የፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዝ (Perianal Abscess)

Biruh Tesfaye
Jul 8, 2025
undefined

ይህ በሽታ የሚከስተው በፊንጢጣ አካባቢ የሚገኙ አመንጪ እጢዎች ሲደፈኑ በውስጣቸው ያለው ፈሳሽ መውጣት ስለሚያቅተው በውስጡ ባክቴሪያ ይራባል። እነዚህም ባክቴሪያዎች ኢንፌክሽን ይፈጥራሉ ። ይህም በፊንጢጣ አካባቢ መግል የያዘና ከፍተኛ ህመም ያለው እብጠት እንዲከሰት ያደርጋል። 

 

ለፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዝ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?

ለፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዝ ተጋላጭ የሆኑት የሚከተሉት ናቸው

  • የአንጀት ቁስለት በሽታ (IBD ) ያለባቸው
  • በተለያዩ ምክንያቶች የበሽታ መከላከል አቅማቸው የወረደ ( ለምሳሌ የስኳር በሽታ  ፣ የኤች. ኣይ ቪ ኤድስ ተጠቂዎች ፣ የበሽታ መከላከል አቅም የሚያዳክሙ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች )
  • ሲጋራ የሚያጨሱ
  • የእንጀት ካንሰር ያለባቸው
  • በፊንጢጣ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው እና
  • አንዳንድ የአባላዘር በሽታ ተጠቂዎች ለፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዝ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው ። 

የፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዣ ምን አይነት ምልክቶች አሉት?

  • በፊንጢጣ አካባቢ ከባድ ህመም መሰማት- ህመሙ ቋሚ ሲሆን ሰገራ በሚወጣበት ጊዜ ሊብስ ይችላል
  • በፊንጢጣ አካባቢ እብጠት መኖር- ይህ እብጠት የመቅላት እና ሲነካ ወደ ውስጥ ገባ የማለት ባህሪ አለው። 
  • መግል መፍሰስ-ቁስሉ በራሱ ከተፈታ ከአካባቢው የሚወጣ ቢጫ ወይም አረንጓዴ ፈሳሽ/መግል ሊኖር ይችላል። 
  • ከቁስሉ ደም መፍሰስ
  • የሰገራ መድረቅ- ይህ በብዛት የሚፈጠረው ሰገራ በሚወጣ ጊዜ በሚከሰት ህመም ምክንያት ነው።
  • በፊንጢጣ አካባቢ ማሳከክ
  • ትኩሳት እና የድካም ሰሜት- በሽታው እየባሰ ሲመጣ ትኩሳት እና የድካም ሰሜት ይኖራል። 

ለፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዣ የምናደርጋቸው ምርመራዎች ምን ምን ናቸው?

የፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዝ ዋነኛ ምርመራ ሐኪሞ ፊንጢጣ አካባቢን በመመልከት እና ዲጂታል ሬክታል ( በጣት ፊንጢጣን እና የፊንጢጣ አካባቢን መመርመር) ምርመራን በማድረግ ነው። 

 

ፊንጢጣ አካባቢ መግል ያለባቸውን ታካሚዎች ለመመርመር የተለዩ የላቦራቶሪ ምርመራዎች አያስፈልጉም። ነገር ግን እንደ ተጨማሪ ምርምራ ወይም ለስኳር ህመምተኞች እና የበሽታ የመከላከል አቅማቸው ለተዳከመባቸው ታካሚዎች የላቦራቶሪ የደም ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላል። 

 

አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን (CT scan) ወይም ኤምአርአይ (MRI) የመሳሰሉ ምርመራዎች ጥልቀት ያላቸውን ቁስሎች ለመመርመር እና የፊስቱላ መተላለፊያዎች መፈጠራቸውን ለማየት ሐኪሞ  ይጠቀምባቸዋል። ኮሎኖስኮፒ (Colonoscopy): ካሜራ እና ብርሃን ያለበት ተጣጣፊ ቱቦ በመጠቀም ትልቁን አንጀትዎን ለመመርመር ይጠቅማል። ይህ አሰራር እንደ የአንጀት ቁስለት በሽታ (IBD) ያሉ ሌሎች ሁኔታዎችን ለመመርመር ሊደረግ ይችላል።

 

የፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዣ በምን ይታከማል?

የፊንጢጣ አካባቢ መግል መያዣ በዋነኝነት የሚታከመው በቀዶ ህክምና ነው (incision and drainage)። ይህም ቀዶ ህክምና ማደንዘዣ ከተሰጠ በኋላ የሚሰራ ሲሆን ሐኪሞ ፊንጢጣ አካባቢን ብቻ በማደንዘዝ ወይም ሙሉ ማደንዘዣ  ከሰጥ በኋላ እብጠቱ ላይ ትንሽ ቀዳዳ በመፍጠር መግሉን ያፈሰዋል። ከቀዶ ህክምናው በኋላ የማገገሚያ ጊዜ ከ3 እስከ 4 ሳምንታት የሚወስድ ሲሆን አንዳንዴ ግን እስከ 8 ሳምንት ሊወስድ ይችላል። 

 

ይህ በሽታ በመድኃኒት ብቻ ሊታከም አይችልም።  የቀዶ ህክምናው በዘገየ ቁጥር የኢንፌክሽን መባባስ፣ ጋንግርን፣ ይሰገራ ማምለጥ እና ፊስቱላ የመፈጠር እድሉ ይጨምራል። 

 

ከቀዶ ጥገና ህክምና በኋላ ምን ሊታዘዝ ይችላል?

ከቀዶ ጥገና ህክምና በኋላ ሐኪሞ የሚከተሉትን ሊያዝሎት ይችላል፡

  • የህመም ማስታገሻ መድኃኒት (antipain)
  • የሰገራ ማለስለሻ መድኃኒት
  • የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት (antibiotic) 
  • ሲትዝ ባዝ (Sitz bath)- ንጹህ መዘፍዘፍያ ወይም ገላ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ለብ ያለ ውሃ ካደረጉ በኃላ ጨው ወይም ሌሎች ሐኪሞ የሚመክሮትን ነገሮችን በመጨመር (ጨው ባይኖረውም ችግር የለውም) ለ10-20 ደቂቃዎች ያህል በውስጡ ይዘፍዘፉ። ከጨረሱም በኋላ በፎጣ ቀስ ብለው ያድርቁት። 

     

 

Comments (3)

Muna Yitaktu
Jul 9, 2025

Thank you Dr. This is really helpful.

Al Amin Worku
Jul 8, 2025

thanks doc

Melat Geatchew
Jul 8, 2025

Thanks you doc 👌👌👌👌