💄የምትወጅው ሊፕስቲክ የከንፈር ለምጽ ወይም መጥቆር ሊያስከትልብሽ እንደሚችል ታውቂያለሽ?
ሊፕስቲክ እራስሽን ለማስዋብ አዘውትረሽ ልትጠቀሚ ትችያለሽ ። ነገር ግን የተወሰኑ ሊፕስቲኮችን ከተቀባሽ በኋላ ከንፈርሽ ሊጠቁር፣ ወዙን ሊያጣ ወይም ነጣ ያሉ ቦታዎች (ለምጽ የሚመስሉ ምልክቶች) ሊወጡበት ይችላል።
አንዳንድ ሊፕስቲኮች (በተለይም ጥራታቸው ዝቅተኛ የሆኑት) የከንፈርን ተፈጥሯዊ ቀለም የሚለውጡ የቆዳ መቆጣቶችና የአለርጂ ምላሾችን ያስከትላሉ። እነዚህ ለውጦች ከንፈርሽ እጅግ እንዲጠቁር (Hyperpigmentation) ወይም ነጣ ያሉ ቦታዎች እንዲፈጠሩበት (Hypopigmentation) ሊያደርጉ ይችላሉ።
ስለዚህ አዘውትረሽ ሊፕስቲክ የምትቀቢ ከሆነና በከንፈርሽ ቀለም ላይ ለውጥ ካስተዋልሽ ይህን ጽሑፍ በጥንቃቄ አንብቢ!
በሊፕስቲክ ምክንያት የከንፈር መጥቆር እንዴት ይከሰታል?
ከንፈር እጅግ ለስላሳ ቆዳ ያለው በመሆኑ በሊፕስቲክ ውስጥ በሚገኙ ንጥረ ነገሮች በቀላሉ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። በውስጡ ያሉት የሽቶ ጠረኖች፣ ሰው-ሠራሽ ቀለሞች፣ ጣዕም ሰጪ ንጥረ ነገሮች (Flavouring agents) እና ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ የሚያደርጉ ኬሚካሎች (preservatives) የከንፈር ቆዳ እንዲቆጣ ወይም በንክኪ የሚከሰት አለርጂ (Allergic contact dermatitis) እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
ተደጋጋሚ ብግነት በሚከሰትበት ጊዜ የከንፈር ቆዳ በማገገም ሂደት ላይ እያለ ተጨማሪ ሜላኒን (Melanin) እንዲያመርት ይገደዳል። ይህም ከብግነት በኋላ የሚከሰት የከንፈር መጥቆርን (Post-inflammatory\ hyperpigmentation) ያስከትላል። ብግነቱን የሚያስከትለውን ሊፕስቲክ መጠቀም በቀጠልሽ ቁጥር ደግሞ መጥቆሩ እየባሰ ይሄዳል።
ከዚህም በተጨማሪ የሚከተሉት ሁኔታዎች የከንፈር መጠቁርን ሊያባብሱት ይችላሉ፦
- ሊፕስቲኮችን አዘውትሮ መጠቀም
ብግነትን የሚያስከትል ንጥረ ነገር ያላቸውን ሊፒስቲክዎች በተደጋጋሚ መጠቀም የከንፈር መጥቆርን ያባብሳል።
- ድርቅ የሚሉ (Matte) እና ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ ተደርገው የሚሰሩ ሊፒስቲኮችን
እነዚህ ሊፕስቲኮች በራሳቸው ከንፈርን የሚያደርቁ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለማስለቀቅ ሲባል በኃይል የመታሸት እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ጥቃቅን ጉዳቶችና ብግነትን ያመጣሉ። ይህም በጊዜ ሂደት ከንፈርሽ ወዙን እንዲያጣ፣ ያልተስተካከለ እንዲመስልና እንዲጠቁር ያደርገዋል።
- ከንፈርን በኃይል ማሸት ወይም መፈቅፈቅ
በከንፈር ቆዳ ላይ ጥቃቅን ጉዳቶችንና ብግነትን በማስከተል መጥቆሩን ያባብሰዋል።
- ጥራታቸው ዝቅተኛ ወይም ፌክ (Counterfeit) የሆኑ ሊፕስቲኮች
ቁጥጥር ያልተደረገባቸው ኬሚካሎችን፣ ያልተረጋገጡ ንጥረ ነገሮችንና የመበከል ስጋት ስላሏቸው የከንፈርን ቆዳ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳሉ።
በሊፕስቲክ ምክንያት ከንፈር ላይ ለምጽ የሚመስሉ ምልክቶች እንዴት ይከሰታሉ?
በብዛት ከሊፕስቲኮች ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የከንፈር መጥቆር ቢሆንም በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን ለምጽ የሚመስሉ ነጣ ያሉ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
የከንፈር ቆዳ ብግነት ወይም በንክኪ የሚከሰት አለርጂ (Allergic contact dermatitis) አንዳንዴ ወደ ሃይፖፒግመንቴሽን (Hypopigmentation) ወይም የቆዳ ቀለም መቀነስ ሊያመራ ይችላል። ይህም የተጎዳው የከንፈር ክፍል አጠገቡ ካለው ቆዳ ይበልጥ ነጣ ብሎ እንዲታይ ያደርገዋል።
ሆኖም ግን ከንፈር ላይ የሚፈጠሩ ነጣ ያሉ ቦታዎች በሙሉ በሊፕስቲክ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው ማለት አይደለም። እንደ ለምጽ (Vitiligo)፣ ልዩ ልዩ ኢንፌክሽኖች፣ የቆዳ በሽታዎች እና ቀደም ሲል የደረሱ ጉዳቶች የከንፈርን ተፈጥሯዊ ቀለም እንዲጠፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ስለሆነም የማይለቅ፣ እየተስፋፋ የሚሄድ ወይም ምክንያቱ ያልታወቀ ነጭ ቦታ ከንፈርሽ ላይ ካስተዋሽ ወዲያውኑ የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪም ማማከር ይኖርብሻል።
የከንፈርሽ ቀለም እንዳይቀየር ምን ማድረግ ትችያለሽ?
ሊፕስቲክ መጠቀምን ሙሉ በሙሉ ማቆም አያስፈልግሽም። ይልቁንም ከንፈርሽ የሚቆጣበትን እድል በመቀነስ እና ከንፈርሽን በመንከባከብ ላይ ትኩረት ያድርጊ።
ከንፈርሽ እንዳይጠቁር ወይም ከንፈርሽ ላይ ነጭ ቦታዎች እንዳይፈጠሩ የሚረዱ ምክሮች እንደሚከተሉት ቀርበዋል
- ሊፕስቲክ ከመግዛትሽ በፊት ከጀርባው ያለውን ዝርዝር አንብቢ። እንደ ሊድ (Lead) ያሉ ጎጂ ኬሚካሎችን፣ Red Dye 40፣ Yellow Lake 5፣ የአሉሚኒየም ውህዶችን ወይም በውስጡ የያዘው ሳይገለጽ Parfum ብቻ ተብሎ የተጻፈባቸውን ሊፕስቲኮች ከመጠቀም ተቆጠቢ
- እንደ ካርናውባ (Carnauba) ያሉ ተፈጥሯዊ ሰሞችን (Waxes) እና እንደ ቪታሚን ኢ (Vitamin E) ያሉ ከንፈርን የሚያለሰልሱና የሚጠብቁ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ሊፕስቲኮችን ተጠቀሚ
- ሊፕስቲክ ከመቀባትሽ በፊት ሁልጊዜ የፀሐይ መከላከያ (SPF) ያለው የከንፈር ቅባት ወይም የከንፈር ፕራይመር (Lip primer) በመጠቀም ከንፈርሽ ላይ ከለላ የሚፈጥር ንብርብር ፍጠሪ
- ለረጅም ጊዜ የሚቆዩና ድርቅ የሚሉ (Matte) ሊፕስቲኮች ከንፈርን ስለሚያደርቁ አዘውትረሽ አትጠቀሚ። የምትጠቀሚ ከሆነ ደግሞ ስታስለቅቂ ቀስ አድርገሽ በማጽዳት ከንፈርሽን እርጥበት በሚሰጥ ቅባት አለስልሺ
- በጭራሽ ሊፕስቲክ እንደተቀባሽ አትተኚ። ከመተኛትሽ በፊት ቀስ አድርገሽ በደንብ በማጽዳት ከንፈርን የሚያለሰልሱና እርጥበት የሚሰጡ ቅባቶችን ተቀቢ
- የምትቀቢው ሊፕስቲክ ሽታው፣ ቀለሙ ወይም ይዘቱ (Texture) ከተቀየረ መጠቀምሽን በአስቸኳይ አቁሚ። በተጨማሪም ለከንፈርሽ ጤና ሲባል የሊፕስቲክ መዋቢያዎችሽን ከሌሎች ሰዎች ጋር ከመጋራት ተቆጠቢ።
ወደ ሐኪም መቼ መሄድ ይኖርብሻል?
እያንዳንዱ የከንፈር ቀለም መለወጥ የሕክምና እርዳታ ላያስፈልገው ይችላል። ሆኖም የሚከተሉት ሁኔታዎች ካጋጠሙሽ የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪም (Dermatologist) ማማከር ይኖርብሻል፦
- ችግሩን አምጥቷል ብለሽ ያሰብሽውን ሊፕስቲክ መጠቀም ካቆምሽ በኋላም የከንፈርሽ መጥቆር ወይም ነጣ ያለው ቦታ ካልጠፋ
- ከንፈርሽ ላይ የተፈጠረው የቀለም መለወጥ ያለ ምንም ግልጽ ምክንያት ከሆነ
- ከንፈርሽ ላይ የወጡት ነጣ ያሉ ቦታዎች ወይም መጥቆሩ እየጨመሩ እና ወደ ሌላ ቦታ እየተስፋፉ ከሄዱ
- ሊፕስቲኩን አቁመሽ እንኳ ማሳከኩ፣ እብጠቱ፣ ሕመሙ ወይም መቆጣቱ ካላቆመ እና
- የማይጠፋ ቁስል፣ የደረቀ ቅርፊት ወይም ደም መፍሰስ ከተከሰተ ሐኪምሽን አማክሪ።
የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪምሽ የቀለም መለወጡ በአለርጂ፣ በብግነት፣ በለምጽ (Vitiligo)፣ በኢንፌክሽን ወይም በሌሎች የቆዳ ሕመሞች ምክንያት የመጣ መሆኑን ለመለየት ይረዳሻል።




