የታለበ የጡት ወተት እንዴት እናስቀምጥ ?

Elsabet Azezew
Sep 30, 2025
undefined

                                  የታለበ የጡት ወተት እንዴት እናስቀምጥ ? 

            የጡት ወተት ለልጅሽ ጤና ውድ ዋጋ ያለው በንጥረ ነገር የበለፀገ ምግብ ነው። በመጀመሪያዎቹ የልጅሽ የእድሜ ጊዜያት ለእድገቱ ቶል ቶሎ መመገብ በሚኖርብሽ ሰዓት፣ በስራ እና በተለይዩ ምክንያቶች ከቤት መውጣት ሲኖርብሽ የጡት ወተት በማለብ ማስቀመጥ ልትፈልጊ ትችያለሽ።

            የታለበው የጡትሽ ወተት ሳይበላሽ እና ለልጅሽ ጤናማ ሆኖ እንዲቆይ የሚያስችሉ ምክሮችን በዚህ ጽሁፍ እናያለን።

                    የጡት ወተት ሳይበላሽ ለማስቀመጥ የሚያስችል መመሪያ 

            የታለበን የጡት ወተት የማከማቻ መመሪያ (መንገድ) የሚወሰነው በሚከማችበት የሙቀት መጠን እንዲሁም ወተቱ አዲስ የታለበ ወይስ ቀደም ሲል ማቀዝቀዣ ውስጥ ገብቶ በረዶ ይዞ የወጣ ነው በሚለው የተመሰረተ ነው።  የሚከተሉትን መመሪያዎች መከተል በታለበው ወተት ውስጥ ልጅዎን ሊያሳምም የሚችል ባክቴሪያ እንዳይራባ እንዲሁም ወተቱ የያዘውን የንጥረ ነገሮች ጥራት እንዳያጣ ይረዳሉ። 

            አዲስ የታለበ ወተት ፍሪጅ ውስጥ ሳይገባ ውጪ ተቀምጦ ለተወሰኑ ሰዓታት ያገለግላል። ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያገለግል ከተፈለገ በማቀዝቀዣ ወይም ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ ተገቢ ነው።

     አዲስ የታለበ ወተት 

አዲስ የታለበ ወተት የተቀመጠበት ሁኔታ  የሚያገለግልበት ጊዜ
ውጪ ወይም ፍሪጅ ውስጥ ሳይገባ ( 25°C)4 ሰዓታት
ማቀዝቀዣ(ፍሪጅ) ውስጥ (4°C)ከ4 እስከ 5 ቀናት
ቀዝቃዛ ወይም በረዶ የያዘ እቃ ውስጥ (Cold packs/insulated container)24 ሰዓታት (ወይም እስከ 24 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ፍሪጅ ማዘዋወር ይችላል)

የፍሪጅ በረዶ ክፍል ውስጥ (-18°C)

 

ከ6 እስከ 12 ወራት

 

      ቀደም ሲል በረዶ ይዞ የቀለጠ ወተትስ ? 

ቀደም ሲል ማቀዝቀዣ ውስጥ ገብቶ በረዶ ይዞ የወጣ ወተትን አገልግሎት ላይ ስታውይ ወይም እንደገና ስታስቀምጪ የተለየ መመሪያዎች አሉት፤ እነርሱም እንደሚከተሉት ቀርበዋል  

ቀደም ሲል በረዶ ይዞ በረዶው የለቀቀ (የቀለጠ) ወተትየሚያገለግልበት ጊዜ
ውጪ ወይም ፍሪጅ ውስጥ ሳይገባ ( 25°C)ከ1 እስከ 2 ሰዓታት
ማቀዝቀዣ(ፍሪጅ) ውስጥ (4°C)24 ሰዓታት
የፍሪጅ በረዶ ክፍል ውስጥ (-18°C)በረዶው የለቀቀ ወይም የቀለጠ ወተትን በድጋሚ የፍሪጅ የበረዶ ክፍል ውስጥ አይቀዝቅዙ
  • የጡት ወተትሽን ያስቀመጥሽበት መንገድ ምን ይሁን ምን ልጅሽ ከተመገበ በኋላ ጡጦ ውስጥ የቀረውን ወተት በ2 ሰዓታት ውስጥ መጠቀም አለብሽ።
  • እዚህ ላይ ማስተዋል ያለበሽ ነገር  ከላይ የተጠቀሱት መመሪያዎች በጊዜያቸው ለተወለዱ ሕፃናት የታሰበ ነው። 

                   የጡት ወተትን በአግባቡ እንዴት ማዘጋጀት ትችያለሽ ?

የጡት ወተትሽን የምታልቢበትን እቃ እንዲሁም የጡት ወተትሽን ከመንካትሽ በፊት እጅሽን ለብ ባለ ውሃ እና  በሳሙና መታጠብሽን ሁልጊዜ ማረጋገጥ ይኖርብሻል። ሳሙና ማግኘት ካልቻልሽ ቢያንስ 60% አልኮል የያዘ የእጅ ሳኒታይዘርን (hand sanitizer) መጠቀም ትችያለሽ።

              የጡት ወተትን በምታቀዘቅዥበት ጊዜ የሚረዱሽ ምክሮች

  • አዲስ ያለብሽውን የጡት ወተት ወዲያውኑ ለመጠቀም ካላሰብሽ የወተቱን ጥራት ለመጠበቅ ወዲያውኑ ብታቀዘቅዥው ይመከራል።
  • የታለበውን የጡት ወተት በምታቀዘቅዢ ጊዜ  በትንሽ መጠን ማለትም ከ 60-120 ሚ.ሊ ቢሆን ይመረጣል። ይህም ልጅሽ ያልጨረሰው ወተት እንዳይባክን ያግዝሻል ፤ ካነሰው ሁልጊዜም መጨመር ስለምትችይ ማለት ነው ።
  • ወተቱን ለማቀዝቀዝ እቃ ውስጥ ወይም ጡጦ ውስጥ በሚያደርጉበት ጊዜ በረዶ ሲሰራ ቦታ እንዲኖረው ሳትሞይ ቢያንስ 2.5 ሴ.ሜ (cm) ያህል ባዶ ቦታ ተይለት። 
  • ወተቱን የፍሪጅ በረዶ ክፍል ውስጥ በምታስቀምጭበት ጊዜ በር ላይ ሳይሆን ውስጥ ላይ ማስቀመጥሽን እርግጠኛ ሁኚ። ይህም ወተቱን ሊኖር ከሚችል የሙቀት መለዋወጥ ለመጠበቅ ይስችልሻል።

              በረዶ የያዘን ወተት ለማቅለጥ እና ለማሞቅ የሚረዱ ምክሮች

  • ሁልጊዜም ፍሪጅ ውስጥ ከገባ የቆየውን ወተት መጀመሪያ ተጠቀሚ።
  • ወተቱን ለማቅለጥ በማቀዝቀዣው የታችኛው ክፍል ውስጥ አንድ ሌሊት አስቀምጪ። ልጅሽ ካልፈለገ በስተቀር ወተቱን ማሞቅ አያስፈልግሽም።
  • ወተቱን ምታሞቂ ከሆነ ግን ስታሞቂ የዕቃው ክዳን በደንብ መዘጋቱን አረጋግጭ። ወተቱን የወተት ዕቃውን ወይም ጡጦውን በሚፈስ ለብ ባለ ውሃ ስር በመያዝ ወይም ለብ ባለ ውሃ ውስጥ በማስቀመጥ አሙቂው።
  • ወተትን ለማሞቅ ማይክሮዌቭ በጭራሽ እንዳትጠቀሚ። ማይክሮዌቭ ወተቱን ሊያበላሸው እና ልጅሽን ሊያቃጥሉ የሚችሉ ትኩስ ቦታዎችን ሊፈጥር ይችላል።
  • ለልጅሽ ከመስጠትሽ በፊት ሁልጊዜም የወተቱን ሙቀት በእጅ ላይ በማንጠባጠብ ፈትሺ። ትኩስ ከሆነ እስኪቀዘቅዝ ድረስ መጠበቅ ይኖርብሻል።
  • የወተቱን ስባማ ክፍል ከውሃማው ክፍል ጋር ለማዋሃድ ወተቱን በኃይል ባትነቀንቂ ይመከራል  ይልቁንም ወተቱን በቀስታ በመወዝወዝ አዋህጂ።

Comments (0)