የሕጻናት አመጋገብ ምን መምሰል አለበት?
ሕጻናትን የምንመግብበት መንገድ በጤናቸው፣ በእድገታቸው ብሎም በወደፊት ሂወታቸው ላይ ያለው ሚና ጉልህ ሲሆን በመጀመሪያወቹ አመታት አግባብ ያለውና በጥናት የተደገፈ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል በሽታን ለመከላከል እና የተሻለ እድገትን ለማረጋገጥ ትልቅ ድርሻ አለው። በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት አእምሮና አካል በፍጥነት የሚያድጉበት እና የወደፊት የማገናዘብ ብሎም የጤና መሠረት የሚጣልበት ጊዜ ስለሆኑ በዚህ ጊዜ ሕጻናት በአግባቡ ካልተመገቡ በአካላዊ እና በአዕምሮአዊ እድገታቸው ላይ የሚፈጠረው ጉዳት በኋላ ለማስተካከል ከባድ ይሆናል።
አንዲት እናት በወለደች በመጀመሪያወቹ ሰዓታት ውስጥ ጡቶቿ የሚያመርቱት በአይነቱ ለየት ያለና በተለምዶ አጠራሩ “እንገር” በመባል የሚጠራ የወተት አይነት ሲሆን ወፈር ያለ፣ ቢጫ መልክ ያለው፣ መጠኑ ትንሽ እና አዲስ ለተወለደ ሕፃን በጣም ተስማሚ እና በቂ ነው። ይህ ወተት በፕሮቲን፣ በቫይታሚን እና በማዕድናት የበለጸገ ሲሆን የሕጻኑ በሽታ መከላከል አቅም ገና በማደግ ላይ በመሆኑ በዚህ ወተት ውስጥ የሚገኙ በሽታ ተከላካይ ንጥረ-ነገሮች ህጻኑ ራሱን ከበሽታ እናዲከላከል ያስችሉታል። ስለዚህ ሕጻናት ይህን ጠቃሚ የወተት አይነት እንዲአያገኙ በተወለዱ አንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ማጥባት መጀመር ሲኖርባቸው በእናት እና ልጅ የቆዳ ለቆዳ መነካካት የሕፃኑን ሙቀት ለመጠበቅ ያግዛል፣ የእናትና የልጅ ግንኙነትን ያጠናክራል እንዲሁም የጡት ወተት እንዲመረት የሚያስችሉ ሆርሞኖችን ያነቃቃል።
በሆነ የጤና ምክንያት ሐኪም ካላዘዘ በስተቀር በመጀመሪያወቹ ስድስት ወራት አንድ ሕፃን የሚያስፈልገው የጡት ወተት ብቻ ሲሆን ውኃ፣ ሻይ፣ ጭማቂ ወይም ሌሎች ምግቦችን ሙሉ በሙሉ ልናስወግድ ይገባል። ። የጡት ወተት አንድ ሕጻን የሚያስፈልገወን በቂ የውሃ መጠን የያዘ ሲሆን ሌላ ተጨማሪ ፈሳሽ መስጠት መጥባት የሚችሉትን የጡት ወተት መጠን በመቀነስ እንዲሁም ለተቅማጥ እና ለሌሎች በሽታወች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። የጡት ወተት በቂ ፕሮቲን፣ ስኳር፣ ስብ፣ ቫይታሚን እና ማዕድናትን ያካተተ ሲሆን በቀላሉ የመፈጨት አቅም አለው። በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የጡት ወተት ብቻ የጠቡ ሕጻናት በዚህ መልኩ ካልተመገቡ ሕጻናት አንጻር ሲታዩ በተቅማጥ፣ በሳንባ ምችና በሌሎች በሽታወች የመያዝ እድላቸው አናሳ ነው። ሌላው በማህበረሰባችን ጥሩ እንደሆነ ቢነገርም ለመጀመሪያወቹ 12 ወራት የላም ወተት ለሕጻናት መስጠት በውስጡ ያለው የብረት መጠን አናሳ በመሆኑ ሕጻናትን ለደም ማነስ ሊያጋልጥ ይችላል።
ስድስት ወር ሲሞላቸው የሕጻናት ሰውነት የጡት ወተት ብቻ ከሚሰጠው የበለጠ ሃይል እና ንጥረ ነገር ስለሚፈልግ በዚህ ጊዜ ጡት ማጥባቱ እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ምግቦችን መጨመር መጀመር ይኖርብናል። የምንጀምራቸው ምግቦች ለስላሳ፣ የበሰሉ እና ለመዋጥ ቀላል መሆን ሲኖርባቸው የተለያዩ ምግቦችን በአንዴ ከመመገብ ይልቅ ተራ በተራ ማስለመድ የተመከረ ሲሆን ለህጻኑ የማይስማማው የምግብ አይነትን በቀላሉ ለመለየት ይረዳል። እነዚህ ምግቦች በተለየ ንጽህና መዘጋጀት እና መቅረብ ሲኖርባቸው ንጹህ የመመገቢያ እቃወች ሊኖሩ ይገባል። ጡጦ በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ሊበከል ስለሚችል የግድ መጠቀም ካለብን በሙቅ ውሃ በማጠብ ንጽናውን መጠበቅ አለብን። በመጀመሪያ በቀን ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ትንሽ ትንሽ መጠን መስጠት በቂ ሲሆን ሕጻኑ እያደገ ሲመጣ ቁጥርና መጠኑንበ በቀስታ መጨመር ያስፈልጋል።
ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ያለው ጊዜ ሕፃናት ለበሽታ እና ደካማ ለሆነ እድገት የሚጋለጡበት ጊዜ ስለሆነ ከጡት ወተት ተጨማሪ የሚሰጠው ምግብ በጊዜ ካልተጀመረ ወይም በቂ ካልሆነ ልጁ ሊቀነጭር ወይም እድገቱ ወደኋላ የቀረ ሊሆን ይችላል። ከዘጠኝ ወር እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያሉ ልጆች በቀን ሶስት ወይም አራት ዋና ምግብ እና በተቻለ መጠን ተጨማሪ ትናንሽ መክሰሶች በየመሃሉ ሲያስፈልጋቸው የጡት ወተት እስከ ሁለት አመት ድረስ ሊቀጥል ይገባዋል። ሕጻናትን መመገብ በትዕግስትና በሃላፊነት መደረግ ያለበት ነገር ሲሆን የርሃብ እና የመጥገብ ምልክቶችን መከታተል እና ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ሁለት ዓመት የሞላው ልጅ ከሌላ የቤተሰቡ አባላት ጋር ተመሳሳይ ምግብ መብላት ሲችል መጠኑ በእድሜው ልክ መሆን አለበት። የቀን ተቀን ምግቡ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣ አትክልት እንዲሁም እንደ ባቄላ፣ አተር፣ ምስር፣ እንቁላል፣ ዓሳ እና ስጋ በቂ ፕሮቲን ያላቸው ምግቦችን ያካተተ እንዲሆን ይመከራል። የለስላሳ መጠጦች እና የታሸጉ ምግቦች ከመጠን በላይ ክብደት መጨመርንና የጥርስ መበላሸትን ስለሚያስከትሉ በተቻለ መጠን ማስወገድ አስፈላጊ ነው።
አንዳንድ ከመወለጃ ጊዚያቸው ቀደም ብለው የተወለዱ ወይም ትንሽ ክብደት ይዘው የተወለዱ ልጆች በቂ የጡት ወተት እንዲያገኙ ወይም መጥባት እስኪችሉ ድረስ የተለየ የአመጋገብ እንክብካቤ እና የህክምና ሰራተኞች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ኤችአይቪ ያለባት እናት መድሃኒት(ART) እየወሰደች ጡት ማጥባቷን መቀጠል ብትችልም ጡት የማጥባት ወይም ያለማጥባት ውሳኔን ከህክምና ባለሙያ ጋር በመማከር መወሰን መልካም ነው።
በመጨረሻም ጤናማ ልጅ ማሳደግ የእናት ብቻ ሐላፊነት ሳይሆን አባቶች እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት እናት በቂ ጡት ለማጥባት የሚያስችላትን ድጋፍ እያገኘች መሆኑን በማረጋገጥ እና ጎጂ የሆኑ የአመጋገብ ልማዶችን እንዲቀሩ በማድረግ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ልጆቻችንን ከውልደት ጀምሮ እስከ እድገት ድረስ በትክክል በመመገብ ከበሽታ በመከላከል እንዲሁም ለራሳቸውና ለሃገራቸው የተሻለ ነገን ለመገንባት የሚያስችላችውን ጥንካሬ፣ ብሩህነት እና በራስ መተማመንን መስጠት ዋና ሃላፊነታችን ነው።
ዮሐንስ አለምመጣ


