የባሕርይ/የስበዕና መዛባት (Personality Disorder)

Biruh Tesfaye
Aug 22, 2025
undefined

ሰዎች ልዩ እና ውስብስብ የሆኑ የባሕርይ ስብስቦች አሏቸው። የባሕርይ መገለጫዎች (personality traits) ሰዎች በዙሪያቸው ያለውን ዓለም እንዴት እንደሚረዱት፣ ከሌሎች ጋር እንዴት እንደሚነጋገሩ፣ እንዲሁም ራሳቸውን እንዴት እንደሚያዩ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ።

የባሕርይ/የስበዕና መዛባት የሚከሰተው አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ከሚጠበቀው መደበኛ ባህል እና አኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የሚለይ ባህሪ እና ውስጣዊ ልምድ ሲኖረው ነው። በአብዛኛው በጉርምስና ዕድሜ ወይም በወጣትነት ጊዜ ነው የሚጀምረው። የስብዕና መታወክ ያለባቸው ሰዎች ስሜቶችን ለመረዳትና ጭንቀትን ለመቋቋም ይቸገራሉ። እንዲሁም ያለማሰብ ድንገተኛ እርምጃ ይወስዳሉ። ይህም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስቸጋሪ ያደርገዋል፣ ከባድ ችግሮችን ይፈጥራል፣ እንዲሁም የቤተሰብ ህይወታቸውን፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን፣ የሥራ እና የትምህርት አፈጻጸማቸውን፣ እና አጠቃላይ የህይወታቸው ላይ ተጸኖ ያሳድራል።

የስብዕና መታወክ ምክንያቶች

የስብዕና መታወኮች መንስኤያቸው በትክክል ባይታወቅም፣ ሳይንቲስቶች መንስኤዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚያምኑባቸው አንዳንድ ምክንያቶች አሉ። እነዚህም

  • ዘረመል (Genetics)
  • የአንጎል/የአእምሮ ለውጦች: በአንዳንድ የስብዕና መታወኮች ውስጥ በአንጎል ውስጥ ስውር ልዩነቶች እንዳሉ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። 
  • በልጅነት የደረሱ የስሜት ቀውስ/ትራውማ (Childhood trauma): ለምሳሌ፣ የቦርደርላይን ስብዕና መታወክ ያለባቸው ሰዎች በልጅነት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸዋል። 
  • የቃል ጥቃት (Verbal abuse): በልጅነታቸው የቃል ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች በአዋቂነት ጊዜ ቦርደርላይን፣ ናርሲሲስቲክ፣ ኦብሴሲቭ ኮምፐልሲቭ ወይም ፓራኖይድ ስብዕና መታወክ ሊያጋጥማቸው የሚችለው ዕድል ሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ አንድ ጥናት አሳይቷል።
  • ባህላዊ ምክንያቶች: በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚታዩት የስብዕና መታወኮች መጠን ልዩነት፣ የባህል ምክንያቶች ተጽእኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ያሳያል።

የስብዕና መታወክ እንዴት ይታወቃል?

የስብዕና መታወኮችን በትክክል መመርመር ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ይህ የሆነበት ምክንያት፣ ብዙውን ጊዜ ችግር አለባቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በባህሪያቸው ወይም በአስተሳሰባቸው ላይ ችግር እንዳለ አያምኑም። ባህሪያቸው በሌሎች ሰዎች ላይ ችግር ሲፈጥር፣ የቅርብ ዘመዶቻቸው ወይም ጓደኞች ወደ የአእምሮ ጤና ባለሙያ ሊመሯቸው ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ እርዳታ የሚፈልጉበት ዋና ምክንያት የስብዕና መታወኩ ራሱ ሳይሆን፣ እንደ ጭንቀት፣ ድብርት ወይም የሱስ ችግር ባሉ ሌሎች የጤና እክሎች እንዲሁም በትዳር መፍረስ ወይም ሥራ ማጣት ባሉ ችግሮች ምክንያት ነው። 

የጤና ባለሙያዎች የስብዕና መታወክን ለመመርመር በሚታተመው "የአእምሮ ሕመሞች ምርመራ እና ስታትስቲክስ ማኑዋል" (Diagnostic and Statistical Manual of Mental Disorders) በተሰጠው መመሪያ ላይ ይመረኮዛሉ። የሥነ-አእምሮ ባለሙያ ወይም የሥነ-ልቦና ባለሙያ አንድ ሰው የስብዕና መታወክ አለበት ብለው ሲጠረጥሩ ስለ የተለያዩ ጉዳዮች ሰፊና አጠቃላይ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። 

የስብዕና መታወክ እንዴት ይታከማል?

የስብዕና መታወኮች ለማከም አብዛኛውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት እነዚህ አስተሳሰቦች በሰውየው ማንነት እና ባህሪ ላይ ለረጅም ጊዜ የተሠሩ በመሆናቸው ነው። እነዚህን የተዛቡ አስተሳሰቦችና ባህርያት ለማስተካከል ደግሞ የረጅም ጊዜ ትኩረትና ሕክምና ያስፈልጋል። 

የስብዕና መታወክ ዋነኛው የህክምና ዘዴ የንግግር ሕክምና ወይም ሳይኮቴራፒ (psychotherapy) ነው።  የሳይኮቴራፒ ዋና ግቦች፤ ጭንቀትን እና ድብርት መቀነስ፣ ችግሮቹ የውስጥ እንጂ የውጭ አለመሆናቸውን መረዳት፣ ጤናማ ያልሆነ እና የማይፈለግ ባህሪን መቀነስ እና ችግር የሚፈጥሩትን የስብዕና ባህሪያት መቀየር ነው።

የስብዕና መታወኮችን በቀጥታ ለማከም ተብለው የተሠሩ መድሃኒቶች ባይኖሩም፣ አንዳንድ ጊዜ እንደ የድባቴ መከላከያዎች (antidepressants)፣ የጭንቀት መከላከያዎች (anti-anxiety medication) ወይም ስሜትን ማረጋጊያዎች (mood-stabilizing medication) የመሳሰሉ መድሃኒቶች የተወሰኑ ምልክቶችን ለማከም ሊረዱ ይችላሉ።

 

Comments (0)