በክረምት ወቅት እንዴት ጤናማ ሆኖ መቆየት ይቻላል?
በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እና ከፍተኛ እርጥበት የሚታወቀው ዝናባማ ወቅት ቫይረሶች፣ ባክቴሪያዎች እና ፈንገሶች በቀላሉ እንዲሰራጩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በዚህም ምክንያት ጉንፋን፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን፣ የሆድ ህመም እና የቆዳ ችግሮች በብዛት ሊከሰቱ ይችላሉ። ነገር ግን ጥቂት ጤናማ ልማዶችን በመከተል እራስዎን እና ቤተሰብዎን መጠበቅ ይችላሉ።
1. እጅዎን በየጊዜው ይታጠቡ
- ምግብ ከመመገብዎ በፊት፣ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ፣ እንዲሁም ከውጪ ወደ ቤት ሲመለሱ እጅዎን በሳሙና እና በውሃ በአግባቡ ይታጠቡ።
- ከቤት ውጪም እንደ ገንዘብ ያሉ ባእድ ነገሮችን ከነኩ በኋላ እጅዎን በእጅ ማጽጃ አልኮል/ሳኒታይዘር ያጽዱ።
2. ጤናማ ምግብ ይመገቡ
- ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ ሙሉ እህሎችን እና ፕሮቲኖችን በመመገብ በሽታ የመከላከል አቅምዎን ያጠናክሩ
- የስኳር መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ መጠጦችን እና በፋብሪካ የተዘጋጁ ምግቦችን ይቀንሱ
3. በቂ ፈሳሽ ይውሰዱ
- በቂ ንጹህ ውሃን ይጠጡ እንዲሁም
- ሞቅ ያሉ መጠጦች እና ሾርባዎችም ሰውነትዎ በቂ ፈሳሽ እንዲኖረው ይረዳሉ።
4. የሰውነትዎን ሙቀት ይጠብቁ
- አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሞቅ ያለ ልብስ እና ውሃ የማያስገቡ ጫማዎችን ያድርጉ እንዲሁም
- ዝናብ ከመታዎ፣ በተቻለ ፍጥነት ደረቅ ልብስን ይቀይሩ።
5. በቂ እንቅልፍ ይተኙ
- በየምሽቱ ከ7 እስከ 9 ሰዓታት ለመተኛት ይሞክሩ
6. ኢንፌክሽኖችን ይከላከሉ
- ሲያስሉ ወይም ሲያስነጥሱ አፍዎን እና አፍንጫዎን ይሸፍኑ
- የቤት ውስጥ ክፍሎች በቂ አየር እንዲያገኙ ያድርጉ እንዲሁም
- በተቻልዎ መጠን በተላላፊ በሽታዎች ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚኖር የቅርብ ግንኙነትን ይቀንሱ።
7. ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ እና መጠጥ ይጠቀሙ
- የአንጀት ኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ለመቀነስ ንጹህ ውሃ ይጠጡ
- ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን በደንብ ይጠቡ
- ምግብን በደንብ ያብስሉ እና
- የተረፈ ምግብን በአግባቡ ያስቀምጡ
8. ወባ ትንኝን ይከላከሉ
- በቤትዎ አካባቢ የተጠራቀመ ውሃ ያስወግዱ
- ነፍሳትን የሚከላከሉ ቅባቶችን ይጠቀሙ እና
- በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች በአጎበር ስር ይተኙ።
9. ወቅቱን ጠብቀው ክትባቶችን ይውሰዱ
- ስለ ኢንፍሉዌንዛ ክትባት እና ለእድሜዎ እና ለጤና ሁኔታዎ ተስማሚ የሆኑ ሌሎች ክትባቶችን በተመለከተ ከጤና ባለሙያ ጋር ይማከሩ።
10. የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ያድርጉ
- በቤት ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ንቁ ሆነው ይቆዩ
የህክምና እርዳታ መቼ ያስፈልጋል?
ከሁለት ወይም ከሶስት ቀናት በላይ የሚቆይ ትኩሳት፣ የመተንፈስ ችግር፣ የማያቋርጥ ማስታወክ ወይም ተቅማጥ፣ የሰውነት ፈሳሽ ማጣት ምልክቶች ወይም ሁኔታዎ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ከሄደ የጤና ባለሙያዎችን ያማክሩ።
በጥሩ የእጅ ንፅህና፣ በጤናማ አመጋገብ፣ በቂ ፈሳሽን በመውሰድ፣ በቂ እንቅልፍን በማግኘት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ በዝናባማው ወቅት ጤናማ ሆነው መቆየት ይችላሉ።


