የፊንጢጣ መሰንጠቅ (Anal fissure)
የፊንጢጣ መሰንጠቅ (Anal fissure) ማለት በፊንጢጣ መውጫ ማስተላለፊያ ቱቦ ስስ ሽፋን ላይ የሚፈጠር ትንሽ መቀደድ ወይም መቆረጥ ሲሆን፥ ሰገራ በሚወጣበት ወቅት እና ከዚያ በኋላ ከባድ እና የሚለበልብ ህመም እንዲሁም ደማቅ ቀይ ደም እንዲፈስ ያደርጋል።
የፊንጢጣ መሰንጠቅ (Anal fissure) በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል ፦
- አጣዳፊ (Acute) — ከ6 ሳምንታት በታች የሚቆዩ እና በመሠረታዊ እንክብካቤ ብዙውን ጊዜ የሚድኑ ናቸው።
- ስር የሰደደ (Chronic) — ከ6 ሳምንታት በላይ የሚቆዩ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ የጡንቻ ፋይበሮች መጋለጥ ወይም “sentinel pile” ተብሎ የሚጠራ ትንሽ የቆዳ ጠጠር/ተጨማሪ የቆዳ ክፍል ይኖራቸዋል።
መንስኤዎች
የፊንጢጣ መሰንጠቅ በዋነኝነት የሚከሰተው በፊንጢጣ ቱቦ ላይ በሚደርስ ጉዳት፣ በአካባቢው በሚኖር የደም ዝውውር መቀነስ ወይም ከስር ባሉ የተለያዩ የጤና ሁኔታዎች ነው፡
- የሆድ ድርቀት ፦ ጠንካራ፣ ደረቅ ወይም ከልክ በላይ ትልቅ ሰገራ ማውጣት፣ እንዲሁም ተደጋገሚ ድንገተኛ ወይም ሥር የሰደደ ተቅማጥ
- የፊንጢጣ ጡንቻ መኮማተር (Anal Sphincter Spasms)፦ የውስጠኛው የፊንጢጣ ጡንቻ ከልክ በላይ መወጠር (Hypertonia) በአካባቢው ያለውን የደም ዝውውር ስለሚገታ ህብረ-ህዋሱ (ቲሹው) በቀላሉ እንዲቀደድና ለማገገም እንዲዘገይ ያደርጋል።
- ወሊድ፦ በወሊድ ወቅት በሚኖር ምጥ እና የአካል ክፍሎች (ቲሹ) ጉዳት።
- ህመሞች፦ የአንጀት እብጠት ህመም (በተለይም የክሮንስ ህመም / Crohn's disease)፣ የፊንጢጣ ካንሰር፣ ወይም እንደ ኤች.አይ.ቪ (HIV)፣ ቂጥኝ (Syphilis)፣ ሄርፒስ (Herpes) ወይም ቲቢ (Tuberculosis) ያሉ ኢንፌክሽኖች (በተለይም ያልተለመዱ የፊንጢጣ ክፍሎች ላይ ሲከሰት )።
- በምግብ ውስጥ አነስተኛ የፋይበር (ቃጫ) መጠን መኖር
- በቂ ውሃ አለመጠጣት
ምርመራ (Diagnosis)
የፊንጢጣ መሰንጠቅ ምርመራ በዋነኝነት በህመም ምልክቶች ላይ የተመሰረተ ሲሆን
- በዓይን ማየት (Visual Inspection)፦አብዛኛዎቹ የፊንጢጣ መሰንጠቆች (ከ90% በላይ) ከጀርባ በኩል ባለው መካከለኛ መስመር ላይ ይከሰታሉ።
- በጣት የሚደረግ የፊንጢጣ ምርመራ (Digital Rectal Examination - DRE)፦ በከባድ ህመም ምክንያት፣ በተለይም በድንገተኛ ህመም ወቅት የሚከሰትን የፊንጢጣ መሰንጠቅ ለማየት ይህ ምርመራ ይመከራል፡፡
- ኤንዶስኮፒ / ኮሎኖስኮፒ / አኖስኮፒ (Endoscopy / Colonoscopy / Anoscopy)፦ የፊንጢጣ መሰነጠቁ ከመካከለኛው መስመር ውጪ (በጎን በኩል) ከሆነ፣ በመደበኛ ህክምናዎች ካልዳነ፣ ወይም የአንጀት እብጠት ህመም፣ ኢንፌክሽን ወይም የካንሰር ጥርጣሬ ካለ የሚመከር የምርመራ ዓይነት ነው።
የ ሕመም ምልክቶቹ (Symptoms)

የፊንጢጣ መሠንጠቅ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡
- ሰገራ በሚወጣበት ጊዜ እና ከወጣ በኋላ የሚሰማ ሕመም፦ ሕመሙ ከባድ ሊሆን ይችላል።
- በፊንጢጣ አካባቢ የማቃጠል ስሜት
- በፊንጢጣ ዙሪያ ማከክ፣ ቀለል ያለ የማቃጠል ስሜት እና ደም መፍሰስ፦ (ለምሳሌ፡ ከተፀዳዱ በኋላ በሶፍት ሲያብሱ ጥቂት ነጠብጣብ ደማቅ ቀይ ደም ሊያዩ ይችላሉ)
- በፊንጢጣ አፍ ላይ የሚሰማ እብጠት ወይም የተንጠለጠለ ቁራጭ ቆዳ (በሴንቲኔል ፓይል / sentinel pile ጊዜ)፦ ይህም ሕመም ሊኖረው ወይም ላይኖረው ይችላል።
የፊንጢጣ መሠንጠቅ ሕክምናው ምንድን ነው?
የፊንጢጣ መሠንጠቅ በሚከተሉት አሰራሮች በአንዱ ወይም በበርካታ ዘዴዎች ቅንጅት ሊታከም ይችላል፡
- የአመጋገብ እና የሕይወት ዘይቤ ለውጥ፦ ከፍተኛ የፋይበር መጠን ያለው ምግብ፣ በቂ ፈሳሽ መጠጣት፣ በሞቀ ውሃ መዘፍዘፍ (sitz bath) እና የቅዝቃዜ ከረጢት (cold packs) መጠቀም ወዘተ።
- መድኃኒቶች፦ የሚቀቡ ቅባቶች (creams)፣ በአፍ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ወዘተ።
- ቀዶ-ሕክምና ያልሆኑ ሂደቶች፦ Rubber band ligation(በላስቲክ ባንድ የማሰር ህክምና)፣ Injection sclerotherapy(በመርፌ ኬሚካል በማስገባት የማድረቅ ህክምና) ወዘተ።
- ቀዶ-ሕክምና፦ የሌዘር ሕክምና (Laser ablation)፣ የደም ሥር ማሰር (Arterial ligation)፣ መደበኛ ወይም በስቴፕለር የሚደረግ የፊንጢጣ ቀዶ-ሕክምና ይገኝበታል።
መከላከያ መንገዶቹ (Prevention)
- ከፍተኛ የፋይበር (ቃጫ) መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገብ፦ የሙሉ እህል ውጤቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ ጥራጥሬዎችን እና ዘሮችን በዕለት ተዕለት ምግብዎ ውስጥ ያካቱ።
- በቂ ውሃ መጠጣት፦ ሰገራ ለስላሳ ሆኖ እንዲቆይ ቀኑን ሙሉ በቂ ውሃ ይጣጡ።
- በሽንት ቤት ወቅት ማማጥ እና ረዥም ጊዜ መቆየት ፦ ሰገራ ለማውጣት በኃይል አያምጡ ወይም መፀዳጃ ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ አይቀመጡ ።
- የመፀዳዳት ስሜት ሲመጣ አለማዘግየት፦ የመፀዳዳት ስሜት እንደመጣ ወዲያውኑ ይፀዳዱ፤ ማዘግየት አንጀት ከሰገራው ላይ ውሃ እንዲመጥ ስለሚያደርገው ሰገራው ደረቅና ጠንካራ እንዲሆን ያደርጋል።




