ፖሊሲኢንዶክራይን ሜታቦሊክ ኦቫሪያን ሲንድረም (PMOS)

Melat Geatchew
Jul 15, 2026
undefined

ፖሊሲኢንዶክራይን  ሜታቦሊክ ኦቫሪያን ሲንድረም 

(Polyendocrine Metabolic Ovarian Syndrome (PMOS) )

ፖሊሲኢንዶክራይን  ሜታቦሊክ ኦቫሪያን ሲንድረም ወይንም በቀድሞ ስሙ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪያን ሲንድረም የሚባለው በሴቶች ላይ የሚከሰት በሽታ ሲሆን፤ አንድ ሴት በሰውነቷ ውስጥ ያለው የወንድ ሆርሞን (androgen) መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ የተለያዩ የሰውነት እና ስነ ልቦናዊ ለውጦችን በህመምተኛዋ ላይ ሲያስከትል ነው። ከነዚህ የሰውነት እና ስነ ልቦናዊ ለውጦች ውስጥ ዋንኞቹ

  • የወር አበባ መዛባት
  • የፊት እና የደረት ፀጉር ማብቀል 
  • የጸጉር መሳሳት 
  • ብጉር
  • መካንነት 
  • ከፍተኛ የሰውነት ክብደት መጠን  ሊኖራቸው ይችላል። 
  • እንዲሁም ለ ስኳር በሽታ የተጋለጡ ናቸው።

PMOS በቀላሉ “በኦቭየሪ ላይ የቋጠሩ ነገሮች መኖር” ብቻ አይደለም። ስሙ ምንም እንኳን “Polycystic” ቢልም፣ PCOS ያለባቸው ሁሉም ሴቶች በኦቭየሪያቸው ላይ የተለወጡ ፎሊክሎች አይኖሯቸውም፤ እንዲሁም እነዚህ ትንንሽ ፎሊክሎች በእውነት ሲስት ማለት አይደሉም።

ይህ በሽታ ከ 5 እስከ 10 በመቶ የሚሆን ሴቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን አንዲት ሴት በዚህ በሽታ እንደተጠቃች ለማረጋገጥ የማህፀን አልትራሳውንድ እና የተለያዩ የደም ምርመራዎች ያስፈልጋሉ። ስለዚህም አንዲት ሴት ሶስቱን መስፈርቶች ከሟላች በበሽታው እንደተጠቃች መገመት ይቻላል። እነሱም፦ 

  1. የተዛባ የወር አበባ ዑደት
  2. ከፍተኛ የወንድ ሆርሞን (androgen) መጠን - ይህም ህመምተኞች በሚያሳዩት የተለያዩ ምልክቶች ወይም በላብራቶሪ ምርመራ ሊታወቅ ይችላል። ከምልክቶቹ ውስጥ ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ፀጉር ወይም ራሰ በርኃነት ወይም እንደ ብጉር አይነት ምልክትቶች መጥቀስ ይችላል።
  3. በአልትራሳውንድ ምርመራ የሚታይ በእንቁልጢ ላይ በሽታውን የሚያመለክት ለውጥ ሲኖር ናቸው። 

ፖሊሲኢንዶክራይን  ሜታቦሊክ ኦቫሪያን ሲንድረም ለምን ይከሰታል?

የPMOS ትክክለኛ መንስኤ ሙሉ በሙሉ አይታወቅም። ነገር ግን የ ዘር ወይንም ጄኔቲክ፣ የሆርሞንና የሜታቦሊክ ምክንያቶች ሚና እንዳላቸው ይታሰባል።የዚህ በሽታ ትክክለኛ ምክንያት ባይታወቅም በበሽተኞቹ ላይ የ ሊውትናይዚንግ ሆርሞን (LH)  እና የአንድሮጅን (androgen hormone) መጠን መጨመር ተስተውሏል። ይህም የበሽታውን ምልክቶች እንዲከሰት ምክንያት ሆኖ ተገኝቷል።

1. የኢንሱሊን መቋቋም (Insulin resistance)

በብዙ PMOS ያላቸው ሴቶች የሰውነት ሴሎች ለኢንሱሊን የሚሰጡት ምላሽ ሊቀንስ ይችላል። ሰውነትም ይህንን ለማካካስ ተጨማሪ ኢንሱሊን ሊያመርት ይችላል።

ከፍ ያለ የኢንሱሊን መጠን ኦቭየሪዎች ተጨማሪ አንድሮጅን ሆርሞን እንዲያመርቱ ሊያነሳሳ ይችላል።

2. የአንድሮጅን ሆርሞን መጨመር

አንድሮጅን ብዙ ጊዜ “የወንድ ሆርሞን” ተብሎ ቢጠራም፣ ሴቶችም በትንሽ መጠን ያመርቱታል።

በPMOS የአንድሮጅን መጠን ከፍ ሊል ስለሚችል፣ ኦቭዩሌሽንን ሊያስተጓጉል እና እንደ ብጉር፣ በፊትና በሰውነት ላይ ከመጠን በላይ ፀጉር መብቀል ያሉ ምልክቶችን ሊያመጣ ይችላል።

3. የኦቭዩሌሽን (የእንቁላል መለቀቅ ሂደት)  መዛባት

በPCOS የእንቁላል ማደግና መልቀቅ በመደበኛነት ላይከናወን ይችላል። ይህም የወር አበባ እንዲዛባ እና እርግዝና እንዲዘገይ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ሊሆን ይችላል።

 

የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

ከላይ እንደተገለፀው በሽታው የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ምልክቶቹም የሚጀምሩት ሴቶች ለአቅመ ሔዋን በሚደርሱበት እድሜ ነው።

  • የወር አበባ ዑደት መዛባት አንዳንዴም ወሩን ሊዘል ይችላል
  • የፊት እና የደረት ፀጉር ማብቀል ወይም ራሰ በራነት
  • ብጉር(Acne) የአንድሮጅን መጨመር በተለይ በፊት፣ በደረትና በጀርባ ላይ ብጉር እንዲበዛ ሊያደርግ ይችላል።
  • መካንነት
  • የሰውነት ክብደት መጨመር
  • የፀጉር መሳሳት;  በጭንቅላት ላይ የፀጉር መሳሳት ወይም መውደቅ ሊከሰት ይችላል።
  • የኢንሱሊን ሆርሞን ስለሚያዛባ የስኳር በሽታ ተጋላጭነት
  • የክብደት መጨመር ; አንዳንድ PMOS ያላቸው ሴቶች ክብደት ሊጨምርባቸው ይችላል፣ በተለይም በሆድ አካባቢ። ነገር ግን  ሁሉም PMOS ያለባቸው ሴቶች ከመጠን በላይ ክብደት አይኖራቸውም።

እንዴት ይመረመራል?

PMOS በአንድ የደም ምርመራ ብቻ አይመረመርም። ሐኪምዎ የሕመምተኛዋን የወር አበባ ታሪክ፣ ምልክቶች፣ የሕክምና ታሪክ እና የአካል ምልክቶችን ይገመግማል።

እንደ ሁኔታው የሚከተሉት ሊያዝ ይችላል፦

  • የሆርሞን የደም ምርመራ
  • የደም ስኳር ምርመራ
  • የኮሌስትሮል ምርመራ
  • የደም ግፊት ምርመራ
  • የእንቁልጢ አልትራሳውንድ
  • በተጨማሪም ሌሎች የወር አበባ መዛባት ወይም የአንድሮጅን መጨመር ሊያመጡ የሚችሉ ሌሎች የጤና ሁኔታዎችም መመርመር እና መለየት ሊያስፈልግ ይችላል።

እንዴት ይታከማል?

PCOS አንድ ብቻ የሆነ ሕክምና ያለው በሽታ አይደለም። ሕክምናው በሴቷ ዋና ችግር ላይ ይመሰረታል።

 

የአኗኗር ለውጥ

  • ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ፣ በቂ እንቅልፍ እና ተገቢ የክብደት ቁጥጥር የPCOS ምልክቶችንና የሜታቦሊክ አደጋዎችን ለመቆጣጠር ሊረዱ ይችላሉ።
  • የሰውነት ክብደት መቀነስ ከመጠን በላይ ክብደት ላላቸው ሴቶች መጠነኛ የክብደት መቀነስ እንኳን የወር አበባን መደበኛነትና የእንቁላል መለቀቅን ለማሻሻል ሊረዳ ይችላል።

መድኃኒት

እንደ ምልክቱ እና የግለሰቧ ፍላጎት ሐኪምዎ የወር አበባን ለመቆጣጠር፣ የአንድሮጅን ምልክቶችን ለመቀነስ፣ የኢንሱሊን መቋቋምን ለመቆጣጠር ወይም እርግዝናን እንዲፈጠር የተለያዩ መድኃኒቶችን ሊመክር ይችላል።

  • የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል - ኤስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን የሚባሉ ሆርሞኖችን የያዘ ሲሆን በዚህ በሽታ ለሚሰቃዩ ህመምተኞት በዋነኝነት ይታዘዛል። ይህም የወር አበባ እንዲስተካከል ከማድረግ ባሻገር በሰውነት ላይ በብዛት የሚወጣ ፀጉርን እና ብጉርን ይከላከላል። ነገር ግን ይህ እንክብል እንደ ክብደት መጨመር እና የደም መርጋት የመሳሰሉትን የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል።
  • ፕሮጀስትሮን - ይህ መድኃኒት በየወሩ ለጥቂት ቀናት ብቻ የሚወሰድ ሲሆን የወር አበባ እንዲስተካከል ቢያደርግም እንደ ብጉር እና የሰውነት ፀጉር ያሉ ምልክቶችን ለማስወገድ አያገለግልም። 
  • የአንድሮጅን ሆርሞንን ለመቀነስ የሚሰጡ መድኃኒቶች - ለምሳሌ እንደ ስፕሪኖላክቶን (spironolactone) ያሉ መድኃኒቶች ይጠቀሳሉ።
  • መካንነትን ማከም - ክሎሚፊን (Clomiphene)

Comments (0)