የእጅና የእግር መደንዘዝ (Numbness) ምንን ያመለክታል?

Betelhem Kenea
Jul 22, 2026
undefined

አንዳንድ ጊዜ እግራችን ወይም እጃችን ሲደነዝዝ አስተውለን ይሆናል። ይህም የመደንዘዝ ሁኔታ በእግራችን ወይንም በእጃችን ምንም ስሜት ካለመሰማት አልፎ አንዳንዴም ማቃጠል (Burning sensation) ፣ መቆጥቆጥ (Tingling) ወይም ጉንዳን እንደሚሄድብን አይነት ስሜት (Formication) ተሰምቶን ይሆናል። ይህም የመደንዘዝ ስሜት አብዛኛውን ጊዜ እጃችንን ፣ ጣታችንን ፣ ክንዳችንን ወይም የታችኛው የእግራችን ክፍልን የሚያጠቃ ቢሆንም፣ በማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ሊከሰት ይችላል። 

ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የሚቆይ የመደንዘዝ ስሜት አሳሳቢ ላይሆን ይችላል።ይህም የሆነበት ምክንያት የእግር መደንዘዝ ለምሳሉእ ለረጅም ጊዜ እግርዎትን አጣምረው ከቆዩ ወይም በእጅዎት ተደግፈው ከተኙ ወደ እግርዎ ወይም እጅዎ የሚሄደውን ነርቭ በጊዜያዊነት ስለሚጫኑት የሚፈጠር ስሜት በመሆኑ ነው። ነገር ግን ተደጋጋሚ ወይም የማይጠፋ መደንዘዝ ካለ የህክምና ምርመራ የሚፈልግ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። 

የመደንዘዝ ስሜትን የሚያመጡ ዋና ዋና መንስኤዎች 

  1. በነርቭ ላይ ጊዜያዊ ጫና 

ይህ ሁኔታ ከላይ እንደተገለጸው አብዛኛዎቻችን አልፎ አልፎ የሚያጋጥመን ስሜት ሲሆን ይህም በነርቭ ላይ ጊዜያዊ ጫና ስለሚፈጠር የመደንዘዝ ስሜት ይፈጠራል። ስለዚህም የነርቭ ጫናው ሲወገድ ፤ ያጣመርነውን እግር እንዘረጋው ወይም የተደገፍንበትን እጅ ስንለቅ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ስሜቱም ወደ መደበኛው ይመለሳል። 

     2.የደም ዝውውር ችግር 

ወደ እጅና እግር የሚደርሰው የደም ፍሰት ሲቀንስ ነፍቮች በቂ ኦክሲጅንና ንጥረ ነገር ማግኘት አይችሉም። ይህም መደንዘዝ ፣ መቆጥቆጥ ወይም ጉንዳን የሚሄድብን አይነት ስሜት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። የደም ዝውውር ችግር በሚፈጠሩትን ምክን ያቶች ሊከሰት ይችላል። 

  • የደም ቧንቧዎች መጥበብ በሽታ (Peripheral Arterial Disease): በተለያዩ ምክንያቶች በደም ቧንቧዎች ውስጥ ስብ ሲከማች የደም ቧንቧዎች የመጥበብ እና የመደንዘዝ ስሜት ያመጣል።
  • የስኳር በሽታ (Diabetes): ከፍተኛ የደም ግፊት እና ኮሎስቴሮል ፤ እነዚህ ህመሞች በጊዜ ሂደት የደም ቧንቧዎችን በመጉዳት ወይም በማጥበብ  የደም ዝውውር እንዲቀንስ ያደርጋሉ። 
  • ሲጋራ ማጨስ(Smoking): በሲጋራ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች የደም ቧንቧዎችን በመጉዳት እንዲሁም በማጥበብ የደም ፍሰትን ይቀንሳሉ። 
  • የደም መርጋት (Blood clots)

የደም ዝውውር መቀነስ ከመደንዘዝ በተጨማሪ የእጅ እና የእግር መቀስቀስ ፣ ቀለም መቀየር ፣ ከመራመድ በኋላ ቁርጥማት (Claudication) ወይም ድካም (Weakness) ሊኖር ይችላል። እነዚህ ምልክቶች በተደጋጋሚ ከታዩ ወይም እየባሱ ከሄዱ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ይመከራል።

     3.የካርፓል ታነል ሲንድሮም (Carpal Tunnel Syndrome)

ይህ ችግር በእጅ አንጓ አካባቢ ያለው መካከለኛ ነርቭ (Median Nerve) ሲጫን ይከሰታል። በተለይ ኮምፒውተር ብዙ ሰዓት የሚጠቀሙ፣ ተደጋጋሚ የእጅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወይም የእጅ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ላይ በብዛት ይታያል። በመጀመሪያ የአውራ ጣት፣ የጠቋሚ ጣት እና የመካከለኛ ጣት መደንዘዝ ይጀምራል፤ በተለይም በሌሊት ምልክቶቹ ሊባባሱ ይችላሉ። ሕክምና ካልተደረገ የእጅ ጥንካሬ ሊቀንስ ይችላል።

     4. የነርቭ በሽታዎች

አንዳንድ የነርቭ ሕመሞችም እጅና እግር መደንዘዝን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል ማልቲፕል ስክለሮሲስ (Multiple Sclerosis)፣ ፔሪፈራል ኒውሮፓቲ (Peripheral Neuropathy) እና አንዳንድ የቫይረስ ወይም የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች ይገኙበታል። እነዚህ ሕመሞች መደንዘዝን ከጡንቻ ድክመት፣ ከመጓዝ ችግር ወይም ከሌሎች የነርቭ ምልክቶች ጋር አብረው ሊያሳዩ ይችላሉ።

      5.የስኳር በሽታ  (Diabetes Mellitus) 

ረጅም ጊዜ ያለተቆጣጠሩት የደም ስኳር መጠን ነርቮችን በቀስታ እየጎዳ ይመጣል። በመጀመሪያ ችግሩ በእግር ጣቶች መደንዘዝ ወይም መቆጥቆጥ በሚመስል ስሜት ሊጀምር ይችላል ። ከጊዜ በኋላ ግን በተለይ ማታ ማታ የሚብስ የእግር ማቃጠል እና የመራመድ ችግርን ሊያስከስት ይችላል። 

      6.የቫይታሚን ቢ 12 እጥረት

ቫይታሚን ቢ12 (Vitamin B12) የነርቭ ጤናን ለመጠበቅ አስፈላጊ ቫይታሚን ነው። የዚህ ቫይታሚን እጥረት ሲከሰት እጅና እግር መደንዘዝ፣ የመራመድ ችግር ፣ በቀላሉ መድከም፣ የማስታወስ ችግር እና የደም ማነስ ሊታዩ ይችላሉ። በተለይ ይህ እጥረት ረጅም ጊዜ ካልታከመ ቋሚ የነርቭ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

       7. እስትሮክ (Stroke)

እስትሮክ ወይም የአንጎል ውስት ደም መቋረጥ አስቸኳይ የሕክምና ሁኔታ ሲሆን ፈጣን ሕክምና ማግኘት ሕይወትን ሊያድን ይችላል። መደንዘዝ ድንገት ከጀመረ እና ከአንድ ወገን የእጅ ወይም የእግር ድክመት፣ የፊት መዛባት፣ የመናገር ችግር፣ የእይታ መቀነስ፣ ከባድ የራስ ምታት ወይም የመራመድ ችግር ጋር ከተያያዘ ወዲያውኑ ወደ አቅራቢያዎ የጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።

        8.የአንገት ወይም የወገብ ዲስክ ችግር 

በአከርካሪ አጥንቶች መካከል የሚገኘው ዲስክ ሲወጣ ወይም ነርቭን ሲጫን የአንገት ወይም የወገብ ዲስክ ችግር ይከሰታል። ይህም ከወገብ ወደ እግር የሚወርድ ህመም፣ የእግር መደንዘዝ፣ የመቆጥቆጥ ስሜት እና የጡንቻ ድክመት ሊያስከትል ይችላል። አንገት ላይ ያለ ዲስክ ችግር ደግሞ በትከሻ፣ በክንድ እና በእጅ ላይ መደንዘዝ ወይም ድክመት ሊያስከትል ይችላል።

መደንዘዝ መቼ አሳስቢ ይሆናል?

የእጅ ወይም የእግር መደንዘዙ ከ24 ሰዓት በላይ ከቆየ፣ በተደጋጋሚ የሚመለስ ከሆነ፣ ከጡንቻ ስንፈት ወይም ከመራመድ ችግር ጋር ከተያያዘ ከሆነ፣ ወይም የሽንትና የሰገራ አለመቆጣጠር ከተከሰተ በአፋጣኝ የህክምና ምርመራ ማድረግ ይኖርብዎታል። በተጨማሪም መደንዘዙ ከከባድ የአንገት ወይም የጀርባ ህመም ጋር ከተያያዘ ወይም ድንገተኛ የፊት መደንዘዝ ካለ ወዲያውኑ ሐኪም ማማከር ይገባል።

ራስዎን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይችላሉ?

የእጅና የእግር መደንዘዝን ለመቀነስ የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ።

  • ረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ ከመቀመጥ ይቆጠቡ
  • በየ30 እስከ 60 ደቂቃው ተነስተው ትንሽ ይንቀሳቀሱ 
  • የስኳር በሽታ ካለብዎ የደም ስኳርዎን በጥሩ ሁኔታ ይቆጣጠሩ
  • በቫይታሚን B12 የበለጸጉ ምግቦችን ዘወትር ይመገቡ 
  • ሲጋራ ማጨስን ያቁሙ 
  • መደበኛ የአካል እንቅስቃሴን ያድርጉ

Comments (0)