አዲስ የተወለደ ልጅዎ ቆዳ ላይ የሚታየውን እሙካ ወዲያውኑ ማጽዳት ያስፈልጋል?
በፊልሞች ላይ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ሮዝ፣ ውብ እና በጣም ንጹህ ሆነው ሲታዩ እንመለከታለን። በእውነታው ዓለም ግን ልጅዎ ሲወለድ ቆዳው ላይ ወፍራም፣ ነጭ እና ቅባታማ ሽፋን ሊኖር ይችላል።
ይህ አይብ መሰል ነጭ ሽፋን በህክምናው አለም ቨርኒክስ ካሴኦሳ' (Vernix caseosa) የሚባል ሲሆን ከውሃ፣ ከተፈጥሯዊ ቅባት፣ ከፕሮቲን እና ከሞቱ የቆዳ ሕዋሳት የተሰራ ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው።
ይህ ሽፋን በእርግዝና በ19ኛው ሳምንት አካባቢ መፈጠር የሚጀምር ሲሆን፣ እስከ 34ኛው ሳምንት ድረስ እየወፈረ ይሄዳል። እርግዝናው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ እንሽርት ውሃው (Amniotic fluid) እየረገፈ ስለሚሄድ በ40ኛው ሳምንት አካባቢ አብዛኛው ሽፋን ይጠፋል። በመሆኑም ያለቀናቸው ቀደም ብለው የሚወለዱ ጨቅላዎች ከፍተኛ የእሙካ ክምችት ሲኖራቸው፤ በቀናቸው ወይም ከዚያ ዘግይተው የሚወለዱት ደግሞ ሽፋኑ በጣም ጥቂት ሊሆን ወይም ሙሉ በሙሉ ላይኖራቸው ይችላል።
የእሙካ (Vernix caseosa) ጥቅም ምንድን ነው?
እሙካ የሚከተሉትን ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ይሰጣል፦
1. በእርግዝና ወቅት (During Pregnancy)
- በሕፃኑ ስስ ቆዳ እና በአካባቢው ባለው የእንሽርት ውሃ (Amniotic fluid) መካከል እንደ ተፈጥሯዊ ጋሻ ሆኖ ያገለግላል፤ ቆዳው ለ9 ወራት ያህል በፈሳሽ ውስጥ በመቆየቱ ምክንያት እንዳይጎዳ ወይም እንዳይላጥ ይከላከላል።
- ፅንሱ በእንሽርት ውሃው ውስጥ የሚረግፈውን እሙካ በሚውጥበት ጊዜ፣ በአንጀቱ ውስጥ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች (Healthy gut microbiome) እንዲፈጠሩና የምግብ መፈጨት ሥርዓቱ እንዲዳብር ያግዛል።
2. በምጥ እና በወሊድ ወቅት (During Labor & Delivery)
እሙካ የማዳለጥ ባሕሪ ስላለው እንደ ተፈጥሯዊ ቅባት (Lubricant) ሆኖ ያገለግላል። ይህም ሕፃኑ በማኅፀን መተላለፊያ በኩል በሚወጣበት ወቅት የሚፈጠረውን ግጭትና ፍትጊያ በማለስለስ ወሊዱ ይበልጥ የተቀላጠፈ እንዲሆን ይረዳል።
3. ከወሊድ በኋላ (Postpartum)
- የልጅዎ ቆዳ እንዳይደርቅና እንዳይሰነጣጠቅ የሚከላከል ጠንካራ የተፈጥሮ ከለላ ሆኖ ያገለግላል፤ የሕፃኑንም ለስላሳ ቆዳ ያርሳል
- ቆዳን ከተለያዩ ጎጂ ባክቴሪያዎችና ፈንገሶች ለመከላከል የሚያስችሉ የተፈጥሮ ፀረ-ተሕዋስያን ንጥረ ነገሮችን (Antimicrobial properties) በውስጡ ይዟል።
- ልጅዎ ከተወለደ በኋላ ወዲያውኑ የሰውነት ሙቀቱን እንዳያጣ ይረዳል፤ ይህም በብርድ ምክንያት ለሚከሰት ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት መቀነስ (Hypothermia) የመጋለጥ ዕድሉን ይቀንሳል
- ከልጅዎ ቆዳ ላይ ፈሳሽ በቀላሉ እንዳይተን በማድረግ ለሰውነት ፈሳሽ እጥረት (Dehydration) እንዳይጋለጥ ይከላከላል
- የእሙካ ተፈጥሯዊ ጠረን በልጅዎ አእምሮ ውስጥ ጡት ለመጥባት አስፈላጊ የሆኑትን የነርቭ ምላሾችን (Suckling reflexes) ያነቃቃል።
እሙካ በሕፃኑ ቆዳ ላይ ለምን ያህል ጊዜ መቆየት አለበት?
እሙካ ለልጅዎ ስስ ቆዳ እጅግ በርካታ ጥቅሞችን የሚሰጥ በመሆኑ ከተወለደ በኋላ ወዲያውኑ ታጥቦ ወይም በጨርቅ ታሽቶ መወገድ የለበትም። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ልጅዎ የዚህን ሽፋን ሙሉ ጥቅም እንዲያገኝ በቆዳው ላይ ቢያንስ ለ6 ሰዓታት ቢቻል ደግሞ እስከ 24 ሰዓታት ድረስ እንዲቆይ ይመክራል።
ለእሙካ የሚመከሩ ትክክለኛ የእንክብካቤ መንገዶች
ልጅዎ ከተወለደ በኋላ ነጩን ሽፋን ወዲያውኑ አጥቦ ከማስወገድ ይልቅ የሚከተሉትን ተገቢ እንክብካቤዎች ያድርጉ ፦
- ሽፋኑ በራሱ ጊዜ ቀስ በቀስ ወደ ሕፃኑ ቆዳ እስኪሰርጽ ድረስ በቂ ጊዜ ይስጡት።
- ሽፋኑ በብዛት ያለ ከመሰለዎት ከማበስ ይልቅ እንደ ሎሽን የልጅዎ ቆዳ ላይ ቀስ አድርገው ይሹት
- በልጅዎ ቆዳ ላይ የተወሰነ ደም ወይም የእንሽርት ውሃ ካለ ነጩን ሽፋን ሳያላቁ በለስላሳና ንጹህ ጨርቅ በጥንቃቄ ይጥረጉ
- የመታጠቢያው ጊዜ ሲደርስ ለብ ያለ ውሃ እና ለጨቅላ ሕፃናት ተብለው የተዘጋጁ ለስላሳ ሳሙናዎችን ይጠቀሙ። ከባድ ሳሙናዎችን እና ቆዳውን በኃይል ከማሸት ይቆጠቡ።
እሙካን ቀደም ብሎ ማጽዳት አስፈላጊ የሚሆነው መቼ ነው?
የመጀመሪያውን ገላ መታጠብ ማዘግየት በአጠቃላይ የሚመከር ቢሆንም በሚከተሉት ልዩ የሕክምና ሁኔታዎች ግን ሐኪሞች ሕፃኑ በተቻለ ፍጥነት ወዲያውኑ እንዲታጠብ ሊወስኑ ይችላሉ፦
- ሕፃኑ በማኅፀን ውስጥ እያለ የመጀመሪያ ሰገራ (Meconium) ካስወጣ እና በሰገራው ከተበከለ
- የእንሽርት ውሃ ኢንፌክሽን (Chorioamnionitis) ከነበረ
- እናትየዋ ወደ ሕፃኑ ሊተላለፉ የሚችሉ እንደ ኤች.አይ.ቪ ወይም ሄፓታይተስ ያሉ ተላላፊ ኢንፌክሽኖች ካሉባት
ልብ ይበሉ እሙካ በፍጹም ታሽቶ ወይም ተፈግፍጎ መወገድ ያለበት የቆዳ ቆሻሻ ሳይሆን ጨቅላ ልጆችን ከኢንፌክሽንና ከብርድ የሚታደግ የተፈጥሮ ጋሻ መሆኑን በመገንዘብ ልጅዎ የዚህን ሽፋን ሙሉ ጥቅም እንዲያገኝ ያድርጉ !




