ሄፓታይተስ ቢ ይድናል?
እርስዎ ወይም በቅርብ የሚያውቁት ሰው በሄፓታይተስ ቢ ተይዘዋል? ከሁሉም በላይ ሊኖርዎት የሚችለው ጥያቄ “ሄፓታይተስ ቢ ሙሉ በሙሉ ይድናል?” የሚለው ነው።
መልካሙ ዜና ሄፓታይተስ ቢ በትክክለኛ ክትትልና ሕክምና መቆጣጠር የሚቻል በሽታ መሆኑ ሲሆን፤ ብዙ ሰዎች ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ። በተለየ መልኩ ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ሄፓታይተስ ቢ በቋሚነት የሚያጠፋ ሕክምና ለማግኘት የሚደረገው ምርምርም በቅርብ ጊዜያት አበረታች ውጤቶችን እያሳየ ነው።
1. ሄፓታይተስ ቢ ሙሉ በሙሉ ይድናል?
መልሱ በበሽታው አይነት ላይ ይመረኮዛል።
- አጣዳፊ ሄፓታይተስ ቢ (Acute Hepatitis B)፦ ብዙዎቹ ጤናማ አዋቂዎች የሰውነታቸው በሽታ የመከላከል አቅም ቫይረሱን በመዋጋት በስድስት ወራት ውስጥ ያገግማሉ።
- ሥር የሰደደ ሄፓታይተስ ቢ (Chronic Hepatitis B)፦ በዚህኛው ሁኔታ ቫይረሱ ከስድስት ወራት በላይ በሰውነት ውስጥ ይቆያል። ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋው መደበኛ ሕክምና ባይኖርም፤ ቫይረሱን በመቆጣጠር ጉበትን ከጉዳት መጠበቅ ይቻላል።
አንዳንድ ታካሚዎች ተግባራዊ ፈውስ (Functional Cure) የሚባለውን ደረጃ ሊያገኙ ይችላሉ። ይህም HBsAg የተባለው የቫይረሱ ምልክት በደም ምርመራ ሳይታይ መቅረትና ቫይረሱ በቁጥጥር ሥር መሆን ማለት ነው።
2. ምን ዓይነት ሕክምናዎች ይገኛሉ?
የሚከተሉት መድኃኒቶች ሄፓታይተስ ቢን ለማከም በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ።
- ቴኖፎቪር (Tenofovir) እና ኤንቴካቪር (Entecavir)፦ የቫይረሱን መባዛት በመከላከል ጉበትን ከጉዳት ይጠብቃሉ።
- ፔጊሌትድ ኢንተርፌሮን (Pegylated Interferon)፦ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በማነቃቃት ቫይረሱን እንዲዋጋ የሚረዳ ሲሆን ለተመረጡ ታካሚዎች ይሰጣል።
ሁሉም ታካሚዎች ወዲያውኑ መድኃኒት መውሰድ ላያስፈልጋቸው ስለሚችል ሐኪሞች የቫይረሱን መጠንና የጉበትዎን ሁኔታ ከመረመሩ በኋላ ተገቢውን ሕክምና ይመክራሉ።
3. ለቋሚ ፈውስ የሚደረገው ምርምር የት ደረሰ?
አዎ! ተመራማሪዎች ቫይረሱን በቀጥታ ለማጥቃት የተለያዩ አዳዲስ የሕክምና ዘዴዎችን እያጠኑ ነው።
ከእነዚህም መካከል፦
- አር.ኤን.ኤ ላይ የተመሰረቱ ህክምናዎች (RNA-based therapies)፦ ቫይረሱ የሚያመነጫቸውን ፕሮቲኖች በመቀነስ ይሠራሉ።
- የህክምና ክትባቶች (Therapeutic vaccines)፦ በሽታው በሰውነት ውስጥ ከተፈጠረ በኋላ የሰውነት መከላከያ አቅም ቫይረሱን እንዲዋጋ ለማሠልጠን የተዘጋጁ ክትባቶች ናቸው።
- የዘረመል ማስተካከያዎች (Gene Editing)፦ በሰውነት ውስጥ የሚቀረውን የቫይረሱን የዘረመል ንጥረ ነገር ለማስወገድ ወይም ሥራውን ለማስቆም የሚደረግ ምርምር ነው።
አስደናቂ ግኝት፦ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጣር በጥቅምት 2026 የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ቤፒሮቪርሰን/ሂብሳጎ (Bepirovirsen/Hibsago) የተባለ አዲስ መድኃኒት ለተወሰኑ ሥር የሰደደ ሄፓታይተስ ቢ ላለባቸው አዋቂዎች ጥቅም ላይ እንዲውል አጽድቋል። ይህ መድኃኒት ቫይረሱ እንዲራባ የሚረዱ የዘረመል መልዕክቶችን በማገድ ይሠራል።
እነዚህ እድገቶች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም፤ አንዳንዶቹ አሁንም በምርምር ላይ ያሉ ስለሆኑ ለሁሉም ታካሚዎች የሚሠራ ቋሚ ፈውስ ገና አልተገኘም።
4. ሄፓታይተስ ቢ እያለብኝ መደበኛ ሕይወት መኖር እችላለሁ?
አዎ! ብዙ የሄፓታይተስ ቢ ታካሚዎች ስራ መሥራት፣ ስፖርት መሥራት፣ ማግባትና ቤተሰብ መመሥረት ይችላሉ።
ጉበትዎን ከጉዳት ለመጠበቅ፦
- አልኮልን ያስወግዱ።
- ጤናማና የተመጣጠነ ምግብን ይመገቡ።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትረው ያድርጉ።
- ያለ ሐኪም ምክር ዘማናዊም ሆነ የባህል መድኃኒትን አይጠቀሙ።
- የሕክምና ክትትልን በየጊዜው ያድርጉ።
5. ቤተሰቤን ከሄፓታይተስ ቢ እንዴት መጠበቅ እችላለሁ?
ሄፓታይተስ ቢ በተበከለ ደምና አንዳንድ የሰውነት ፈሳሾች ይተላለፋል። በተጨማሪም ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል።
ራስዎንና ቤተሰብዎን ለመጠበቅ፦
- የሄፓታይተስ ቢ ክትባትን ይውሰዱ።
- መርፌ፣ ምላጭና የጥርስ ብሩሽን ከሌሎች ጋር አይጋሩ።
- ደህንነቱ የተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይኑርዎት።
- ቤተሰብዎና የወሲብ አጋርዎ ምርመራ እንዲያደርጉና ክትባት እንዲወስዱ ያበረታቱ።
ያስታውሱ! ሄፓታይተስ ቢ በመተቃቀፍ፣ እጅ በመጨባበጥ ወይም ምግብ አብሮ በመብላት አይተላለፍም።
ተስፋ አለ!
በሄፓታይተስ ቢ መያዝ ጤናማ ሕይወትን መኖር አይቻልም ማለት አይደለም። አሁን ላይ ያሉት ሕክምናዎች ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ጉበትዎን ለመጠበቅ የሚረዱ ሲሆን፤ አዳዲስ የሕክምና ምርምሮች ደግሞ ለወደፊቱ የበለጠ ውጤታማ ፈውስ የሚገኝበትን ተስፋ እያሳደጉ ነው።
ተስፋ አይቁረጡ! በየጊዜው የጤና ክትትልን ያድርጉ እንዲሁም የሐኪምዎን ምክር ይከተሉ።
ማጣቀሻዎች፦




