ይሰጣል።
- የደም ግፊትን ይቀንሳል
- የኦክስጅን መጠንን ያሻሽላል
- በአየር ውስጥ የሚገኙ አለርጂዎችን በመያዝ ያጣራል
- የጉሮሮ መድረቅን እና መቆጣትን ይቀንሳል
- የአፍ መድረቅን ያሻሽላል
- የአፍ ጠረንን እና የጥርስ ጤናን ያሻሽላል
- ማንኮራፋትን ያሻሽላል
- የመንጋጋ አጥንት አቀማመጥን ያሻሽላል
ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች መሰረት በአፍንጫ መተንፈስ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በመግለጽ አፍን የመለጠፍ (Mouth taping) ልምድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስፋፋቱ ይታያል። አፍን ለመለጠፍ ልምድ በቂ ሳይንሳዊ ድጋፍ ባይኖረውም አንዳንድ ጥናቶች አፋቸውን በፕላስተሮች ሸፍነው የሚተኙ ሰዎች ላይ የእንቅልፍ መሻሻል እንደታየባቸው እና መለስተኛ የእንቅልፍ ጊዜ የመተንፈሻ መዘጋት (Mild obstructive sleep apnea) ባለባቸው ሰዎች ላይ የኦክስጅን መጠናቸው እንደተሻሻለ ፣ ማንኮራፋታቸው እንደቀነሰ ገልጸዋል። ሆኖም ግን አፍን ለጥፎ መተኛት በጽሁፍ ላይ አሳማኝ ጥቅም ቢኖረውም በተግባር የተሰሩ ጥናቶች ግን ጥቂት ወይም ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አልፎም በአንዳንድ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል አሳይተዋል።
አፍን መለጠፍ የማይመከርባቸው ሁኔታዎች
አፍን በፕላስተር መለጠፍ የማይመከርባቸው ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉትን መግለጽ ይቻላል።
የአፍንጫ መዘጋት ያለባቸው ሰዎች
አፍንጫ በቂ አየር እንዳያስገባ የሚያደርጉ ችግሮች ፤ ለምሳሌ የአፍንጫ ግድግዳ መጣመም ፣ የአፍንጫ ፖሊፕ ወይም ከባድ አለርጂ ባሉባቸው ሰዎች ላይ አፍን መለጠፍ አይመከርም።
- የእንቅልፍ ጊዜ መተንፈሻ መዘጋት (Obstructive sleep Apnea) ያለባቸው ሰዎች
በእንቅልፍ ጊዜ መተንፈስ የሚቋረጥበት ሰው፤ ይህም ከፍተኛ ማንኮራፋት ፣ የመታፈን ስሜት እና የእንቅልፍ መቋረጥ ምልክቶች ያሉበት ሰው የአፍ መለጠፊያን ያለ ሐኪም መመሪያ መጠቀም የለበትም። - በቀላሉ መተንፈስ የማይችሉ ሰዎች
በአፍንጫ በነፃነት መተንፈስ የማይችሉ ሰዎች አፋቸውን መዝጋት አደጋ ሊያመጣ ይችላል። የአፍንጫ መጨናነቅ ወይም የመተንፈሻ ችግር ካለ መጀመሪያ መፍትሄ መፈለግ ይገባል። - የልብ ወይም የሳንባ ከባድ በሽታ ያላቸው ሰዎች
እንደ አስም (Asthma) እና ሲኦፒዲ (COPD) ያሉ ከባድ የመተንፈሻ ህመሞች ያሉባቸው ሰዎች ተጨማሪ የአየር መግቢያ ገደብ ሊያስቸግራቸው ይችላል። የአፍ አካባቢ የቆዳ ችግር ያላቸው ሰዎች
አፍ ላይ የሚለጠፈው ቴፕ የቆዳ መጎዳትን እና መቆጣትን ሊያባብስ ስለሚችል የቆዳ አለርጂ ወይም መቆጣት እና ቁስል ላለባቸው ሰዎች አይመከርም።
አልኮል ወይም የማስተኛ መድሀኒት የወሰዱ ሰዎች
አልኮል እና የእንቅልፍ መድኃኒት የንቃት መጠንን እና አተነፋፈስን የመቆጣጠር አቅምን ስለሚቀንሱ አልኮል ወይም የእንቅልፍ መድኃኒት ተጠቅሞ መተኛት መታፈንን ሊያመጣ ይችላል።
ልጆች
በልጆች የአፍ መተንፈስ ብዙ ጊዜ የአዴኖይድ ወይም የቶንሲል መተለቅ (Adenoid or Tonsillar hypertrophy) እንዲሁም ሌሎች የአፍንጫ ችግሮች ምልክት ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ህፃናት ላይ በአፍ መተንፈስ እንዲሁም ማንኮራፋት ካስተዋሉ ወደ ሃኪም ቤት በመሄድ መታየት ያስፈልጋል።
አፍን ከመለጠፍ ልምድ (Mouth taping)ይልቅ የሚመከሩ አማራጮች
አንዳንዶች በአፍንጫ መተንፈስን ለማበረታት እና ማንኮራፋትን ለመቆጣጠር አፍን መለጠፍ እንደ መፍትሔ ቢጠቀሙበትም አብዛኛዎቹ ጥናቶች ግን ይህን ዘዴ አይደግፉትም። በምትኩ ማንኮራፋትን ለማስቆም እና በአፍንጫ መተንፈስን ለማበረታት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መንገዶች መጠቀም ይመክራሉ።
የአፍንጫ መዘጋትን መታከም
ብዙ ሰዎች በአፈ የሚተነፍሱት አፍንጫቸው ስለሚዘጋ ነው። ስለዚህም ዋናውን ምክንያት ማከም አፍን ከመለጠፍ ልምድ የተሻለ ነው። ይህንንም በሚከትሉት መንገዶች ማድረግ ይቻላል።
- በጉንፋን ምክን ያት አፍንጫ ከተዘጋ ለብ ባለ ውሃ እና ጨው አፍንጫን ማጽዳት
- የአለርጂ ሕክምናን ማግኘት
- የአፍንጫ ፖሊፕ ፣ የአፍንጫ ግድግዳ መጣመም (Deviated septum) እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ካሉ በሐኪም መታየት
በጎን መተኛት
በጀርባ መተኛት ለአንዳንድ ሰዎች ማንኮራፋትንና በአፍ መተንፈስን ሊጨምር ይችላል። ስለሆነም በጎን መተኛት የአየር መግቢያን ክፍት ለማድረግ ስለሚረዳ ማንኮራፋትንም ሊቀንስ ይችላል።
የአፍንጫ ስትሪፕ (Nasal Strip) መጠቀም
የአፍንጫ ስትሪፕ በውጫዊ የአፍንጫ ክፍል የሚለጠፍ ሲሆን የአፍንጫ መተንፈሻ መንገድን በትንሹ ሊያሰፋ ይችላል። የአፍንጫ ስትሪፕ በአፍንጫ በቀላሉ ለመተንፈስ ቢረዳም ከአፍ መከፈትን ግን አይከላከልም።
ጤናማ ክብደትን መጠበቅ
ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት በአንገት አካባቢ ስብ እንዲከማች ስለሚያደርግ የአየር መግቢያን ሊያጠብ ይችላል። ጤናማ ክብደትን መጠበቅ በአፍንጫ መተንፈስን እና የእንቅልፍ ጥራትን ለማሻሻል ይረዳል።
የእንቅልፍ ጊዜ የመተንፈሻ መዘጋትን (Sleep apnea) መመርመር
ከፍተኛ ማንኮራፋት፣ በእንቅልፍ ወቅት መተንፈስ መቋረጥ ፣ በቀን ከፍተኛ ድካም ወይም በጠዋት ራስ ምታት ካለ የእንቅልፍ ጊዜ የመተንፈሻ መዘጋት (Obstructive sleep apnea) ሊኖር ይችላል። በዚህ ሁኔታ አፍን መለጠፍ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ሊያባብሰው ስለሚችል በሐኪም መመርመር እና አስፈላጊውን ሕክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው።
የአፍ መለጠፍ በማህበራዊ ሚዲያ ታዋቂ ቢሆንም፣ ለአብዛኛዎቹ ጤናማ ሰዎች ጥቅሙን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃ ገና ውስን ነው። ከዚህ ይልቅ የአፍንጫ መዘጋትን ማከም፣ የአፍንጫ ስትሪፕ መጠቀም፣ የእንቅልፍ አቀማመጥን ማሻሻል፣ ጤናማ ክብደት መጠበቅ እና አስፈላጊ ከሆነ ለእንቅልፍ አፕኒያ ምርመራ ማድረግ በረጅም ጊዜ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች ናቸው።


