ለጨቅላ ልጅዎ ውሃ መስጠት መጀመር ያለቦት መቼ ነው ?
ምንም እንኳን ለልጅዎ ውሃ አለመስጠት ተፈጥሯዊ ያልሆነ ወይም ያልተለመደ ነገር ሊመስሎት ቢችልም ለህፃናት እስከ 6 ወር ዕድሜያቸው ድረስ ውሃ መስጠት የለቦትም። ይህም የራሱ የሆነ ምክንያት አለው።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚያመለክተው የጡት ወተት በውስጡ ከ80 በመቶ በላይ ውሃን የሚይዝ ሲሆን ለልጅዎ የሚያስፈልገውን ፈሳሽ ይሰጣል። ስለዚህ ልጅዎ ተጨማሪ ውሃ አያስፈልገውም። የፎርሙላ ወተት የሚመገቡ ህፃናትም በፎርሙላቸው አማካኝነት በቂ ፈሳሽ ያገኛሉ።
ልጅዎን በደንብ የሚያጠቡ ከሆነ እና በቂ የፎርሙላ ወተት የሚሰጡ ከሆነ በቂ ውሃ አገኝቷል ወይ የሚለው ነገር ሊያሳስቦት አይገባም።
ለጨቅላ ልጅዎ ውሃ መስጠት የሌለቦ ለምንድን ነው?
ከስድስት ወር በታች ለሆኑ ህፃናት ውሃ እንዲሰጣቸው የማይመከርባቸው ምክንያቶች የሚከተሉትን ይመስላሉ
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የክብደት መቀነስን ያስከትላል
ለጨቅላ ህፃናት ውሃ መስጠት ቶሎ እንዲጠግቡ በማድረግ ጡት የመጥባት ፍላጎታቸውን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ ክብደት እንዲቀንሱ እና ቢሊሩቢን (bilirubin) የተባለው ንጥረ ነገር በሰውነታቸው እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።
- የውሃ መመረዝ (Water Intoxication)
አዲስ ለተወለዱ ህፃናት ውሃ መስጠት የውሃ መመረዝን ያስከትላል። ይህም በሰውነታቸው ውስጥ ያሉትን ሌሎች ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል።
- የኤሌክትሮላይት መዛባት
ከመጠን በላይ የሆነ ውሃ መውሰድ የሕፃኑ ኩላሊቶች እንደ ሶዲየም ያሉ ጠቃሚ ኤሌክትሮላይቶችን እንዲያስወግድ ያደርጋል። ይህም በሰውነት ውስጥ የኤሌክትሮላይት ሚዛን መዛባት (imbalances) ያስከትላል።
ዕድሜያቸው ከ 6 እስከ 12 ወር ለሆኑ ህፃናት ምን ያህል ውሃ እንስጣቸው?
ልጅዎ ተጨማሪ ምግቦችን መመገብ በሚጀምርበት ወቅት ውሃን አብረው ማስጀመርም ይኖርቦታል።
የፊላዴልፊያ የህፃናት ሆስፒታል (Children’s Hospital of Philadelphia (CHOP)) እንደገለጸው ጨቅላ ህፃናት ተጨማሪ ምግብ መውሰድ ሲጀምሩ ቀደም ሲል ሲወስዱት የነበረው የወተት ፍጆታ መጠን በ60-300 ሚ.ሊ ይቀንሳል።
ከ6 እስከ 12 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ሕፃናትን በቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብን መመገብ እና አጠቃላይ እድገታቸውን እንዲረጋገጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው ። ይህንንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማሳካት ተጨማሪ ምግቦችን በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ያስጀምሯቸው። በዚህ ወቅት ውሃ መስጠት ተገቢ ነው። ነገር ግን በቂ የጡት ወይም የፎርሙላ ወተት አብረው እየወሰዱ ከሆነ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ60 እስከ 120 ሚ.ሊ በላይ ውሃ መስጠት ላያስፈልገው ይችላል። ውሃውን ለህፃናት ተብሎ በተሰሩ ክዳናቸው ላይ መጠጫ ባላቸው ኩባያዎች ይስጧቸው። ልጅዎ የበለጠ ንቁ እየሆነ ሲሄድም ተጨማሪ ውሃ መስጠት ይችላሉ።
ዕድሜያቸው 12 ወር እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ህፃናት ምን ያህል ውሃ እንስጣቸው?
ልጅዎ 12 ወር ሲሞላው የሚወስደው የወተት መጠን ይቀንሳል። በዚህ ወቅት ቁርስ፣ ምሳ እና እራት በመደበኛነት የሚመገብበት እና ለተለያዩ አዲስ ምግቦች የሚተዋወቅበት ጊዜ ነው ። በዚህ እና በልጅዎ የወተት ፍጆታ መቀነስ እንዲሁም በዚህ እድሜያቸው ላይ የበለጠ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት የሚወስዱት የውሃ መጠን መጨመር ይኖርበታል።
በካሊፎርኒያ የሚገኘው CHOC የህጻናት ሆስፒታል የአንድ ዓመት ህፃን ልጅ በየቀኑ 240 ሚ.ሊ. ወይም 8 አውንስ ኩባያ ውሃ እንዲጠጣ ይመክራል። ይህ የውሃ መጠን በየአመቱ እየተጨመረ መሄድ አለበት። በየቀኑ የሚጠጡት የ 8 አውንስ (240 ሚ.ሊ.) ኩባያ ውሃ ብዛት ከእድሜያቸው ጋር መመጣጠን አለበት ፤ ለምሳሌ አንድ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጅ በየቀኑ ሁለት የ8 አውንስ ኩባያ ውሃ መጠጣት አለበት።



