የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ሙዝ መብላት ይችላሉ?
የስኳር ህመም በሚኖርበት ጊዜ በደም ውስጥ ያለውን የስክኳር መጠን በሚገባ ሁኔታ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። ጥሩ የሆነ የደም የስኳር መጠን ቁጥጥር (አያያዝ) መኖር በስኳር ህመም ምክንያት የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመከላከል እና ከተፈጠሩም እንዳይባባስ ይረዳል። ስለሆነም የደም የስኳር መጠንን የሚጨምሩ ምግቦች ከመመገብ መቆጠብ ወይም መቀነስ አስፈላጊ ነው።
ምንም እንኳን ሙዝ ጤናማ ፍራፍሬ ቢሆንም በስኳር እና በካርቦሃይድሬት የበለጸገ በመሆኑ የደም የስኳር መጠንን ይጨምራል።
ሙዝ የደም የስኳር መጠንን የሚጨምረውን ካርቦሃይድሬት የተባለውን ንጥረነገር በውስጡ ይዟል።
ካርቦሃይድሬት ከለሎች ንጥረነገሮች በላይ የደም የስኳር መጠንን ይጨምራል። የስኳር በሽታ የሌለባቸው ሰዎች የደም የስኳር መጠናቸው ሲጨምር ሰውነታቸው ኢንሱሊን የተባለውን ሆርሞን በማምረት ስኳር ከደም ወደ የሰውነት ህዋሳት እንዲገባ እና እንዲከማች ያደርጋል። ነገር ግን የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች በቂ የሆነ ኢንሱሊን ስለማያመርቱ ወይም የሰውነት ህዋሳት ለዚህ ኢንሱሊን በቂ የሆነ ምላሽ ባለመስጠታቸው ምክኒያት ይህ ሂደት እነርሱ ላይ በተገቢው መልኩ አይሰራም።ስለዚህ ተገቢ የሆነ የስኳር በሽታ ህክምና ከሌለን እነዚህን በካርቦሃይድሬት የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ የደም የስኳር መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ያረጋሉ።
በሙዝ ውስጥ ምን ያህል ስኳር አለ?
አንድ መካከለኛ ሙዝ ማለትም ክብደቱ 126 ግራም አካባቢ የሆነ ሙዝ 29 ግራም ካርቦሃይድሬት እና 112 ግራም ካሎሪ በውስጡ ይይዛል። ካርቦሃይድሬቱም በስኳር ፣ በስታርች እና በፋይበር መልክ ይኖረዋል፤ 15 ግራም የሚሆንም ስኳር በውስጡ አለው።
ሙዝ በውስጡም የደም የስኳር መጠን ሊቀንስ የሚችለውን ፋይበር የተባለ ንጥረ ነገር ይይዛል። አንድ መካከለኛ ሙዝ ከስኳር እና ከስታርች በተጨማሪ 3 ግራም ፋይበር በውስጡ አለው። የስኳር በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም ሰው በጤናው ጠቀመታው ምክኒያት በቂ የሆነ ፋይበር አመጋገባቸው ውስጥ ሊያክሉ ይገባል።
ፋይበር የካርቦሃይድሬትን መፈጨት እና ወደ ሰውነት የመሰራጨት ሂደትን በማዘግየት የደም የስኳር መጠንን ይቀንሳል ይህም የስኳር በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ የደም የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ይረዳል። ካርቦሃይድሬት ያለው ምግብ በደም ዉስጥ ባለው የስኳር መጠን ላይ እንዴት ለውጥ እንደሚያመጣ ለማቅ የሚረዳን አንዱ መንገድ ግላይሴሚክ ኢንደክስ (glycemic Index) ነው።
ግላይሰሚክ ኢንደክስ (GI) ምግብ ከበላን ከ 2 ሰአት በሗላ የሚደረግ የደም የስኳር ልኪት ሲሆን ይህም ምግቦች በምንያክል መጠን እና በምን ያክል ፍጥነት የደም የስኳር መጠንን እንደሚጨምሩ ይመዝንልናል።
ግላይሴሚክ ኢንደክስ ከ 0 እስከ 100 ውጤት የሚሰጥ ሲሆን የሚከተሉት ምድቦች አሉት።
- ዝቅተኛ ግላይሴሚክ ኢንዴክስ ፦ 55 እና ከዚያ በታች ውጤት
- መካከለኛ ግላይሴሚክ ኢንደክስ ፦ ከ 56 እስከ 69 ውጤት
- ከፍተኛ ግላይሴሚክ ኢንደክስ ፦ ከ 70 እስከ 100 ውጤት
ዝቅተኛ ግላይሴሚክ ኢንደክስ ያላቸው ምግቦች ቀስ በቀስ ወደ ደም ስለሚሰራጩ የደም የስኳር መጠን ቶሎ እንዳይጨምር ሲረዱ በተቃራኒው መልኩ ከፍተኛ ግላይሴሚክ ኢንዴክስ ያለቸው ምግቦች ደግሞ ቶሎ ወደ ደም በመሰራጨት በፍጥነት የደም የስኳር መጠን እንዲጨምር ያደርጋሉ። ስለሆነም የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ዝቅተኛ ግላይሴሚክ ኢንደክስ ያላቸውን ምግቦች እዲመገቡ ይመከራል።
በአጠቃላይ ሙዝ ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ማለትም ከ 31 እስከ 62 ግላይሴሚክ ኢንዴክስ አለው። ይህም እንደ ብስለቱ ይወሰናል።
አረንጓዴ (ያልበሰለ) ሙዝ
አረንጓዴ ወይም ያልበሰለ ሙዝ አነስተኛ ስኳር እና የበለጠ ተከላካይ የሆነ ስታርች (resistant starch) በውስጡ ይይዛል። ተከላካይ ስታርች (resistant starch) የምንላቸው በላይኛው የምግብ መፍጫ ስርዓት ውስጥ መፈጨትን የሚቋቋሙ (የሚከላከሉ) ረዥም የግልኮስ ሰንሰለቶች ናቸው። ይህም ማለት ልክ እንደ ፋይበር የደም የስኳር መጠን እንዳይጨምር ይረዳሉ። እንዲሁም በሆድ ውስጥ ያሉትን ጠቃሚ ባክቴሪያዎች በመመገብ የምግብ የመፈጨትና ለሰውነት ጥቅም የማዋል ሂደትን እና የደም የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ሊረዱ ይችላሉ።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አረንጓዴ ወይም ያልበሰለ ሙዝ መመገብ በባዶ ሆድ የሚሰራውን የደም የስኳር መጠን እንደሚቀንስ እና በ አይነት 2 የስኳር በሽታ የሰውነት ህዋስ የሚታየውን ለኢንሱሊን ምላሽ አለመስጠትን እንደሚያሻሽል አሳይቷል። እንዲሁም የረሃብ ስሜትን በመቀነስ የሙሉነት ስሜት እንዲሰማን ይረዳል።
ሙዝ በደም ስኳር ላይ ያለው ተጽዕኖ እንደ ብስለቱ ይወሰናል።ቢጫ ወይም የበሰለ ሙዝ ከአረንጓዴ ሙዝ ያነሰ ተከላካይ የሆነ ስታርች እና እንዲሁም የበለጠ ስኳር የያዘ በመሆኑ ቶሎ የደም የስኳር መጠንን ይጨምራል።
የሙዝ መጠን
በሙዝ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በብስለቱ ብቻ የሚወሰን አይደለም። የሙዙ መጠን ተጽዕኖ አለው። ሙዝ ትልቅ በሆነ ቱጥር በውስጡ የሚይዘው የካርቦሃይድሬት መጠንም በዛው ልክ ይጨምራል። ይህም የደም የስኳር መጠን ላይ የበለጠ ተጽዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህም የምንበላውን የሙዝ መጠን መለካት የደም የስኳር መጠን ከመጠን በላይ እንዳይጨምር ይረዳል።
በአጠቃላይ፦
የስኳር በሽታ ካለብዎ እንደ ሙዝ ያሉ ፍራፍሬዎችን አመጋገቦ ላይ ማጠቃለል ለጤናዎ እጅግ ጠቃሚ ነው። በሚመገቡበት ጊዜ የሚከተሉትን ምክሮች መከተል በደምዎ የስኳር መጠን ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ይረዳዎታል።
- በአንድ ጊዜ የሚመገቡትን የስኳር መጠን ለመቀነስ ትንሽ ሙዝ ይምረጡ።
- በደንብ ያልበሰለ ሙዝ ይመገቡ።
- የምንመገባቸውን ፍራፍሬዎች በቀን ውስጥ አራርቆ መመገብ ይህም በአንድ ጊዜ ብዙ ስኳር እንዳይመገቡ እና የደም የስኳር መጠኖ ከፍ እንዳይል ይረዳል።
- ሙዝን እንደ ለውዝ እና እርጎ ካሉ ሌሎች ምግቦች ጋር አብረው ይመገቡ ይህም ስኳር ቶሎ እንዳይፈጭ እና ለሰውነት ጥቅም እንዳይውል በማድረግ የደም የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ያስችሎታል።


