የምግብ ትቦ ካንሰር (Esophageal cancer)

Elsabet Azezew
Aug 4, 2025
undefined

              የምግብ ትቦ ካንሰር (Esophageal cancer)

         የምግብ ትቦ(Esophagus) ምግብን ከአፍ ወደ ጨጓራ የሚወስድ 25 ሴ.ሜ እርዝማኔ ያለው ጡንቻማ ትቦ ነው። የምግብ ትቦ ካንሰር የምግብ ትቦ ውስጥ የሚገኙ ኖርማል ህዋሳት ወደ ያልተለመዱ ህዋሳት ሲቀየሩ እና ከቁጥጥር ውጪ ሲያድጉ የሚፈጠር ካንሰር ነው። የምግብ ትቦ እና ጨጓራ የሚገናኙበት ቦታ ጨምሮ ካንሰሩ (እጢው) በየትኛውም የትቦው እርዝማኔ ላይ ካንሰሩ ሊፈጠር ይችላል።

 

        የምግብ ትቦ ካንሰር በአለም በ 7ተኛው ደረጃ የሚከሰት ካንሰር ሲሆን በካንሰር ሞት መንስኤነቱም በ 6ተኛ ደረጃ ይጠቀሳል። በሃገራችን በኢትዮጵያም SAGE ጀርናል በ 2024 አጀንዳ እንዳወጣው መረጃ መሰረት በ 15ተኛ ደረጃ የሚከሰት ካንሰር እና 12ተኛ ደረጃ የሚጠቀስ የካንሰር ሞት መንስኤ ነው። በአርሲ እና ባሌ ክልሎችም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚታይ ጠቁማል። 

 

       ስኳመስ ሴል ካርሲኖማ እና አዲኖ ካርሲኖማ በዋነኝነት የሚፈጠሩ የምግብ ትቦ ካንሰር አይነቶች ሲሆኑ ስርኮማ፣ ስሞል ሴል ካርሲኖማ እና ሊንፎማ የተባሉ የካንሰር አይነቶች ደግሞ በአንጻራዊ ያልተለመዱ የካንሰሩ አይነቶች ናቸው።

 

        ስኳመስ ሴል ካርሲኖማ የምግብ ትቦ ግድግዳን የሚሸፍኑትን ቀጭን እና ጠፍጣፋ ስኳመስ ሴል የተባሉትን ህዋሳት የሚጎዳ ሲሆን በማንኛውም የምግብ ትቦ ክፍል ሊፈጠር ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን በላይኛው እና በመካከለኛው የምግብ ትቦ ክፍል ይፈጠራል። በአለም ዙርያ በዋነኛነት የሚታየው የምግብ ትቦ ካንሰር አይነትም ነው። 

  

        ከስኳመስ ሴል ካርሲኖማ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚታየው ካሰር ደግሞ አዲኖ ካርሲኖማ ነው።አዲኖ ካርሲኖማ እንዲፈጠር የምግብ ትቦ ውስጥ ያሉት ስኳመስ ህዋሳት ንፋጭ(mucus) ወደ ሚያመርቱ ኮለመናል ኢፒቴልየም ህዋሳት መቀየር አለባቸው። ይህም የጀርድ (የሆድ አሲድ ወደ ምግብ ትቦ መመለስ በሽታ) የጎንዮሽ ጉዳት በሆነው ባሬት ኢሶፈገስ ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚፈጠር ሁኔታ ነው። የሆድ አሲድ ከጨጓራ ወደ የምግብ ትቦ መመለስ ምግብ ትቦ ውስጥ ያሉት ህዋሳት ወደ ጨጓራ ውስጥ ወዳሉት ህዋሳት አይነት እንዲቀየር ያደርጋል። ይህንንም ባሬት ኢሶፋገስ የምንለው ሲሆን አዲኖ ካርሲኖማ የመፈጠር እድልን ከፍ ያደርጋል። አዲኖ ካርሲኖማ በብዛት በታችኛው የምግብ ትቦ ክፍል እና ጨጓራ እና የምግብ ትቦ የሚገናኙበት ቦታ (gastroesophageal Junction) ላይ ይፈጠራል። 

        ለምግብ ትቦ ካንሰር የሚያጋልጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

      አንዳንድ ሁኔታዎች በምግብ ትቦ ካንሰር የመያዝ እድልን ይጨምራሉ እነርሱም የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ

  • ሲጋራ ማጨስ
  • አልኮል መጠጣት 
  • የጀርድ በሽታ(የሆድ አሲድ ከጨጓራ ወደ የምግብ ትቦ መመለስ)
  • ባሬት ኤሶፈገስ (Barrett's esophagus)
  • የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ(HPV) ኢንፌክሽን
  • ከመጠን በላይ ውፍረት 
  • ቀደም ሲል የጨጓራ ቀዶ ጥገና ከተሰራልን እና
  • የአፍ ንፅህና ጉድለት ይጠቀሳሉ 

        ቀደም ሲል እንዳየነው በሃገራችን በኢትዮጵያ በአርሲ እና በባሌ ክልል አርሶ አደሮች ላይ የምግብ ትቦ ካንሰር በከፍተኛ ደረጃ የታየ ሲሆን ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአመጋገብ ባህላቸው ገንፎን የሚያጠቃልል መሆኑ እና ለረጅም ጊዜ ትኩስ ገንፎ መመገባቸው በሁለቱም ክልሎች ላለው ከፍተኛ የምግብ ትቦ ካንሰር አስተዋጽኦ እንዳልው ያስረዳሉ ።ከዚህም ጋር ተያይዞ ትኩስ ገንፎ የሚመገቡበት ፍጥነት እና ትኩስ ቡና መጠጣታቸው ለካንሰሩ የመጋለጥ እድላል ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርጉም ገልፀዋሉ።ይህም የሚሆነው በምግቡ ሙቀት ተፅዕኖ ምክንያት ሲሆን በምግብ ትቦ ውስጥ ያሉት ኖርማል ህዋሳት ወደ ያልተለመዱ ህዋሳት እና በኋላም ወደ ካንሰር እንዲቀየሩ ስለሚያደርግ ነው።

            የምግብ ትቦ ካንሰር ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

        የምግብ ትቦ ካንሰር ያለባቸው ሰዎች መጀመሪያ ላይ ምንም አይነት ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ካንሰሩ እየተሰራጨ ሲሄድ ግን አንድ ሰው ሊያስተውላቸው ከሚችል ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ ፦

 

  • ለመዋጥ መቸገር ወይም በሚውጡበት ጊዜ ህመም መኖር
  • የደረት ህመም
  • የድምጽ መጎርነን
  • ክብደት መቀነስ
  • ማስታወክ
  • በምግብ ትቦ ውስጥ ደም መፍሰስ ይህም ሰገራ ላይ ጥቁር ደም እንዲታይ ያረጋል
  • ድካም
  • የምግብ መፈጨት ችግር
  • ካንሰሩ ወደሌላ የሰውነት ክፍል ከተሰራጨ እንደ አንጀት ህመም ያሉ ምልክቶችም ሊኖሩን ይችላሉ።

             የምግብ ትቦ ካንሰር ምርመራ ምን ይመስል ?

          የምግብ ትቦ ካንሰር ምርመራ የሚከተሉትን ሊያጠቃልል ይችላል

  • ኢንዶስኮፒ:-ሓኪማችን በቀጭን ካሜራ በመታገዝ የምግብ ትባ ግድግዳ ላይ መቆጣት እና ያልተለመዱ ለውጦች መኖራቸውን ያይልናል።በምርመራው ያልተለመደ ህዋስ ከተገግኘም ናሙና ለመውሰድ ያስችለዋል ።
  • ባርየም ስዋሎ ምርመራ፦ ይህ ምርመራ የ x-ray ምርመራ አይነት ሲሆን ባሪየም የተባለ ኬሚካል እንድንውጥ ከተደረገ በኃላ ምስሉ ይወሰዳል።ሓኪማችን የምግብ ትቦ ግድግዳ ላይ ያለን ማንኛውም ለውጥ ለማየት ያስችለዋል ።
  • የናሙና ምርመራ(ባዮፕሲ)፡-ሓኪማችን በኢንዶስኮፒ ታግዞ የወሰደውን ያልተለመደ ህዋስ ናሙና በላብራቶሪ የሚመረምርበት ሂደት ነው።
  • ሲቲ ስካን(CT Scan) እና ኤም አር አይ (MRI) ምርመራ:-ካንሰሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች መሰራጨቱን ለመለየት ያስችለናል።

              የምግብ ትቦ ካንሰር ደረጃ 

          የምግብ ትቦ ካንሰር ደረጃ ምድብ በጣም ውስብስብ ሲሆን እንደ ካንስሩ አይነት፣ የካንሰሩ ወደ ሌላ ክፍል መሰራጨት እና እንደ እድገቱ ፍጥነት ይወሰናል። የምግብ ትቦ ካንሰር ህክምና እና የመዳን እድል በደረጃወቹ ይወሰናል። ደረጃዎቹም የሚከተሉትን ይመስላል

  • ደረጃ 0 - ካንሰሩ የምግብን ትቦ ግድግዳ ብቻ የሚጎዳ ከሆነ
  • ደረጃ 1- ካንሰሩ የምግብ ትቦ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እያደገ ከሆነ ነገር ግን ወደ ፍርንትት ካልተሰራጨ ደረጃ 1 እንለዋለን
  • ደረጃ 2- ካንሰሩ ወደ የምግብ ትቦ እና ፍርንትት (lymph node) ከተሰራጨ
  • ደረጃ 3- ካንሰሩ የምግብ ትቦን፣ ፍርንትትን እና የምግብ ትቦ አካባቢ ያሉ ህዋሳትን የሚጎዳ ከሆነ
  • ደረጃ 4- ካንሰሩ ከምግብ ትቦ ርቀው የሚገኙ እንደ ሳንባ እና ጉበት ወዳሉ የሰውነት ክፍሎች ሲሰራጭ

 

              የምግብ ትቦ ካንሰር ህክምና

        ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የምግብ ትቦ ካንሰር ህክምና በካንሰሩ ደረጃ የሚወሰን ሲሆን የሚከተሉትን የህክምና አማራጮችም ያጠቃልላል 

 

  • የቀዶ ህክምና- ካንሰሩ ትንሽ ከሆነ እና ወደሌላ የሰውነት ክፍል ካልተሰራጨ ሓኪማችን ኢንዶስኮፒን በመጠቀም ትንሽ ቀዳዳ በመፍጠር እጢውን ሊያስወግድልን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትልቅ ቀዶ ጥገና በማድረግ ሓኪማችን የተጎዳውን የምግብ ትቦ ክፍል እና አካባቢው ላይ ያለውን ፍርንትት ሊያስወግድ ይችላል። እንዲሁም የጠጓራን የላይኛውን ክፍል ማስወገድ የሚኖርበት አጋጣሚም አለ።
  • ኬሞተራፒ (chemotherapy)- ይህ አይነቱ ህክምና መድሃኒቶችን በመጠቀም የካንሰር ህዋሳትን የሚያጠቃ ሲሆን ከቀዶ ጥገና በፊት ወይም ቦሃላ ሊሰጥ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ከጨረር ህክምና ጎን ለጎን ሊታዘዝም ይችላል።
  • የጨረር ህክምና (radiation therapy) - ይህ ህክምና ጨረርን በመጠቀም የካንሰር ህዋሳትን ይገድላል።

 

Comments (0)