ሳንባ ላይ ደም መርጋት (Pulmonary Embolism) የሚከሰተው የደም መርጋት በሳንባዎ ውስጥ ያለን የደም ቧንቧ ሲዘጋ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የደም መርጋት የሚጀምረው በእግር ውስጥ ባለ የደም ሥር ውስጥ ሲሆን ከዚያም ወደ ሳንባ ይጓዛል። አልፎ አልፎ፣ የደም መርጋቱ በሰውነት ውስጥ ባሉ ሌሎች የደም ሥሮች ውስጥ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልታከመ የልብ ወይም የሳንባ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል።
ለሳንባ ውስጥ ደም መርጋት ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?
የደም መርጋት በሳንባ ውስጥ (pulmonary embolism) የመጋለጥ እድልን የሚጨምሩ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው።
- ለረጅም ጊዜ እንቅስቃሴ አልማድረግ (ለምሳሌ ለረጅም ጊዜ በአልጋ ላይ መቆየት፣ ረጅም ርቀት በአውሮፕላን ወይም በመኪና መጓዝ)
- በቅርቡ በደም ሥር ላይ ጉዳት ወይም አደጋ የደረሰባቸው (ለምሳሌ ከቀዶ ጥገና ወይም ከአጥንት ስብራት የተነሳ)
- በሆርሞን ላይ የተመሠረተ የወሊድ መቆጣጠሪያ ወይም የኢስትሮጅን ምትክ ሕክምና መጠቀም
- የደም መርጋት ችግር ያለባቸው ወይም ከዚህ በፊት የደም መርጋት አጋጥሞ ከነበረ
- በቤተሰብ ውስጥ የደም መርጋት ታሪክ ያለባቸው
- ሲጋራ ማጨስ
- የስኳር ህመም ያለባቸው
- የእድሜ መጨመር
- ከመጠን በላይ ክብደት ወይም ውፍረት መኖር
- እርጉዝ የሆኑ ወይም ባለፉት ስድስት ሳምንታት የወለዱ
- በእጃቸው ወይም በእግራቸው በኩል ማዕከላዊ የደም ሥር ካቴተር (central venous catheter) የተገጠመላቸው
- የካንሰር፣ የልብ ድካም፣ የሳንባ በሽታ (COPD)፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ በእግሮች ላይ ያበጡ ደም ስሮች (varicose veins) ስትሮክ እና የአንጀት እብጠት በሽታ መኖር
የሳንባ ውስጥ ደም መርጋት ምን አይነት ምልክቶች አሉት?
የሳንባ ውስጥ ደም መርጋት የተለያዩ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። ከእነዚህም ውስጥ በብዛት የሚታዩት የሚከተሉት ናቸው።
- የትንፋሽ ማጠር
- የደረት ህመም በተለይ በጥልቀት ሲተነፍሱ፣ ሲያስሉ ወይም ወደፊት ሲደገፉ ህመሙ ሊብስ ይችላል
- ራስን መሳት፦ ይህ የሚከሰተው የደም ግፊትዎ በድንገት ሲቀንስ ነው
ሌሎች ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ደም የቀላቀለ አክታ ያለው ሳል
- የተዛባ ወይም ፈጣን የልብ ምት
- ማላብ
- ማዞር
- ትኩሳት
- የቀዘቀዘ ቆዳ ወይም የቆዳ ቀለም ወደ ሰማያዊ መለወጥ
- የእግር ህመም ወይም እብጠት
- ትንፋሽ ሲወስዱ የሚሰማ ጩኸት (wheezing)
የሳንባ ውስጥ ደም መርጋት እንዴት ይታወቃል?
የሳንባ ውስጥ ደም መርጋት ለመመርመር ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ምልክቶቹ ከብዙ ሌሎች የጤና እክሎች እና በሽታዎች ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት ስላላቸው ነው።
አንድ የጤና ባለሙያ የሳንባ ውስጥ ደም መርጋትን ከጠረጠረ የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያዝ ይችላል፦
- የደም ኦክሲጅን መጠንዎን ለመፈተሽ በጣትዎ ጫፍ ላይ የሚሰካ የልብ ምት ኦክስሜትር (pulse oximeter) ሊደረግሎት ይችላል።
- የደም ምርመራዎች- ደም በቀላሉ የመርጋት ሁኔታውን ለማጣራት ይጠቅማሉ ከነዚህም አንዱ ዲ-ዳይመር የተባለ የደም መርጋት ደረጃ መለኪያ ምርመራ ነው
- ሲቲ አንጂዮግራም-በዚህ ምርመራ ወቅት በደም ስር የሳንባ የደም ስሮችን ግልጽ ሆነው እንዲታዩ ይረዳል። በተጨማሪም በሳንባዎ የደም ስሮች ውስጥ ያሉ ለውጦችን ያሳያል።
- የእግር አልትራሳውንድ- ይህ በእግር ላይ ያሉ የደም መርጋቶችን መኖራችሀውን ለማወቅ ይረዳል።
- ኢኮካርዲዮግራም (የልብ ምርመራ ማሽን)- ትናንሽ ተለጣፊ ፕላስተሮች በደረት፣ ክንዶች እና እግሮች ላይ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ይቀመጡና የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ይለካሉ
- የደረት/ የሳንባ ራጅ
ከነዚህም በተጨማሪ ቬንትሌሽን ፐርፊውዥን ስካን (V/Q scan)፣ የሳንባ አንጂኦግራፊ እና እም.አር.አይ የሳንባ አንጂኦግራፊ የሚባሉ ምርመራዎች አሉ።
የሳንባ ውስጥ ደም መርጋት በምን ይታከማል?
የሳንባ ውስጥ ደም መርጋት ዋናው ህክምና የደም ማቅጠኛ (anticoagulant) ነው። የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች (Anticoagulants) ደምዎ የመርጋት አቅሙን ይቀንሳሉ። ይህ ወደፊት የደም መርጋት እንዳይፈጠር ይከላከላል። ልክ እንደ ማንኛውም መድሃኒት፣ የደም ማቅጠኛ መድሃኒትዎን እንዴት እና መቼ መውሰድ እንዳለብዎ መረዳትና የሐኪምዎን መመሪያዎች መከተል አስፈላጊ ነው። የደም ማቅጠኛ መድሃኒት በሚወስዱበት ጊዜ፣ የደምዎ የመርጋት ፍጥነትን ለማየት ተደጋጋሚ የደም ምርመራዎች (prothrombin time test) ሊደረግልዎ ይችላል። ይህ ሐኪምዎ ትክክለኛውን መጠን እየወሰዱ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳል።
መድሃኒቱን ለጥቂት ወራት መውሰድ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ሰውነትዎ የቆየውን የረጋ ደም ለማሟሟት ጊዜ ይሰጠዋል። በተጨማሪም፣ የረጋ ደም ያለባቸው ሰዎች በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ሌላ የረጋ ደም የመፍጠር ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ይህን ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ህመሙ በጣም አደገኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ ፣ የቀዶ ጥገና ሐኪም በቀጭን ቱቦ በመጠቀም የደም መርጋትን ከሳንባዎ ሊያስወግድ ይችላል። ይህ ቱቦ በደም ሥሮች በኩል ይገባል። ይህ አብዛኛውን ጊዜ የሚደረገው ሕይወትን በሚያሰጉ ሁኔታዎች ላይ ብቻ ነው።


