ጥርሶችዎን መቦረሽ የአፍ ጤናዎን ለማሻሻል ፣ የጥርስ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ፣ እንዲሁም የድድ በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚረዳ መንገድ ነው። ከጊዜ በኋላ፣ የጥርስ ብሩሽ በባክቴሪያ፣ በቆሻሻ፣ በደም እና በምራቅ ሊበከል ይችላል። እንዲሁም በቆዩ ቁጥር ውጤታማነታቸውን ያጣሉ፣ እና ብሩሾቹ መበታተን ሲጀምሩ፣ ጥስ ላይ የተለጠፉ ነገሮችን ከጥርሶች ላይ በአግባቡ ማስወገድ አይችሉም። የጥርስ ብሩሽዎ በተቻለ መጠን ውጤታማ እንዲሆን፣ ያልተበላሹና ጥራት ያላቸው ብሩሾች ሊኖሩት ይገባል።
የጥርስ ባለሙያዎች በቀን ሁለት ጊዜ ለ2 ደቂቃዎች ጥርስዎን እንዲቦርሹ ይመክራሉ፣ ይህም ጥርሶችዎን ከመቦርቦር ለመከላከል ይረዳዎታል። በቀን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ጊዜ ጥርሶትን የሚቦረሹ ከሆነ በብሩሽዎ ውስጥ ያሉት ፀጉሮች በ3 ወር ጊዜ ውስጥ መውጣት፣ መበላሸት ወይም መጣመም ይጀምራሉ።
የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል (CDC) እና የአሜሪካ የጥርስ ሕክምና ማህበር (American Dental Association) የጥርስ ብሩሽዎን ቢያንስ በየሶስት እስከ አራት ወሩ አንዴ መቀየር እንዳለብዎት ይመክራል። ብሩሾቹ መበላሸትና ጥርሶችዎን የማጽዳት አቅማቸው መቀነስ የሚጀምረው በዚህ ጊዜ አካባቢ ነው።
ከሶስት ወር ገደብ በፊት የጥርስ ብሩሽዎን መለወጥ የሚያስፈልግበት ጊዜም አለ። የሚከተሉትን ካዩ የጥርስ ብሩሽዎን ወዲያውኑ ይቀይሩ፦
- የጥርስ ብሩሽዎት የተጎዳ ወይም የተበላሸ ከመሰልዎት
- ታመው ከነበሩ (ኢንፌክሽንን ለመከላከል)
- ለጉዳት ከተጋለጠ (ለምሳሌ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ከወደቀ፣ በቦርሳዎ ውስጥ ተከፍቶ ከተቀመጠ፣ የቤት እንስሳ ጋር ንክኪ ከነበርዎት ወይም ለረጅም ጊዜ በዕቃው ውስጥ ችላ ተብሎ ከቆየ)
- ከተቦረሹ በኋላ ጥርሶችዎ እንደጸዱ የማይሰማዎት ከሆነ
- ለመጨረሻ ጊዜ የቀየሩት መቼ እንደሆነ የማያስታውሱ ከሆነ
- ሽታ መምጣት ከጀመረ
- የቀለም መቀየር ካመጣ
የጥርስ ብሩሽዎን እንዴት መንከባከብ አለብዎት?
የጥርስ ብሩሽዎ እስከ ሶስት ወር ሳይደርስ ለመቀየር የሚያስገድድዎ ከሆነ፣ ዕድሜውን ለማርዘም የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ፦
- የጥርስ ብሩሽዎን አያጋሩ፦ ከቤተሰብ አባላት ጋር እንኳን የጥርስ ብሩሽዎን መጋራት የለብዎትም። የጥርስ ብሩሽዎ ከሌሎች ጋር በአንድ ዕቃ ውስጥ ከተቀመጠ፣ ብሩሽ ጭንቅላቶቹ እርስ በእርስ እንዳይነካኩ ጥንቃቄ ያድርጉ።
- በደንብ ይጠቡት፦ ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ የጥርስ ብሩሽዎን ሙሉ በሙሉ በቧንቧ ውሃ ያጠቡት። ለማጽዳት ፀረ-ተባይ (disinfectant)፣ የአፍ ማጠቢያ ወይም ትኩስ ውሃ መጠቀም አያስፈልግም።
- በተከደነ ዕቃ ውስጥ አያስቀምጡ፦ ብሩሽዎን በማይጠቀሙበት ጊዜ ንፁህ ሆኖ እንዲቆይ ልዩ የሆነ የተዘጋ ዕቃ አያስፈልግም። አንዳንዶቹ የተዘጉ ዕቃዎች ሻጋታ እንዲፈጠር ወይም ባክቴሪያዎች እንዲስፋፉ ሊያደርጉ ይችላሉ።
- ብሩሹን ቀጥ አድርገው ያስቀምጡ፦ ሙሉ በሙሉ እንዲደርቅ ቀጥ ባለ ቦታ ያስቀምጡት።
- ከመጠን በላይ አይጫኑ፦ በጣም አጥብቆ መቦረሽ የበለጠ ንጽህና ማለት አይደለም፤ የጥርስ ብሩሽዎንም ያበላሻል።
- በሚጓዙበት ጊዜ፣ የጥርስ ብሩሽዎ ጭንቅላት በመንገድ ላይ ቆሻሻ እንዳይነካ ለመከላከል ለመሸፈን ጥረት ያድርጉ።
ኤሌክትሪክ ወይስ መደበኛ የጥርስ ብሩሽ?
በቀን ሁለት ጊዜ ለሁለት ደቂቃዎች ያህል በጥሩ የመቦረሽ ዘዴ የሚቦርሹ ከሆነ፣ መደበኛ የጥርስ ብሩሽ (manual toothbrush) ጥርስዎና ድድዎ በትክክል እንዲጸዳ በቂ ነው። ነገር ግን የኤለክትሪክ ብሩሾች ከመደበኛው የጥርስ ብሩሾች የበለጠ የማጽዳት አቅም አላቸው።
የኤሌክትሪክ የጥርስ ብሩሾች የድምፅ ሞገዶችን በመጠቀም ጥርስ ላይ የተጣበቁ ነገሮችን እና ባክቴሪያዎችን ከጥርስዎና ከድድዎ ላይ በቀስታ በመንቀጥቀጥ ያስወግዳሉ።
የኤሌክትሪክ የጥርስ ብሩሾች ከመደበኛ የጥርስ ብሩሾች የበለጠ በብቃት እና በውጤታማነት ያጸዳሉ፤ ምክንያቱም በሚመከረው የሁለት ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ከመደበኛው ብሩሽ እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ የመቦረሽ እንቅስቃሴን ያከናውናሉ። በተጨማሪም፣ የጥርስ ብሩሹን ከጥርስዎ እና ከድድዎ ላይ ከመጠን በላይ እንዳይጫኑት ያደርጋሉ።
አብዛኛዎቹ የኤሌክትሪክ የጥርስ ብሩሽ ጭንቅላቶች በየሶስት ወሩ መለወጥ አለባቸው። ነገር ግን በኤሌክትሪክ የጥርስ ብሩሽ ጭንቅላት ላይ ያሉት ፀጉሮች ከመደበኛ የጥርስ ብሩሽ ያጠሩ ናቸው። ይህ ማለት የብሩሽ ፀጉሮቹ በፍጥነት ሊያልቁ እና ሊበታተኑ ይችላሉ። ስለዚህ የኤሌክትሪክ ብሩሾችን ከመደበኛ የጥርስ ብሩሾች ከሚቀይሩበት ጊዜ ቀደም ብሎ ሊቀይሩ ይችላሉ።


