በመፀዳጃ ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የሚያስከትለው የጤና ጉዳት እና መፍትሔዎቹ

Elsabet Azezew
Nov 11, 2026
image 2026 09 22 155619151

               በመፀዳጃ ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የሚያስከትለው የጤና ጉዳት እና መፍትሔዎቹ

በዘመናችን ስልክ ይዞ ማህበራዊ ሚዲያ ወይም ቪዲዮዎችን እየተመለከቱ በመፀዳጃ ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የተለመደ ልማድ ሆኗል። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መጠናቀቅ ያለበት መፀዳዳት ስልካችን ላይ በመጠመዳችን ምክንያት ሳይታወቀን 10፣ 20 ወይም 30 ደቂቃዎችን ልንወስድ እንችላለን።

ነገር ግን ይህ ቀላል የሚመስል ልማድ በሰውነታችን በተለይም በፊንጢጣ፣ በዳሌ እና በምግብ መፈጨት ሥርዓታችን ላይ ከፍተኛ የሕክምና ችግሮችን እንደሚያስከትል ያውቃሉ? የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ መሃሉ ክፍት በመሆኑ ዳሌው ያለ ምንም ድጋፍ ተንጠልጥሎ እንዲቆይ ያደርጋል።ይህም የመሬት ስበትና የሰውነት ክብደት በፊንጢጣ ደም ሥሮች ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዲፈጥሩ ያደርጋል። 

በመጸዳጃ ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የሚያስከትላቸው ዋና ዋና የጤና ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፦ 

            1. ኪንታሮት (Hemorrhoids) 

ኪንታሮት በፊንጢጣ ወይም በውስጠኛው የፊንጢጣ ክፍል የሚገኙ የደም ሥሮች ማበጥ እና መወጠር ነው። በመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ላይ ተቀምጠን በቆየን ቁጥር የመሬት ስበት ደም በእነዚህ የደም ሥሮች እንዲሰበሰብ እና እንዲቋጠር ያደርጋል። ይህም ተደጋጋሚ ጫና የደም ሥሮቹ እንዲያብጡ እና ወደ ውጭ ወጥተው እንዲታዩ ያደርጋል።

           2.የፊንጢጣ መሰንጠቅ (Anal Fissures) 

የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ መሃሉ ክፍት በመሆኑ ምክንያት የመቀመጫችን ክፍሎች ወደ ታች እንዲወርዱ ያደርጋል። ይህም በፊንጢጣ ዙሪያ ባለው ለስላሳ ቆዳ ላይ ከፍተኛ ውጥረት ይፈጥራል። ውጥረቱ የቆዳውን የመለጠጥ አቅም ስለሚቀንሰው፣ በቀጣይ በሚኖሩ የመፀዳዳት ሂደቶች ላይ ቆዳው በቀላሉ እንዲሰነጠቅ፣ እንዲቆስልና ከፍተኛ ሕመም ወይም ደም መፍሰስ እንዲያስከትል ያደርጋል።

           3.የዳሌ ወለል ጡንቻዎች መድከም (Weakened Pelvic Floor) 

የዳሌ ወለል ጡንቻዎች ፊኛን፣ ማህፀንን (በሴቶች) እና ፊንጢጣን ደግፈው ይይዛሉ። በመፀዳጃ ቤት ለረጅም ጊዜ ተቀምጦ መቆየት በእነዚህ ጡንቻዎች ላይ ሳያቋርጥ ጫና በመፍጠር እንዲላሉና እንዲደክሙ ያደርጋቸዋል። የእነዚህ ጡንቻዎች መዳከም ደግሞ ከጊዜ በኋላ የሽንትና የሰገራ ማምለጥ (Incontinence) ወይም ለከፋ የሰገራ ድርቀት (Chronic Constipation) ያጋልጣል።

          4.የፊንጢጣ ወደ ውጭ መውጣት (Rectal Prolapse)

ይህ በጣም ከባድ ከሚባሉ የሕክምና ሁኔታዎች አንዱ ሲሆን የፊንጢጣ ውስጠኛው ክፍል (Rectum) ከቦታው በመንሸራተት በፊንጢጣ ቀዳዳ በኩል ወደ ውጭ ሲወጣ ነው። ይህ ሁኔታ በብዛት ሰገራ በሚጸዳዱበት ወቅት ወይም ከተጸዳዱ በኋላ ይከሰታል። በመፀዳጃ ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥና ማማጥ ፊንጢጣን ደግፈው የሚይዙትን የዳሌ ወለል ጡንቻዎችና ጅማቶች ስለሚጫንና ስለሚያደክም ለዚህ ችግር መከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

          5.የእግር መደንዘዝ እና የነርቭ መቆጣት (Numbness & Sciatic Nerve Pressure)

በመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ከጭን በስተጀርባ ባሉ ዋና ዋና የነርቭ መስመሮች (በተለይም የሳይያቲክ ነርቭ / Sciatic Nerve) እና የደም ሥሮች ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህም ወደ እግር የሚሄደውን የደም ዝውውር ስለሚቀንሰው በእግርና ቁርጭምጭሚት አካባቢ የመደንዘዝ፣ የመጠዝጠዝ ወይም በመርፌ እንደመወጋት የሚመስል ስሜት ያስከትላል። ይህ ልማድ በተደጋጋሚ የሚቀጥልም ከሆነ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የነርቭ መቆጣትና የጡንቻ መዳከም ሊያስከትል ይችላል።

          6.የምግብ መፈጨት እና የተፈጥሮ የመፀዳዳት ሂደት መዛባት

የሰው ልጅ አእምሮ የመፀዳዳት ስሜት በሚመጣበት ጊዜ ለአንጀት ምልክት ያስተላልፋል። በመፀዳጃ ቤት ተቀምጠን በስልክ ወይም በሌላ ነገር ስንወጠር ግን አእምሯችን ለተፈጥሮአዊው የአንጀት እንቅስቃሴ (Peristalsis) የሚሰጠውን ትኩረት ይከፋፍላል። ይህም አንጀት መደበኛ ስራውን እንዳያከናውን በማድረግ ለከፍተኛ የሰገራ ድርቀትና ለአንጀት እንቅስቃሴ መዛባት ይዳርጋል።

               በመፀዳጃ ቤት ውስጥ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመቀነስ የሚረዱ ውጤታማ መፍትሔዎች

  •  ጊዜዎን ይወሰኑ 

በመፀዳጃ ቤት ከ 5 እስከ 10 ደቂቃዎች በላይ በፍጹም ላለማሳለፍ ይሞክሩ።

  • ስልክዎን ውጭ ይተዉ 

በመፀዳጃ ቤት የሚያሳልፉትን ጊዜ የሚያረዝመው ዋናው ምክንያት ስልክዎ በመሆኑ ሲገቡ ስልክ፣ መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ ይዘው አይግቡ።

  • ታይመር (Timer) ይጠቀሙ

በመፀዳጃ ቤት የመቀመጥ ልማድ ካለዎት ጊዜዎን ለመቆጣጠር በስልክዎ ላይ የ5 ደቂቃ አላርም ማዘጋጀት ይችላሉ።

  • አነስተኛ የእግር መደገፊያ ባርጩማ (Footstool) ይጠቀሙ

እግርን ከፍ አድርጎ መቀመጥ (Squatting position) የአንጀት መውጫን ቀጥ  ስለሚያደርገው ሰገራ ያለ ምንም ጫና እና ማማጥ በፍጥነት እንዲወጣ ይረዳል።

  • አያምጡ

ከ10 ደቂቃ በኋላ ሰገራ ማስወገድ ካቃትዎት በመፀዳጃ ቤት ላይ ተቀምጠው ከማማጥ ይልቅ ተነስተው ጥቂት ውሃ ይጠጡ፣ ትንሽ ተንቀሳቅሰው የመፀዳዳት ስሜቱ ሲመጣ ብቻ ተመልሰው ይግቡ።

  • 🥗 የፋይበር ምግቦች እና ውሃ 

 ሰገራ እንዲለሰልስና የመፀዳዳት ሂደቱ ቀላል እንዲሆን በቀን ከ2-3 ሊትር ውሃ ይጠጡ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችንም አብዝተው ይመገቡ።

ልብ ይበሉ ከላይ የተጠቀሱት እንደ ደም መፍሰስ፣ ከባድ ሕመም ወይም የፊንጢጣ ወደ ውጭ መውጣት ያሉ ምልክቶች ካጋጠመዎት በአስቸኳይ የሕክምና ባለሙያ ማማከር ይኖርብዎታል።

Comments (0)