የአስም በሽታ

Asteraye Belay
Aug 4, 2025
undefined

የአስም በሽታ እየተደጋገመ የሚመጣ፣ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ፣ የመተንፈሻ ቱቦ እና የሳምባ ሕመም ነው።  በሽታው የአየር ቱቦዎችን በማጥበብና በማስቆጣት መተንፈስን ከባድ ያደርገዋል፡፡ 

የአስም በሽታ በበለፀጉት አገራት የበለጠ ቢከሠትም፤ አሁን አሁን ግን በታዳጊ አገሮችም እየጨመረ ይገኛል።

በዓለማችን 10 - 12% የሚሆኑት ጎልማሳዎችና እና 15% የሚሆኑት ሕፃናት  በዚህ በሽታ ይጠቃሉ። ወንዶች ሕፃናት ከሴት ሕፃናት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። በወጣቶች ላይ ግን ሁለቱም እኩል ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ዕድሜያቸው ከ 40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ይጠቃሉ።

ለአስም በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

●         በቤተሰብ የአስም ሕመም ከአለ፤

●        በልጆች ላይ  የቆዳ ወይም ማንኛውም ዓይነት የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ከአለ ፤

●        ታማሚው  አዋቂ ከሆነ ደግሞ በልጅነት ጊዜ ማንኛውም ዓይነት የአለርጂ ችግር ከነበረ፤

●        የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ከነበረ፤

●        ከመጠን ያለፈ ውፍረት

●        ሲጋራ ማጨስ ወይም ተገብሮ ማጨስ (passive smoking)

●        የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን

የአስም በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የአስም ምልክቶች ቀላል ወይም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ቢሆንም የአስም ምልክቶች በድንገት ጀምረው እስከ ሞት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡

●        በሚተነፍሱበት ወቅት ሲር ሲር የሚል ድምፅ ማሰማት፤

●        ሳል (በተለይም ምሽት ላይ)

●        በደረት አካባቢ የመጨነቅ ስሜት 

●        ትንፋሽ ማጠር

ምልክቶቹ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ ወይም ከዚህም ባነሰ ጊዜ ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡ 

የአስም በሽታ ምርመራዎች

ከላይ የተጠቀሱት  ምልክቶች  እንዳሉ ሆነው በተጨማሪም ሪስፓይሮሜትር (የመተንፈሻ መለኪያ) ምርመራ ይደረጋል፡፡ ይህም የሳምባን የመተንፈስ ዐቅም የሚለካ እና የአለርጂ ችግር ከአለም  ምርመራ የሚደረግበት ነው፡፡።

የአስም በሽታ እንዴት ይታከማል?

ሕክምናው ከሥር የተጠቀሱትን ሁለት ነገሮች መሠረት ያደረገ ይሆናል።

●        ምልክቶቹ  በየስንት ጊዜው ይከሠታሉ?

●        ምን ያህል ከባድ ናቸው?

  1. የፈጣን - እፎይታ መድኃኒቶች (quick relief medicines)፡- እነዚህ በአፍ የሚነፉ መድኃኒቶች የአስም ምልክቶች በሚከሠቱበት ጊዜ ሁሉ ይወሰዳሉ። መድኃኒቶቹ ለመሥራት የሚወስድባቸው  ጊዜ ከ 5 - 15 ደቂቃ ሲሆን፤ በፍጥነት ፋታ በመስጠት ምልክቶቹን የሚያስታግሱ ናቸው።
  2. የረጅም ጊዜ ማስታገሻ (long term controllers) መድኃኒቶች፡- እነዚህ መድኃኒቶች ቶሎ ለውጥ ባያሳዩም የአስም በሽታን በመቆጣጠር ወደፊት ምልክቶቹ እንዳይከሠቱ ይከላከላሉ። ስለዚህ መድኃኒቱን ሳያቋርጡ መውሰድ  ያስፈልጋል። በሳምንት ውስጥ ከ ሁለት ጊዜ በላይ የአስም በሽታ ምልክቶች የሚታዩባቸው ሰዎች፤ በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ የመቆጣጠሪያ መድኃኒት መጠቀም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

በአጠቃላይ የአስምን በሽታ ለመቆጣጠር የሚከተሉትን መተግበር ያስፈልጋል።

●   በሕክምና ተቋም ውስጥ በመደበኛነት ክትትል ማድረግ

●   ክትትሉ በየ1 - 6 ወር ሊሆን ይችላል፡፡ በክትትሉ ወቅትም የጤና ባለሙያው ፣ ስለመድኃኒቶቹና አጠቃቀማቸው በሚገባ ያስረዳል፡፡ ማለትም  የአስም ታማሚዎች በቤት ውስጥ በየቀኑ የሚጠቀሙባቸው የትኞቹ መድኃኒቶች እንደሆኑ፣ምልክቶች እየባሱ ከሄዱ የትኞቹን መድኃኒቶች መውሰድ እንደአለባቸው፣ በሽታውን የሚያስነሡትን ሁኔታዎች ስለመቆጣጠር ጨምሮ ትምህርት ይሰጣል። 

በተጨማሪ በሕመሙ  ምልክቶች እና በሳምባ ምርመራ ውጤቶች መሠረት መድኃኒቶች ይስተካከላሉ።

Comments (0)