የቆዳዬን አይነት እንዴት ማወቅ እችላለሁ(How can I know my skin type)

Christina Zewdu
Jul 29, 2026
undefined

የቆዳዎን አይነት እንዴት ማወቅ ይችላሉ?

ቆዳ ምንድን ነው?

ቆዳ የሰውነታችን ትልቁ አካል ሲሆን፣ መላውን የሰውነት ውጫዊ ክፍል ይሸፍናል። ሰውነታችንን ከጉዳት፣ ከጀርሞች፣ ከኬሚካሎች፣ ከፀሐይ ጨረር (UV) ይጠብቃል። በተጨማሪም የሰውነትን ሙቀት ይቆጣጠራል፣ እንዲሁም ለቫይታሚን D መመረት አስፈላጊ ሚና ይጫወታል።

የቆዳ አይነቶች (Types of Skin)

በቆዳ ሕክምና (Dermatology) መሠረት፣ የቆዳ አይነት የሚወሰነው ቆዳው በሚያመነጨው የተፈጥሮ ዘይት (Sebum) መጠን፣ በቆዳው እርጥበት ደረጃ እና ለአካባቢያዊ ተጽዕኖዎች በሚሰጠው ምላሽ መሠረት ነው።

በቆዳ ሕክምና መጻሕፍትና በተለመደው ክሊኒካዊ አጠቃቀም መሠረት፣ ቆዳ በአምስት ዋና ዋና አይነቶች ይመደባል።

  1. መደበኛ ቆዳ (Normal Skin)
  2. ደረቅ ቆዳ (Dry Skin)
  3. ወዛማ ቆዳ (Oily Skin)
  4. ድብልቅ ቆዳ (Combination Skin)
  5. ስሜታዊ ቆዳ (Sensitive Skin)

1. መደበኛ ቆዳ (Normal Skin)

መደበኛ ቆዳ ተመጣጣኝ መጠን ያለው የተፈጥሮ ዘይት  እና እርጥበት የያዘ የቆዳ አይነት ነው። ከመጠን በላይ ወዛም

 ሆነ ደረቅ አይደለም፣ እንዲሁም የቆዳው መከላከያ (Skin Barrier) በተገቢው ሁኔታ ይሠራል።

ባህሪያቱ

• ለስላሳ እና ጤናማ የሆነ ቆዳ

• ትንንሽ የቆዳ ቀዳዳዎች (Pores)

• ብጉር በጣም ጥቂት ወይም ፈጽሞ የለም

2. ደረቅ ቆዳ (Dry Skin)

ደረቅ ቆዳ  ማለት የቆዳው ውጫዊ ሽፋን (Stratum Corneum) በቂ እርጥበትና የተፈጥሮ ቅባት (Lipids) በማጣቱ ምክንያት የሚከሰት የቆዳ ሁኔታ ነው።

ባህሪያቱ

• ቆዳው ደረቅና ሻካራ ይሆናል የቆዳ መፋቅ (Flaking/Scaling) ሊታይ ይችላል።

• የቆዳ  መጎተት (Tightness) ስሜት ሊሰማ ይችላል።

• ማሳከክ (Itching) ሊኖር ይችላል።

• በከባድ ሁኔታ ቆዳው ሊሰነጠቅ እና ደም ሊፈስ ይችላል።

3. ወዛማ ቆዳ (Oily Skin)

ወዛማ ቆዳ (Oily Skin ) ማለት የሴባሲየስ እጢዎች (Sebaceous glands) ከመጠን በላይ የተፈጥሮ ዘይት (Sebum) የሚያመነጩበት የቆዳ ሁኔታ ነው። በዚህ ሁኔታ ቆዳው የሚያብረቀርቅ ሊሆን፣ የቆዳ ቀዳዳዎች (Pores) ሊሰፉ እና ለብጉር (Acne) መፈጠር የተጋለጠ ሊሆን ይችላል።

ባህሪያቱ

• ቆዳው በቀላሉ የሚያብረቀርቅ ይሆናል።

• የቆዳ ቀዳዳዎች (Pores) ሰፋ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ።

• ብጉር (Acne) እና ጥቁር ነጠብጣቦች (Blackheads) የመፈጠር እድሉ ሊጨምር ይችላል።

• የቆዳ ሜካፕ (Makeup) ወይም ሌሎች የቆዳ ምርቶች በቀላሉ ሊለወጡ ወይም ሊበላሹ ይችላሉ።

4. ድብልቅ ቆዳ (Combination Skin)

ድብልቅ ቆዳ (Combination Skin) ማለት በተለያዩ የፊት ክፍሎች የተለያየ የቆዳ ባህሪ የሚታይበት የቆዳ አይነት ነው። በአብዛኛው የፊት መሃል ክፍል (T-zone—ግንባር፣ አፍንጫ እና አገጭ) ዘይታማ ሲሆን፣ የጉንጭ ክፍሎች ግን መደበኛ ወይም ደረቅ ሊሆኑ ይችላሉ።

ባህሪያቱ

• የT-zone ክፍል (ግንባር፣ አፍንጫ እና አገጭ) ወዛማ መሆን።

• የጉንጭ ክፍሎች ደረቅ ወይም መደበኛ መሆን።

• በአንዳንድ የፊት ክፍሎች የቆዳ ቀዳዳዎች (Pores) ሰፋ ሊሉ ይችላሉ።

• በወዛማ ክፍሎች ብጉር (Acne) የመፈጠር እድል ሊጨምር ይችላል።

• የቆዳ እርጥበትና የተፈጥሮ ዘይት ሚዛን በተለያዩ የፊት ክፍሎች ሊለያይ ይችላል።

5. ስሜታዊ ቆዳ (Sensitive Skin)

ስሜታዊ ቆዳ  ማለት ለውጫዊ ወይም ውስጣዊ ተጽዕኖዎች በቀላሉ ምላሽ የሚሰጥ የቆዳ ሁኔታ ሲሆን፣ እንደ ማቃጠል ወይም  ማሳከክ ያሉ የማይመቹ ስሜቶችን ሊያስከትል ይችላል።

ባህሪያቱ

• አዲስ የቆዳ ምርቶችን ሲጠቀሙ የማቃጠል ስሜት ሊሰማ ይችላል።

• ቆዳው በቀላሉ መቅላት (Redness) ሊያሳይ ይችላል።

• ማሳከክ ወይም የመጎተት ስሜት ሊኖር ይችላል።

• ለአየር ሁኔታ፣ ለፀሐይ ጨረር እና ለኬሚካሎች በቀላሉ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።

የቆዳዎን አይነት ለማወቅ የሚረዱ መንገዶች

1. የመታጠቢያ ምርመራ (Bare Face / Wash Test)

ይህ የቆዳ ዓይነትን ለመለየት በቆዳ ሐኪሞች በተለምዶ የሚመከር ቀላል ዘዴ ነው።

እንዴት ይደረጋል?

  • ፊትዎን በለስላሳ ማጽጃ (Gentle Cleanser) ይታጠቡ።
  • ፊትዎን በንጹህ እና ደረቅ ፎጣ በቀስታ ያድርቁ።
  • ምንም ዓይነት ክሬም፣ ሎሽን፣ ሴረም ወይም ዘይት ሳይቀቡ ለ30–60 ደቂቃ ይጠብቁ።
  • ከዚያ በኋላ ቆዳዎን በመመልከት እና የሚሰማዎትን ስሜት በመገምገም የቆዳዎን ዓይነት መለየት ይችላሉ።

ውጤቱን እንዴት ይተረጉሙ?

  • ቆዳው ሚዛናዊ፣ ለስላሳ እና ምቹ ከሆነ → መደበኛ ቆዳ
  • ቆዳው የተጎተተ ወይም ደረቅ ከሆነ → ደረቅ ቆዳ
  • ፊቱ በሙሉ ወዛማ  እና የሚያብረቀርቅ ከሆነ → ወዛማ ቆዳ
  • የፊት መሃል ክፍል (T-Zone፦ ግንባር፣ አፍንጫ እና አገጭ) ብቻ ወዛማ ከሆነ → ድብልቅ ቆዳ
  • ቆዳው መቅላት፣ ማሳከክ ካሳየ → ስሜታዊ ቆዳ ሊሆን ይችላል።

2. የቲሹ ወረቀት/የዘይት መለኪያ ወረቀት ምርመራ (Blotting Paper Test)

ይህ ዘዴ የቆዳውን የተፈጥሮ ዘይት መጠን ለመገምገም በቆዳ ሐኪሞች እና በውበት ባለሙያዎች በተለምዶ የሚጠቀሙበት ቀላል ዘዴ ነው።

እንዴት ይደረጋል?

  • ንጹህ የቲሹ ወረቀት ወይም የዘይት መለኪያ ወረቀት (Blotting Paper) ይዘጋጁ።
  • ወረቀቱን በግንባር፣ በአፍንጫ፣ በጉንጭ እና በአገጭ ላይ በቀስታ ይጫኑ።
  • ከዚያ በኋላ በወረቀቱ ላይ የታየውን የዘይት መጠን ይመልከቱ።

ውጤቱን እንዴት ይተረጉሙ?

  • ምንም ወዝ ካልታየ → ደረቅ ቆዳ ሊሆን ይችላል።
  • በሁሉም የፊት ክፍሎች ብዙ ወዝ ከታየ → ወዛማ ቆዳ ሊሆን ይችላል።
  • በT-Zone (ግንባር፣ አፍንጫ እና አገጭ) ብቻ ወዝ ከታየ → ድብልቅ ቆዳ ሊሆን ይችላል።
  • በወረቀቱ ላይ በጣም ትንሽ ወዝ ከታየ እና ቆዳው ምቹ ከሆነ → መደበኛ ቆዳ ሊሆን ይችላል።

3. የቀን ውስጥ ምልከታ (Daily Observation)

ይህ ዘዴ በቀን ውስጥ ቆዳዎ እንዴት እንደሚለዋወጥ በመመልከት የቆዳዎን ዓይነት ለመገምገም ይረዳል።

ውጤቱን እንዴት ይተረጉሙ?

  • ቆዳው ቀኑን ሙሉ የሚደርቅ ከሆነ → ደረቅ ቆዳ
  • ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ፊቱ በሙሉ የሚያብረቀርቅ ከሆነ →ወዛማ ቆዳ
  • የፊት መሃል ክፍል (T-Zone) ብቻ የሚያብረቀርቅ ከሆነ → ድብልቅ ቆዳ
  • ቆዳው ቀኑን ሙሉ ሚዛናዊ፣ ለስላሳ እና ምቹ ከሆነ → መደበኛ ቆዳ

4. የቆዳ ቀዳዳዎችን (Pores) መመልከት

ጥሩ ብርሃን ባለበት ቦታ በመስታወት ፊት ቆመው የቆዳ ቀዳዳዎችዎን ይመልከቱ።

ውጤቱን እንዴት ይተረጉሙ?

  • በሁሉም የፊት ክፍሎች ትልልቅ የቆዳ ቀዳዳዎች ከታዩ → ወዛማ ቆዳ
  • በT-Zone (ግንባር፣ አፍንጫ እና አገጭ) ብቻ ትልልቅ የቆዳ ቀዳዳዎች ከታዩ → ድብልቅ ቆዳ
  • የቆዳ ቀዳዳዎቹ ትንንሽ ወይም ብዙም የማይታዩ ከሆኑ → መደበኛ ወይም ደረቅ ቆዳ

5. ቆዳዎ ለምርቶች የሚሰጠውን ምላሽ መመልከት

አዲስ የቆዳ እንክብካቤ ምርት ሲጠቀሙ ቆዳዎ የሚያሳየውን ምላሽ ይመልከቱ።

ውጤቱ

  • በቀላሉ መቅላት፣ ማሳከክ፣ ወይም ማቃጠል ከታየ → ስሜታዊ ቆዳ ሊኖርዎት ይችላል።

ማስታወሻ

ስሜታዊ ቆዳ በራሱ የተለየ የቆዳ ዓይነት ሳይሆን፣ ከመደበኛ፣ ከደረቅ፣ ወዛማ ወይም ከድብልቅ ቆዳ ጋር አብሮ ሊኖር የሚችል የቆዳ ሁኔታ ነው። ስለዚህ መደበኛ፣ ደረቅ፣ ወዛማ ወይም ድብልቅ ቆዳ ያለው ሰው ስሜታዊ ቆዳም ሊኖረው ይችላል።

6. በቆዳ ሐኪም ምርመራ (Professional Skin Assessment)

ይህ የቆዳዎን አይነት እና ጤንነት ለመገምገም በጣም ትክክለኛው ዘዴ ነው። የቆዳ ሐኪም (Dermatologist) ወይም የቆዳ እንክብካቤ ባለሙያ (Skin Care Professional) የሚከተሉትን ይገመግማል፦

ሀ.የቆዳ እርጥበት (Skin Hydration)

በቆዳው የውጭ ሽፋን ውስጥ ያለውን የውሃ መጠን ማለት ነው። በቂ እርጥበት ያለው ቆዳ ለስላሳ ይሆናል። በሌላ በኩል፣ እርጥበት የጎደለው ቆዳ የተወጠረ ስሜት ሊኖረው ይችላል።

ለ. የቆዳ ዘይት መጠን (Sebum Production)

በሴባሽየስ (Sebaceous) እጢዎች የሚመረተው የቆዳ ዘይት (Sebum) መጠን ይገመግማል። ይህም ቆዳው ወዛማ፣ ደረቅ ወይም ድብልቅ (Combination) መሆኑን ለመወሰን ይረዳል።

ሐ. የቆዳ መከላከያ (Skin Barrier Function)

የቆዳው ውሃን የመጠበቅ፣ ጀርሞችን፣ አለርጂ አምጪ ንጥረ ነገሮችን (Allergens) እና ጎጂ ኬሚካሎችን የመከላከል ችሎታ ይገመግማል። የቆዳ መከላከያው ሲጎዳ ደረቅነት፣ መቅላት፣ መነካካት (Irritation) እና ብግነት (Inflammation) ሊከሰቱ ይችላሉ።

መ. የቆዳ ስሜታዊነት (Skin Sensitivity)

ቆዳው ለመዋቢያ ምርቶች (Cosmetics)፣ ለሙቀት፣ ለብርድ ወይም ለሌሎች አካባቢያዊ ሁኔታዎች በቀላሉ ምላሽ ይሰጣል ወይስ አይሰጥም የሚለው ይገመግማል።

ሠ. የፀሐይ ጉዳት (Sun Damage)

በአልትራቫዮሌት (UV) ጨረር ምክንያት የተፈጠሩ እንደ የቆዳ ቀለም መቀየር፣ መጨማደድ፣ የእድሜ ምልክቶች እና የፀሐይ ነጠብጣቦች መኖራቸው ይገመግማል።

ረ. ሌሎች የቆዳ ችግሮች (Other Skin Conditions)

እንደ ብጉር (Acne)፣ ኤክዚማ (Eczema)፣ ሮሴሺያ (Rosacea)፣ የቆዳ ኢንፌክሽኖች፣ የቆዳ ቀለም መቀየር (Hyperpigmentation/Hypopigmentation) እና ሌሎች የቆዳ በሽታዎች ወይም ችግሮች ይመረምራሉ።

 

 

 

Comments (0)