ልጅዎን ተጨማሪ ምግብ ሲጀምሩ ሊያውቋቸው የሚገቡ ዋና ዋና አለርጂ ቀስቃሽ ምግቦች !

Elsabet Azezew
Nov 11, 2026
image 2026 09 28 151112863

            ልጅዎን ተጨማሪ ምግብ ሲጀምሩ ሊያውቋቸው የሚገቡ ዋና ዋና አለርጂ ቀስቃሽ ምግቦች !

ለልጅዎ አዳዲስ ምግቦችን ማስጀመር በዕድገቱ ውስጥ አስደሳች ከሆኑ ሂደቶች አንዱ ነው። ገር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። በመሆኑም ስለ አለርጂ አምጪ ምግቦችና ስለሚያስከትሏቸው ምልክቶች ማወቅ ልጅዎን ከአደጋ ለመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። 

የምግብ አለርጂ የሚከሰተው የሰውነት የበሽታ የመከላከል ስርዓት በምግብ ውስጥ የሚገኘውን ፕሮቲን በስህተት እንደ ጎጂ አካል በመመልከት ምላሽ ሲሰጥ ነው።

ይህም ሰውነት አይጂኢ(IgE) በመባል የሚታወቁ ፀረ እንግዳ አካልሎችን (antibodies) እንዲያመነጭ በማድረግ እንደ ሂስታሚን (histamine) ያሉ ኬሚካሎች እንዲለቀቁ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የአለርጂ ምልክቶች ይከሰታሉ። ምልክቶቹ አብዛኛውን ጊዜ ምግቡን ከተመገቡ ከጥቂት ደቂቃዎች እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ። 

አብዛኞቹ የምግብ አለርጂዎች ቀላል የሚባሉ ቢሆኑም አንዳንዴ ግን ከባድ ምላሾችን በመቀስቀስ ለሕይወት አስጊ ሊሆኑ ይችላሉ። 

              የተለመዱ አለርጂ አምጪ ምግቦች የትኞቹ ናቸው ?

በሕፃናት ላይ የአለርጂ ምላሽ ከሚቀሰቅሱ ዋና ዋና ምግቦች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦ 

  • ወተት
  • እንቁላል
  • ስንዴ
  • አኩሪ አተር (Soya)
  • ለውዝ / ኦቾሎኒ (Peanuts)
  • ዓሣ
  • ሰሊጥ
  • የባሕር ምግቦች (Shellfish)

ከ 90% በላይ የሚሆኑት የምግብ አለርጂዎች የሚከሰቱት በእነዚህ ምግቦች ምክንያት ነው።  እንደ እንቁላል፣ ወተትና ለውዝ ያሉ ምግቦች በሕፃናት ላይ ለሚከሰቱ አለርጂዎች የተለመዱት ቀስቃሾች ሲሆኑ ኦቾሎኒ እና ዓሣ ደግሞ ከባድ የአለርጂ ምላሾችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

አንዳንድ አለርጂዎች በተለይም የወተት፣ የእንቁላል፣ የስንዴ እና የአኩሪ አተር አለርጂዎች ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ሊጠፉ ይችላሉ። ነገር ግን የኦቾሎኒ፣ የዓሣ እና የባሕር ምግቦች አለርጂ ካደጉም በኋላ የመቆየት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። 

                 ሊከታተሏቸው የሚገቡ የምግብ አለርጂ ምልክቶች

የምግብ አለርጂ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ ምግቡ ከተሰጠ ከጥቂት ደቂቃዎች እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ይታያሉ። ሆኖም እያንዳንዱ ሕፃን ምልክቶቹን የሚያሳይበት መንገድ ሊለያይ ይችላል። 

 

ከሚያሳዩአቸው ምልክቶች መከከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦ 

- ማስታወክ፣ የማቅለሽለሽ ስሜት፣ ተቅማጥ ወይም የሆድ ቁርጠት 

- የቆዳ ሽፍታ ወይም ቆዳ ላይ የሚወጡ ቀይ እብጠቶች  (Hives)

- የፊት፣ የከንፈር፣ የምላስ ወይም የአፍ እብጠት 

- በአፍ ወይም በጉሮሮ ውስጥ ማሳከክ እና የመዘጋት ስሜት 

- ሳል፣ ትንፋሽ ሲወጣ የሚሰማ የፉጨት ድምፅ (Wheezing) ወይም የመተንፈስ ችግር 

- የማዞር ስሜት ወይም ድንገተኛ የደም ግፊት መቀነስ 

ልብ ይበሉ ልጅዎ የመተንፈስ ችግር፣ የጉሮሮ ወይም የምላስ እብጠት፣ ከፍተኛ የማዞር ስሜት ወይም ሌሎች ከባድ የአለርጂ ምልክቶች ካጋጠሙት አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርበታል። 

               አለርጂ አምጪ ምግቦችን ለልጅዎ ለማስጀመር የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮች 

  • ቀደም ብለው ያስጀምሩ 

ልጅዎ ተጨማሪ ምግብ ለመጀመር ዝግጁ በሚሆንበት ወቅት (በ6 ወር አካባቢ) እንደ ኦቾሎኒ፣ እንቁላል፣ ስንዴና የወተት ተዋጽኦዎችን ማስተዋወቅ ይመከራል። 

  • በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ምግብ ብቻ ያስጀምሩ 

የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (CDC) በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት አለርጂ አምጪ ምግብ ብቻ እንዲሰጡ ይመክራል። ይህም የአለርጂ ምላሽ ከተከሰተ መንስኤውን በቀላሉ ለመለየት ይረዳል። በመሆኑም እያንዳንዱን አዲስ ምግብ ሲያስተዋውቁ በመካከል ከ3 እስከ 5 ቀናት ያሳርፉ። 

  • በአነስተኛ መጠን ይጀምሩ 

ምግቦቹን ሲያስጀምሩ ጥቂት መጠን በመስጠት ብቻ በመጀመር ልጅዎ ምንም ዓይነት የአለርጂ ምላሽ አለማሳየቱን በጥንቃቄ ይከታተሉ። 

  •  አዳዲስ ምግቦችን ቀን ላይ ያስጀምሩ

የአለርጂ ምልክቶች ቢታዩ በቅርብ መከታተል እንዲያስችልዎት ምግቦቹን ቁርስ ወይም ምሳ ሰዓት ላይ ቢሰጡ ይመረጣል። 

  •  የአለርጂ ምልክቶችን ይከታተሉ

እንደ ሽፍታ፣ እብጠት፣ ማስታወክ፣ ሳል፣ የመተንፈስ ችግር ወይም ሲተነፍስ የሚሰማ የፉጨት ድምፅ (wheezing) ያሉ ምልክቶችን በጥንቃቄ ይከታተሉ።

  • የተቀበለውን ምግብ አዘውትረው ይስጡ 

ልጅዎ ምግቡን ያለ ምንም ችግር ከተቀበለው መደበኛ የአመጋገብ ክፍሉ በማድረግ አዘውትረው ይስጡት

  • ምግቦችን በቆዳ ላይ በመቀባት አይሞክሩ

አለርጂን ለመፈተሽ ሲሉ ምግቡን በሕፃኑ ቆዳ ላይ በፍጹም አይቀቡት ። ምግቡን በልጅዎ ቆዳ ላይ ማሸት አስተማማኝ የአለርጂ መፈተሻ መንገድ አይደለም ፤ ይልቁንም ለከፋ የቆዳ መቆጣት ሊዳርግ ይችላል። 

  •  የመታነቅ አደጋን ይከላከሉ

የለውዝ ፍሬዎችን ወይም ወፍራም የለውዝ ቅቤን በፍጹም አይስጡ። ይልቁንም የተፈጨውን የለውዝ ቅቤ በውሃ፣ በእናት ጡት ወተት ወይም በተፈጨ ምግብ በማቅጠን ይስጡ።

                  የምግብ አለርጂ መድኃኒት አለው? 

በአሁኑ ወቅት የምግብ አለርጂን ሙሉ በሙሉ የሚያድን መድኃኒት የለም። ዋናው ሕክምና አለርጂ የሚያመጡ ምግቦችን ከአመጋገብ ማስወገድ እና ድንገት ተጋላጭነት ቢፈጠር አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ መሆን (Emergency Action Plan) ነው። 

ሆኖም ለአንዳንድ ሕፃናት ሐኪሞች የአለርጂ ምላሾችን ሥጋትና ክብደት ለመቀነስ የሚከተሉትን ሕክምናዎች ሊያዙ ይችላሉ፦ 

  •  ኦማሊዙማብ (Omalizumab)  

ዕድሜያቸው 1 ዓመት እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሕፃናት የተፈቀደ፣ በመርፌ የሚሰጥ ሕክምና ነው። ድንገት ለምግቦቹ በሚጋለጡበት ጊዜ የአለርጂ ምላሾችን ክብደት ለመቀነስ ይረዳል። 

  • ፓልፎርዚያ (Palforzia)

ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 17 ዓመት ለሆኑ የኦቾሎኒ አለርጂ ላለባቸው ሕፃናት በአፍ የሚወሰድ መድኃኒት ነው። ድንገት ለኦቾሎኒ ተጋላጭነት ቢፈጠር ምላሹ ከባድ እንዳይሆን ይከላከላል። 

 

እነዚህ ሕክምናዎች እንደ ኤፒኔፍሪን/አድሬናሊን (Epinephrine) ያሉ ድንገተኛና አጣዳፊ የሕክምና መድኃኒቶችን በፍጹም አይተኩም። በመሆኑም ወላጆች ለከባድ የአለርጂ አደጋዎች የታዘዘላቸውን ኤፒኔፍሪን ሁልጊዜ መያዝ እና የድንገተኛ ሕክምና መመሪያውን ተከትለው መስጠት ይኖርባቸዋል። 

Comments (0)