ጥሬ ጉበትን መመገብ
ጉበት ከፍተኛ ጥራት ያለው ፕሮቲን፣ አይረን፣ ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ቢ12፣ ፎሌት፣ መዳብ እና ሌሎች ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ምግብ ነው። አንዳንድ ሰዎች ንጥረ ነገሮቹን እንደያዘ ይቆያል ብለው በማመን ጥሬ ጉበትን ሳያበስሉ የሚመገቡ ሲሆን ከምግብ ደህንነት ጋር የተያያዙ ከፍተኛ አደጋዎችንም ሊያስከትል እንደሚችል ልብ ማለት ያስፈልጋል።
የጉበት ስነ-ምግብ ይዘት
ጉበት የሚከተሉትን ጠቃሚ የስነ-ምግብ ግባቶች ይይዛል።
- ፕሮቲን፡- የጡንቻ እድገትን፣ የሰውነት ጥገናን እና የበሽታ መከላከል ተግባርን ይደግፋል።
- ቫይታሚን ኤ፡- ለእይታ፣ ለበሽታ መከላከል እና ለጤናማ ቆዳ አስፈላጊ ነው።
- ቫይታሚን B12፡- ለቀይ የደም ሴሎች እና ለነርቭ መደበኛ ተግባር አስፈላጊ ነው።
- ፎሌት፡- የሕዋስ እድገትን እና የቀይ የደም ሴሎች ምርትን ይደግፋል።
- አይረን፡- ጤናማ ቀይ የደም ሴሎችን ለማምረት እና የአይረን እጥረት የሚያመጣውን ችግሮች ለመከላከል ይረዳል።
- መዳብ እና ሌሎች ማዕድናት፡- የሰውነታችን አይረንን እንዲጠቀም ለማገዝ፣ የበሽታ መከላከል ስርአትን ለመደገፍ እና መደበኛ የሰውነት ተግባራትን ለማስቀጠል ይጠቅማል።
ንጥረ ነገሮች በጉበት ውስጥ በብዛት የተከማቹ ስለሆኑ፤ ትንሽ አቅርቦት እንኳን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን በርካታ ቫይታሚኖችን እና ማዕድናትን መስጠት ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሞች የሚገኙት በጉበት ውስጥ ከሚገኙት ንጥረ ነገሮች እንጂ ጥሬውን በመመገብ አይደለም። ጉበትን ሳይበስል መመገብ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ የተረጋገጠ ምንም መረጃ የለም።
ጥሬ ጉበትን የመመገብ አደጋዎች
ጥሬ ጉበትን የመመገብ ዋና ስጋት በምግብ አማካኝነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ናቸው። ለምግብነት የሚውሉ ጥሬ የእንስሳት አካል ክፍሎች እንደ ሳልሞኔላ፣ ካምፓይሎባክተር፣ አንዳንድ የኢ-ኮላይ ዝርያዎች ያሉ ጎጂ ባክቴሪያዎችን እና የተለያዩ ጥገኛ ተህዋሲያንንም ሊይዙ ይችላሉ።
በተለይም ጥሬ ምግብን በመመገብ ምክንያት የሚከሰት የምግብ መመረዝ ለነፍሰ ጡር ሴቶች፣ ለህጻናት፣ ለአረጋውያን እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው ለተዳከመ ሰዎች ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ።
በተጨማሪም ጉበት ከፍተኛ መጠን ያለው 'ፕሪፎርምድ ቫይታሚን ኤ'ን ስለሚይዝ፤ በብዛት እና በተደጋጋሚ ይህን ምግብ መመገብ ከሚያስፈልገው በላይ ቫይታሚን ኤ እንዲከማች እና በእርግዝና ወቅት የሚኖር የጽንስ አወቃቀር ላይ ስጋት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
ደህንነቱ የተጠበቀ የጉበት አመጋገብ
የጉበትን ስነ-ምግብ ጠቀሜታዎች ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ለማግኘት፡-
- ጉበትን በጥሬው ወይም በደንብ ሳይበስል ከመመገብ ይልቅ በደንብ አብስለው ይመገቡ።
- ጉበትን ከታመነ ምንጭ ይግዙ እንዲሁም ደህንነቱ በተጠበቀ ማቀዝቀዣ ውስጥ ያስቀምጡት።
- ጥሬ ጉበትን ለመመገብ ዝግጁ ከሆኑ ምግቦች ለይተው ያስቀምጥጡ እንዲሁም የማብሰያ ዕቃዎች እና ቦታዎችን በትክክል በማጽዳት የብክለት መተላለፍን ይከላከሉ።
- ከፍተኛ መጠን ያለው ቫይታሚን ኤ ስላለው ጉበትን በመጠኑ ይመገቡ።
- ነፍሰ ጡር ሴቶች ለኢንፌክሽን እና ከመጠን በላይ ቫይታሚን ኤን ለመውሰድ አደጋ እንዳይጋለጡ ልዩ ጥንቃቄን ማድረግ አለባቸው።
ጉበት ፕሮቲን፣ አይረን፣ ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ቢ12፣ ፎሌት እና መዳብን የሚያቀርብ ከፍተኛ የስነ-አመጋገብ ዋጋ ያለው ምግብ ነው። ሆኖም፣ ጥሬውን መመገብ ለጎጂ ባክቴሪያዎች እና ጥገኛ ተህዋሲያን ሊያጋልጥዎት እና ከመጠን በላይ የሆነ ቫይታሚን ኤ የመውሰድ አደጋን ሊጨምር ይችላል። በአግባቡ የበሰለ ጉበትን በመጠኑ መመገብ ጥሬ ጉበትን ከመመገብ የተሻለ ጥቅምን ይሰጣል።




