የቶንሲል ቀዶ ሕክምና (Tonsillectomy)

Biruh Tesfaye
Sep 17, 2026
images   2026 09 17T145042.826

ቶንሲል ቀዶ ሕክምና (Tonsillectomy) ማለት ቶንሲሎችን በቀዶ ሕክምና ማስወገድ ነው። ቶንሲሎች በጉሮሮ ጀርባ ላይ የሚገኙ ሁለት ሞላላ ቅርጽ ያላቸው የሕብረ ሕዋስ ክፍሎች ናቸው። በእያንዳንዱ ጎን አንድ አንድ ቶንሲል ይገኛል። ቶንሲሎች የሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓት አካል ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ቶንሲሎች ሊቆጠቁ እና የጉሮሮ ሕመም ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም ሊያብጡ እና የአየር መተላለፊያዎን በከፊል ሊዘጉ ይችላሉ። በነዚህም ምክኛቶች ይህ የቀዶ ሕክምና ሂደት ሊሰራ ይችላል።

አዋቂዎችም አንዳንድ ጊዜ የቶንሲል ቀዶ ሕክምና (Tonsillectomy) ሊያስፈልጋቸው ቢችልም፣ ይህ ቀዶ ሕክምና በሕፃናት ላይ በብዛት ይደረጋል። ቶንሲሎች በልጅነት ጊዜ መጠናቸው ይጨምራል፣ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ ግን ሊቀንሱ ይችላሉ። ስለዚህ ሕፃናት የቶንሲል ማስወገጃ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የመሆኑ ዕድል ከአዋቂዎች የበለጠ ነው።

የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ለምን ይደረጋል?

የቶንሲል ማስወገጃ ቀዶ ሕክምና ብዙውን ጊዜ ለሕፃናት ይደረጋል። ሆኖም በአዋቂዎች ላይም በሚከተሉት ምክንያቶች ቶንሲል ማስወገድ ሊያስፈልግ ይችላል፦

  • በተደጋጋሚ የሚከሰት እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የጉሮሮ ሕመም ካለ። በተደጋጋሚ ማለት የቶንሲል እብጠት/ኢንፌክሽን (Tonsillitis) ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ 7 ጊዜ ከተከሰተ፣ ባለፉት 2 ዓመታት በየዓመቱ ቢያንስ 5 ጊዜ ከተከሰተ ወይም ባለፉት 3 ዓመታት በየዓመቱ ቢያንስ 3 ጊዜ ከተከሰተ ማለት ነው።
  • በቶንሲሎች ማበጥ ምክንያት የአየር መተላለፊያ በመዘጋቱ የሚከሰት በእንቅልፍ ጊዜ የመተንፈስ መቋረጥ (Sleep apnoea) ካለ
  • በቶንሲሎች ኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰት ከባድ የአፍ ጠረን (Halitosis) ከተከሰተ
  • በቶንሲል አካባቢ ካንሰር ከተከሰተ
  • በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የቶንሲል ጠጠሮች (Tonsil stones)።
  • የቶንሲል መድማትን ለማከም።
  • የቶንሲል እብጠትን የሚያስከትል የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ቢታከምም ካልተሻሻለ።
  • ከቶንሲል ጀርባ መግል እንዲከማች የሚያደርግ ኢንፌክሽን ካለ (የቶንሲል አብሰስ /Tonsillar abscess) 
  • በተደጋጋሚ እና በከፍተኛ ድምፅ ማንኮራፋት (Snoring) ካጋጠምዎት 

የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

የቶንሲል ቀዶ ሕክምና (Tonsillectomy) መደረጉ በርካታ ጥቅሞችን ሊያስገኝ ይችላል፣ እነሱም፦

  • የእንቅልፍ ጥራት መሻሻል
  • የኢንፌክሽን መከሰት መቀነስ
  • የኑሮ ጥራት መሻሻል

የቶንሲል ቀዶ ሕክምና አደጋዎች

የቶንሲል ማስወገጃ ቀዶ ሕክምና (Tonsillectomy) እንደሌሎች ቀዶ ሕክምናዎች አንዳንድ አደጋዎች ሊኖሩት ይችላል፣ እነሱም፦

  • ለማደንዘዣ መድኃኒት የሚከሰት ምላሽ: በቀዶ ሕክምና ጊዜ ለማስተኛት የሚሰጡ መድኃኒቶች ብዙውን ጊዜ ቀላልና ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ችግሮችን፣ ለምሳሌ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ ወይም የጡንቻ ሕመምን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
  • እብጠት: የምላስ እና ለስላሳው የላንቃ ክፍል እብጠት ሊያጋጥም ይችላል። ይህም ብዙውን ጊዜ ቀዶ ሕክምናው ከተደረገ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰዓታት ይከሰታል።
  • በቀዶ ሕክምና ጊዜ መድማት: አልፎ አልፎ በቀዶ ሕክምናው ወቅት ደም መፍሰስ ሊከሰት ይችላል። ይህም ተጨማሪ ሕክምና እና ረዘም ያለ የሆስፒታል ቆይታ ሊያስፈልገው ይችላል። ቁስሉ በሚድንበት ጊዜ ደም ሊፈስ ይችላል።
  • ኢንፌክሽን: አልፎ አልፎ ሕክምና የሚያስፈልገው ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል።

ይህ የቀዶ ሕክምና ሂደት ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ብዙውን ጊዜ ለማጠናቀቅ ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ያህል ይወስዳል። ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ከዚህ የበለጠ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ያደረጉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ቀዶ ሕክምናው በተደረገበት ቀን ወደ ቤታቸው መመለስ ይችላሉ። ነገር ግን ያልተጠበቁ ችግሮች ከተከሰቱ፣ ቀዶ ሕክምናው ትንሽ ሕፃን ላይ ከተደረገ ወይም ሌሎች የጤና ችግሮች ካሉ፣ ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሌሊት መቆየት ሊያስፈልግ ይችላል። 

በአማካይ፣ አብዛኛዎቹ ሰዎች በ2 ሳምንታት ያህል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ። የማገገሚያ ጊዜው እንደተደረገልዎት የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ዓይነት፣ ሰውነትዎ በተለምዶ ምን ያህል ፈጣን እንደሚያገግም እና በቀዶ ሕክምናው ወቅት ማንኛውም ችግር እንደተከሰተ ሊለያይ ይችላል።

ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ምን ላድርግ?

ሕመምን ለመቆጣጠር እና በፈጣኑ ለማገገም የሚከተሉትን ይከተሉ፦

  • መድኃኒቶች: የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን የጤና ባለሙያዎ እንዳዘዘዎት ይውሰዱ።
  • ፈሳሽ: ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የሰውነት ውሃ እጥረት (Dehydration) እንዳይከሰት ብዙ ፈሳሽ ይጠጡ። ውሃ እና የቀዘቀዙ የፍራፍሬ ጭማቂዎች እና ጣፋጭ በረዶዎች ጥሩ ምርጫዎች ናቸው።
  • ምግብ: ከቀዶ ሕክምናው በኋላ በቀላሉ ሊዋጡ የሚችሉ ለስላሳ ምግቦች፣ ለምሳሌ የተፈጨ አፕል ወይም ቀላል ሾርባ፣ በተለይ ይመከራሉ። የማይረብሹዎት ከሆነ አይስክሬም እና ፑዲንግ ያሉ ምግቦችንም መጨመር ይችላሉ። ሕመም ወይም መድማት ሊያስከትሉ ከሚችሉ አሲዳማ፣ ቅመማ ቅመም የበዛባቸው፣ ጠንካራ ወይም ደረቅ ምግቦች ከመብላት ይቆጠቡ።
  • እረፍት: ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ለበርካታ ቀናት በቂ እረፍት ያድርጉ። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ለ2 ሳምንታት መሮጥ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም ሌሎች ከባድ እንቅስቃሴዎችን አያድርጉ።

 

 

Comments (0)