የሕፃናትን ጥርስ መቼ መቦረሽ እንጀምር?🦷
እንደ ወላጅ ለልጅዎ ህይወት ምርጡን ጅማሮ በጤናማ ልምዶች ፣ ጥሩ አመጋገብ እና የሚያብረቀርቅ ፈገግታ መስጠት ይፈልጋሉ። እንደ ወላጅ ከሚያጋጥሙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው “የመጀመሪያዎች” ውስጥ የመጀመሪያ ፈገግታ፣ የመጀመሪያ እርምጃ እና የመጀመሪያ ጥርስ የተወሰኑት ናቸው። አብዛኛዎቹ አዳዲስ ወላጆች ከሚጠይቋቸው በጣም የተለመዱ ጥያቄዎች አንዱ "የልጄን ጥርስ መቦረሽ የምጀምረው መቼ ነው?" የሚለው ጥያቄ ነው። አጭር መልስ? የመጀመሪያው ጥርስ እንደታየ! እንደ እውነቱ ከሆነ, የልጅዎን የአፍ ጤንነት ከልጅነት ጊዜ ጀምሮ መንከባከብ ጥሩ ልምዶችን እና ጤናማ ጥርሶችን ይሰጣል። ጥርስ መቦረሽ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ እና ልጆችን እንዴት በትክክል እንደሚቦርሹ በዚህ ጽሁፍ እንይ።
የሕፃናትን ጥርስ መቦረሽ አስፈላጊ ነው?
የሕፃናት የመጀመሪያ ጥርስ የወተት ጥርስ በመባልም የሚታወቅ ሲሆን ጊዜያዊ ቢሆንም በልጅዎ እድገት ውስጥ ትልቅ ሚናን ይጫወታል። ልጅዎ የሚከተሉትን እንዲያከናውን ይረዳሉ፡-
- ምግብን በትክክል ለማኘክ እንዲችሉ
- ግልፅ ንግግርን ለመለማመድ
- ለአዋቂዎች ጥርሶች ቦታ ይዞ ለማመቻቸት
- ለውብ ፈገግታ
ምንም እንኳን የወተት ጥርስ ውሎ አድሮ የሚወልቅ ቢሆንም የዕድሜ ልክ ጤናማ ልምምዶችን ለመገንባት ይረዳል።
የሕፃን ጥርሶች መቼ ይበቅላሉ?
አብዛኞቹ ሕፃናት ከ6 እስከ 12 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ጥርሳቸውን ማብቀል ይጀምራሉ። ነገር ግን አንዳንድ ሕፃናት ትንሽ ቀደም ብለው ወይም ዘግይተው ጥርስ መውጣት ሊጀምሩ ሲችሉ የተለመደ ሁኔታ ነው። ብዙውን ጊዜ የታችኛው የፊት ጥርሶች መጀመሪያ ላይ ሲበቅሉ የላይኛው የፊት ጥርሶች ይከተላሉ።
መቦረሽ መጀመር ያለብዎት መቼ ነው?
የአሜሪካ የጥርስ ህክምና ማህበር ልክ የመጀመሪያው የልጅዎ ጥርስ እንደመጣ መቦረሽ እንዲጀምሩ ይመክራል። ምንም እንኳን እነዚህ የህፃን ጥርሶች ትንንሽ እና ለጉድጓድ የተጋለጡ ባይሆኑም ባክቴሪያ ሊያከማቹ ስለሚችሉ ከመጀመሪያ ማጽዳት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ልጅዎ የመጀመሪያ ጥርሱን ከማብቀሉ በፊት ድዱን በለስላሳ እና ንጹህ ማጠቢያ ማጽዳት ይችላሉ። ልጅዎ የመጀመሪያውን ጥርስ ካበቀለ በኋላ ደግሞ ለስላሳ የህፃን የጥርስ ብሩሽ እና ትንሽ የፍሎራይድ የጥርስ ሳሙና በመጠቀም ከምግብ ጋር የሚገናኙትን የጥርስ ንጣፎች በትንሽ ክብ እንቅስቃሴዎች በቀስታ ይቦርሹ።
የሕፃናትን ጥርስ መቦረሽ ጥቅም
የወተት ጥርሶች በመጨረሻ የሚወልቁ ከሆነ ለምን መቦረሽ እንደሚያስፈልግ ሊያስቡ ይችላሉ። መቦረሽ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እነሆ፡-
መቦርቦርን ይከላከላል፡- ስኳር (ከጡት ወተት፣ ፎርሙላ፣ ጭማቂ ወይም መክሰስ) በአፍ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በህጻናት ጥርሶች ውስጥ መቦርቦር፣ ኢንፌክሽን እና ህመም ሊያመጣ ይችላል። ይህም የልጅዎን በአግባቡ የመመገብ ወይም የመናገር ችሎታን ስለሚጎዳ መልካም ልማዶችን ማሳደግ እና የመቦረሽ ልምድን ቀደም ብሎ መጀመር ልጅዎ ጥርሱን የመቦረሽ ሀሳብን እንዲለማመድ እና እስከ አዋቂነት ድረስ የሚዘልቅ አወንታዊ የጥርስ ንፅህና ልማዶችን እንዲፈጥር ያስችላል። የሕፃን ጥርሶች አቀማመጥ ለአዋቂ ጥርሶች ማስቀመጫ ቦታ ሆነው ያገለግላሉ። የሕፃን ጥርስ ከተቦረቦረ ወይም ያለጊዜው ከተነቀለ የአዋቂ ጥርሶች ቀጣይ አበቃቀል ላይ ችግር በመፍጠር ወደ አለመመጣጠን ወይም ሌሎች የጥርስ ችግሮች ያመራል።
እንዴት ይቦርሹ?
የልጅዎን ጥርስ ለመቦረሽ ቀላል ምክሮች እነሆ፡-
- ትክክለኛውን የጥርስ ብሩሽ ይጠቀሙ፡- የሕፃን መጠን ያለው ለስላሳ የጥርስ ብሩሽ ለማጽዳት ተስማሚ ሲሆን ለንንሽ ሕፃናት በተለየ ሁኔታ የተዘጋጁ የጥርስ ብሩሾችን ማግኘት ይችላሉ።
- ትንሽ የጥርስ ሳሙና ይጠቀሙ፡- ትንሽ (የሩዝ መጠን ያለው) የፍሎራይድ የጥርስ ሳሙናን መጠቀም የጥርስ መቦርቦርን ለመከላከል ይረዳል። ነገር ግን ህጻናቱ በጣም ብዙ ሳሙናን ከዋጡ ጎጂ ሊሆን ስለሚችል በሚያጸዱበት ጊዜ ልጅዎን በደንብ ይቆጣጠሩ።
- ሃይል አያብዙ፡- የልጆች ድድ ለስላሳ ስለሆነ በሁሉም የጥርስ ንጣፎች (የፊት፣ የኋላ እና የማኘክያ ንጣፎች) ላይ በማተኮር ድዱን በእርጋታ እና በጥንቃቄ መቦረሽዎን ያረጋግጡ።
- በቀን ሁለት ጊዜ መቦረሽ፡- ጠዋት እና ከመተኛት በፊት የመቦረሽ ልማድን ለመመስረት በመሞከር ልጅዎን መደበኛ የጥርስ ንፅህናን እንዲለምድ ያድርጉ።
- ልጅዎን ይቆጣጠሩ፡- ልጅዎ በ 2 ዓመቱ በራሱ እንዲቦርሽ መፍቀድ ቢችሉም ትንንሽ ልጆች ጥርሳቸውን በራሳቸው ለመቦረሽ ቅልጥፍና የላቸውም። 6 ወይም 7 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ጥርሳቸውን በስርአት መቦረሻቸውን መከታተል አለብዎት።
ሀኪም ጋር መቼ መሄድ ያስፈልጋል?
ልጆች አንድ ዓመት ሲሞላቸው ወይም የመጀመሪያ ጥርሳቸውን ባገኙ በስድስት ወራት ውስጥ የጥርስ ሀኪምን እንዲጎበኙ የሚመከር ሲሆን የጥርስ ሀኪም የልጅዎን ጥርስ ተገቢ እድገት እንደከሚከታተሉ እና እንዴት መንከባከብ እንደሚችሉ በቂ መመሪያን ይሰጥዎታል። በተጨማሪም ሃኪምዎ ጣት ስለመምጠጥ እና ጡጦ ስለማጥባት ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይችላሉ።
ጥርስ ስለማብቀል ምክሮች
ጥርስ ማብቀል ህመምን በምፍጠር ለሕፃናት እና ወላጆች ፈታኝ ጊዜ ሊሆን ስለሚችል የልጅዎን ድድ ለማስታገስ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች እነሆ፡-
- ንጹህና የቀዘቀዘ ጨርቅን ማኘክ ህመምን ሊያረጋጋ ይችላል።
- ቀዝቀዝ ያሉ የድድ መጫወቻዎች ላይ ድድን ማሸት ህመምን ለመቀነስ እና እፎይታን ለመስጠት ይረዳሉ።
- ልጅዎ በህመም በጣም እየተሰቃየ ከሆነ እንደ አሲታሚኖፌን ወይም የጥርስ መፋቂያ ጄል ያሉ አስተማማኝ የህመም ማስታገሻ አማራጮችን በተመለከተ ከህፃናት ሐኪምዎ ጋር ይመካከሩ።
ቀደም ብለው በመጀመር እና የማያቋርጥ የአፍ ንፅህና አጠባበቅ ሂደቶችን በማቋቋም ለልጆችዎ ህይወት ዘመን ሁሉ የሚጠቅሙ ጤናማ ልምዶችን እንዲያዳብሩ ይረዳሉ።



