የወንዶች ማረጥ እና የቴስቴስትሮን ሆርሞን መቀነስ
“የወንዶች ማረጥ” ወይም አንድሮፓውዝ/ማኖፓውዝ በዕድሜ መጨመር የቴስቶስትሮን ሆርሞን መጠን ቀስ በቀስ መቀነሱን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ቴስቴስትሮን በዋነኝነት በወንዶች ውስጥ የሚገኝ ጾታዊ ሆርሞን ሲሆን በወንዶች የጾታዊ ፍላጎት፣ በጡንቻ ጥንካሬ፣ በአጥንት ጤና፣ በቀይ የደም ሕዋስ ምርት እና በስሜት ላይ ጉልህ ሚና ያለው ሆርሞን ነው። ቴስቶስትሮን ሆርሞን በሴቶች ውስጥም ሲኖር ግን መጠኑ ከወንዶች በጣም ያነሰ ነው። ከሴቶች ማረጥ በተለየ መልኩ የወንዶች ማረጥ በአንድ ጊዜ የሚከሰት ሳይሆን በቀስታ የሚከሰት ነው።
የቴስቴስትሮን መጠን ከዕድሜ ጋር በቀስታ ሊቀንስ ሲችል በተለያዩ ወንዶች ላይ በተለያየ መጠን ሊፈጠር ይችላል። በተጨማሪም የቴስቶስትሮን መጠን በቀኑ ውስጥ ሊለዋወጥ ሲችል፤ ብዙውን ጊዜ በጠዋት ከፍ ያለ ሲሆን በኋላ በቀኑ ውስጥ ሊቀንስ ይችላል።
ቴስቶስትሮን ከዕድሜ ጋር ምን ያህል ይቀንሳል?
የቴስቶስትሮን መጠን በአብዛኛዎቹ ወንዶች ከ30–40 ዓመት ባለው እድሜ አካባቢ ጀምሮ በቀስታ መቀነስ ሊጀምር ይችላል። ከ30-40 ዓመት ጀምሮ በአማካይ በየዓመቱ 1% ያህል ሊቀንስ ሲችል፤ ከወጣትነት ጋር ሲነጻጸር በ60 ዓመት ዕድሜ የቴስቶስትሮን መጠን በግምት ከ20–30% ያህል ዝቅ ሊል ይችላል። ሆኖም የመቀነሱ መጠን ከሰው ወደ ሰው በእጅጉ ስለሚለያይ፤ የዕድሜ መጨመር ብቻ የቴስቶስትሮን እጥረት እንዳለ አያረጋግጥም።
የቴስቶስትሮን መቀነስ ምን ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል?
የቴስቶስትሮን መጠን በእጅጉ መቀነሰ እንደሚከተሉት ካሉ ምልክቶች ጋር ተያይዞ ሊታይ ሲችላል፤ ምልክቶቹም:-
- የጾታዊ ፍላጎት መቀነስ
- የጡንቻ ጥንካሬና መጠን መቀነስ
- የኃይል ማነስ ወይም የድካም ስሜት
- የአጥንት ጥንካሬ መቀነስ
- የስሜት መለዋወጥ ወይም የተነሳሽነት መቀነስ
- ትኩረት የማድረግ ችግር
- የሰውነት ስብ መጨመር
- የብልት መቆም ችግር እና
- የጾታዊ አፈጻጸም ለውጥ ናቸው።
ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች ሙሉ በሙሉ የቴስቶስትሮን መቀነስን ብቻ የሚያመለክቱ አይደሉም። የእንቅልፍ እጥረት፣ ውፍረት፣ ጭንቀት፣ አንዳንድ መድኃኒቶች እና ሌሎች የጤና ችግሮችም ተመሳሳይ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የቴስቶስትሮን መጠን ምርመራ መቼ ያስፈልጋል?
አጠቃላይ የቴስቶስትሮን መጠንን በደም ምርመራ መለካት ቢቻልም የደም ምርመራ ብቻውን የቴስቶስትሮን እጥረትን ለመመርመር በቂ አይደለም።
የሚያሳስቡ ምልክቶች ካሉ፣ የጤና ባለሙያዎች የምልክቶች ታሪክን ከአካልዊ ምርመራ ጋር በማጣመር የቴስቶስትሮን ምርመራዎችን ሊያዙ ይችላሉ። ምርመራው ብዙውን ጊዜ ጠዋት ላይ ቢደረግ የተሻለ ሲሆን ዝቅተኛ ውጤት ከተገኘ እንደገና ሊደረግ ይችላል።
በተፈጥሮ የቴስቶስትሮን ጤናን ለመደገፍ ምን ማድረግ ይቻላል?
የቴስቶስትሮን መጠንን ብቻ ለማሳደግ ከማሰብ ይልቅ አጠቃላይ ጤናን መጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
ክብደት እንደማንሳት፣ ካሊስቴኒክስ እና ሃይድሮክስ ያሉ የጡንቻ ማጠናከሪያ እና ካርዲዮ ልምምዶች ጠቃሚ ናቸው።
- ጤናማ ምግብ
በቂ ፕሮቲን፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ሙሉ እህሎች እና ጤናማ ቅባቶችን ያካተተ ጤናማ አመጋገብ አስፈላጊ ነው።
- በቂ እንቅልፍ
የእንቅልፍ እጥረት የቴስቴስትሮን ምርትን እና የሆርሞን ሚዛንን ሊነካ እና ሊያዛባ ይችላል።
- ጤናማ የሰውነት ክብደት
ከመጠን በላይ የሰውነት ስብ መኖር ከዝቅተኛ ቴስቶስትሮን ጋር ሊያያዝ ይችላል።
- አልኮል መቀነስ እና ማጨስ ማቆም
እነዚህ ልማዶች አጠቃላይ የወንድ ጤናን በመጉዳት የቴስቴስትሮን ምርት ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ።
ህክምና ያስፈልጋል?
የቴስቶስትሮን መተካት ሕክምና የሆርሞን እጥረት በተገቢው የሕክምና ምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ በሐኪም ክትትል ሊሰጥ ይችላል። ራስዎን በመመርመር የቴስቶስትሮን መድኃኒት ወይም “testosterone booster” የሚባሉ ምርቶችን መጠቀም አይመከርም። ከዕድሜ ጋር የቴስቴስትሮን መጠን መቀነስ ብቻውን የቴስቶስትሮን መተካት ሕክምና ለመጀመር በቂ ምክንያት አይደለም። የቴስቶስትሮን እጥረት እንዳለ ከጠረጠሩ የራስን ሕክምና ከመጀመር ይልቅ የጤና ባለሙያን ያማክሩ።
የቴስቶስትሮን መጠን ከዕድሜ ጋር መቀነስ የተፈጥሮ የእርጅና ሂደት አካል ሲሆን ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ እንቅስቃሴ፣ በቂ እንቅልፍ እና ጤናማ ክብደትን መጠበቅ አጠቃላይ ጤናን እና የሆርሞን ጤናን ለመደገፍ ይረዳሉ።


