የመርሳት ችግር/dementia
•ሰዎች በጊዜ ሂደት በፊት የነበሯቸው የማሰብ፣የማስታወስና የማገናዘብ ብቃት(Cognitive capacity) እየቀነሰ ሲመጣና በህይወታቸው ላይ ችግር መፍጠር ሲጀምር የመርሳት ችግር ተከሰተ እንላለን::
• ይህ ህመም:- በተለይም እድሜያቸው ከ65 አመት በሆናቸው ሰዎች ላይ በብዛት ቢስተዋልም : በወጣትና ጎልማሶች ላይ ሊከሰት ይችላል::
ምክንያቶቹም
•አልዛይመር እና ሌሎች የአዕምር ሴሎችን የሚያጃጁ ችግሮች ፤ የጭንቅላት ደም ስር ችግሮች (ስትሮክ..)፣የጭንቅላት እጢዎች : ጭንቅላት ላይ የሚደርስ አደጋ ፤ ኢንፌክሽኖች( HIV እና የመሳሰሉ)፣ የንጥረ ነገሮች መዛባት(ቪታሚን እና የመሳሰሉ)
የአልዛይመር በሽታ / Alzheimer Disease
አልዛይመር የማስታወስ ችሎታን፣ አስተሳሰብንና ባህሪን የሚጎዳ የመርሳት በሽታ (Dementia) አይነት ነው::
የእለት ተእለት ስራዎችን ለማደናቀፍ ምልክቶቹ ከጊዜ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋሉ:: የበሽታው የመጀመሪያ ምልክቶች የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ወይም ንግግሮችን መርሳትን ያካትታሉ:: በሽታው እየገፋ ሲሄድ የአልዛይመር በሽታ ያለበት ሰው ከፍተኛ የማስታወስ እክል ያጋጥመዋል እና የእለት ተእለት ተግባራትን የማከናወን አቅም ያጣል::
የአልዛይመርስ ህመም ስያሜውን ከየት አገኘ?
•ህመሙ መጠርያውን ያገኘዉ በጀርመናዊው የነርቭ ሀኪም አሎይስ አልዛይመር (1864-1915) ስም ነው። አሎይስ አልዛይመር በ1901 የመርሳት ችግር ያለባትን ሴት(አዉጉስቴ ዲተር) ሲያክም ቆይቶ ከ5 አመት በሁዋላ ህያወቷ ሲያልፍ በአንጎሏ ላይ የስነ-ደዌ(Pathology ምርመራ በማድረግ የነርቭ ሴሎቿ መሞት ምክንያት የሆነውን በአድ የፕሮቲን ክምችቶች (neurofibrillary tangles and neuritic plaques) ለመጀመረያ ጊዜ በመለየትና ህመሙንም “Presenile dementia” ብሎ በመሰየም በፅሁፍ መዝግቦ አስቀምጧል።በ1910 ለአልዛይመርስ መታሰቢያ እንዲሆን የቅርብ የስራ ባልደረባው የነበረው ዶ/ር ኤሊክራፕሊን የህመሙን መጠሪያ "የአልዛይመርስ ህመም" ሲል ሰይሞለታል።
ከመገለጫዎቹ ጥቂቶቹ
•የመናገር፣ የመረዳት እና ሀሳቦችን የመግለፅ፣ ወይም ማንበብ እና መጻፍ መቸገር ፤ የማስታወስ ችሎታ ማጣት ፤ ደካማ የማመዛዘን ችሎታ እና ግራ መጋባት ያስቀመጡትን እቃ መርሳት ፤ ገንዘብን በኃላፊነት መያዝ እና ሂሳቦችን በመክፈል ላይ ችግር ፤
የተለመዱ የዕለት ተዕለት ተግባራትን ለማጠናቀቅ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰድ ፤ በቅርብ የተፈጠሩ ነገሮችን አለማስታወስ (recent memory impairment) ፤ የእንቅልፍ መዛባት ፤ ብስጩ መሆን እንዲሁም ሰዎችን፣ ቦታዎችን መርሳት ሁኔታው እየበረታ ሲሄድ እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ ሲሆን የልጆቻቸውን ስም እስከ መርሳት ይጠቀሳሉ::
የአልዛይመር በሽታ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
•የአልዛይመር በሽታ ትክክለኛ መንስኤዎች ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደሉም።ነገር ግን በመሠረታዊ ደረጃ የአንጎል ፕሮቲኖች በመደበኛነት መስራት ይሳናቸዋል : ይህም የአንጎል ሴሎችን (ኒውሮንስ) ስራን የሚያውክ እና ተከታታይ መርዛማ ክስተቶችን ያስነሳል ፣ አንጎል በአደጋ ምክንያት መጎዳት ፣ በዕድሜ መግፉት (65 ከደረሱ በኋላ የአልዛይመርስ በሽታ የመያዝ እድሉ በየ 5 ዓመቱ በእጥፍ ይጨምራል) ፣ሁለት ሶስተኛ (2/3) የሚጠጉ የአልዛይመር ታማምሚዎች ሴቶች ሆነው ይታያል፤ የድም ቧንቧ ችግሮች ዋና ዋና የሚባሉ አጋላጮች እንደሆኑ ይገለጻል።
ከ 3 ሰዎች 2ቱ ዲሜንሺያ የተፈጥሮ ኡደት እና የጤናማ እርጂና ምልክት አድርገው ይመለከቱታል ፤ በዚህም ምክኛት ህመሙን ለመከላከል ማድረግ የምንችለው ምንም ነገር የለም ብለው ያምናሉ።
በመረጃዎች የተረጋገጠው እውነታ ግን አጋላጭ መንስኤዎችን በማስወገድ እና በመቆጣጠር 45 በመቶ የሚሆነው የዲሜንሺያ ህመምን መከላከል እና መዘግየት እንደሚቻል ነው።አኃዙ የሚያሳየው ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ እና በዲሜንሺያ ዙሪያ ያለው መገለል (stigma) ሰዎች መረጃ፣ ምክር፣ ድጋፍ እና የሕክምና እርዳታ እንዳይፈልጉ እንቅፋት እየሆነባቸው መሆኑን ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ሌሎች የጤና ድርጅቶች እንዳረጋገጡት ዕድሜ ትልቁ አደገኛ ሁኔታ ቢሆንም፣ ዲሜንሺያ ባዮሎጂያዊ እርጅናን ተከትሎ መምጣት ያለበት ነገር አይደለም፤ ለአደጋ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ እርምጃዎችም (ለምሳሌ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ማጨስን ማስወገድ፣ የደም ግፊትን መቆጣጠር) አሉ።
የዲመንሻ ህመምን በመራመድ እንከላከለው ይሆን?
• እድሜያቸው ከ40-79 አመት የሆኑ ሰዎች በየቀኑ 10,000 እርምጃን በመራመድ በዲመንሻ የመያዝ እድላቸውን በግማሽ መቀነስ እንደሚችሉ አዲስ ጥናት አሳየ። ነገር ግን ይህን ማድረግ ለማይችሉት በየቀኑ 4,000 እርምጃ መሄድ የህመሙን ተጋላጭነት በሲሶ (25%) መቀነስ እንደሚቻል ይሄው ጥናት አረጋግጧል።በተጨማሪም ከምንሄደው እርቀት ይበልጥ የምንራመድበት ፍጥነት ለአእምሮ ጤናና ዲመንሻን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለው ጥናቱ አመላክቷል። በዚህም መሰረት ለ30 ደቂቃ ያህል በፍጥነት (112 እርምጃዎችን በደቂቃ) መራመድ የዲመንሻ ተጋላጭነትን በ62 በመቶ ይቀንሰዋል።
• የእግር ጉዞ ለሁላችንም የሚመከር ቢሆንም የዲመንሻ ታማሚዎችም እንደ አቅማቸው እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ የህመሙን ጫና በመቀነስ የተሻለ ህያወት እንዲመሩም ያግዛቸዋል።
የምንበላው ምግብ ለዲመንሻ ተጋላጭ ያረገን ይሆን?
• በቅርብ በብራዚል ከ10ሺ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ለአስር አመት በተደረገ ጥናትና ክትትል የተቀነባበሩ ምግቦችን ማለትም የድንች ጥብስ፣ በርገር፣ ኬክ፣ ኩኪስ፣ ለስላሳ መጠጦችና አይስክሬም የመሳሰሉትን ከፍተኛ የስኳር፣ የጨውና የስብ መጠን ያላቸው ምግቦችን በየቀኑ በብዛት መመገብ (ቢያንስ አንድ ጊዜ) የአእምሯችንን የማሰብና የማሰላሰል አቅም በ28 በመቶ በመቀነስ ለዲመንሻ ህመም ተጋላጭነትን እንደሚጨምር አረጋግጧል። ስለሆነም በተቻለን አቅም መሰል ምግቦችን በመተው ጤናማ በሆኑ አትክልት፣ ፍራፍሬና ያልተፈተጉ ጥራጥሬዎች መተካት።የስጋና የስጋ ውጤቶችን መቀነስና ምግባችንን እራሳችን አብስለን መመገብ ጥሩ የጤና አማራጮች እንደሆኑ አጥኚዎቹ ይመክራሉ።
የዲመንሻ ህመምና የክብደት መቀነስ
ምክንያታዊ ያልሆነ የክብደት መቀነስና መክሳት ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት የዲመንሻ ታማሚዎች ላይ ይታያል።
•መረጃዎች እንደሚያሳዩት እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ያልተፈለገ የክብደት መቀነስ የዲመንሻ ህመም እየጀመረ ለመሆኑ አመላካች ሊሆን እንደሚችል ተረጋግጧል።
የአልዛይመርና መሰል የዲመንሻ ታማሚዎች ላይ የሚከሰት የክብደት መቀነስ መንስኤዎች በጥቂቱ:-
•እንዴትና መቼ ምግብ መብላት እንዳለባቸው ሲረሱ
• ከህመሙ ጋር የተያያዘ የባህሪ ለውጦች በተለይም ያለማቋረጥ መንቀሳቀስና እረፍት ማጣት ብዙ ሀይል እንዲያባክኑ ስለሚያደርጋቸው
•ምግብን የማሽተትና ጣእም የመለየት አቅም መቀነስ : ህመሙ እየባሰ ሲሄድ ለማላመጥና ለመዋጥ መቸገር
•የሰውነት የስብ መጠን መቀነስን ተከትሎ የምግብ ፍላጎትን የሚቆጣጠረው ሆርሞን (Leptin): ለዲመንሻ ህክምና የሚሰጡ (AChEI) የተባሉ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት (ማቀለሽለሽ፣ማስመለስ፣ ተቅማጥና የምግብ ፍላጎት መቀነስ) ለደምግፊት፣ለቁርጥማት፣ ለድብርት፣ ለስቃይ ማስታገሻ የሚሰጡ የተለያዩ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ተጓዳኝ የሆኑ የካንሰር፣ የውስጥ ደዌና የስነ አእምሮ ህመሞች መኖር እንደ መንስኤነት ይጠቀሳሉ::
የአልዛይመር በዘር የሚተላለፍ ነው?
• አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአልዛይመር በሽታ በዘር የመተላላፍ እድሉ ከ 60% እስከ 80% ነው::95% የአልዛይመር በሽታ በጊዜ ሂደት በሰውዬው ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ የጄኔቲክ : የአካባቢ እና የአኗኗር ዘይቤዎች ውጤት ነው::ከዕድሜ መግፋት ቀጥሎ፣ የቤተሰብ ታሪክ ለአልዛይመር በሽታ (AD) የመጋለጥ ሁለተኛው ትልቅ ምክንያት ነው።
የአልዛይመር በሽታ "ዓይነት 3 የስኳር በሽታ" ተብሎ ይጠራል። የሚጠራበት ምክንያት የአንጎል ሴሎች ኢንሱሊንን በአግባቡ መጠቀም ስለሚያቅታቸው (insuline resistance)(ልክ በዓይነት 2 የስኳር በሽታ ላይ እንደሚሆነው) ነው።
ዳውን ሲንድሮም እና አልዛይመር በሽታ (AD) መካከል ያለው ግንኙነት የዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ይልቅ በአልዛይመር በሽታ የመያዝ እድላቸው በጣም ከፍተኛ ሲሆን፣ በሽታውም ቀደም ብሎ በእድሜያቸው ይጀምራል።
1. የዘረመል (Genetic) ምክንያቱ፡-ክሮሞዞም 21 (Chromosome 21): ዳውን ሲንድሮም የሚከሰተው በሰውነት ውስጥ ካሉት ክሮሞዞም 21 አንዱ ተጨማሪ ቅጂ (ሦስተኛ ቅጂ) በመኖሩ ነው።
የ APP ጂን (The APP Gene): ይህ ክሮሞዞም 21 ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የአልዛይመር በሽታን ከሚያስከትሉ ዋና ፕሮቲኖች አንዱ የሆነውን "Amyloid Precursor Protein (APP)" የሚያመርተውን ጂን ይዟል።
የፕሮቲን ክምችት (Plaque Buildup): ተጨማሪ የ APP ጂን ቅጂ በመኖሩ ምክንያት፣ የዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች አንጎል ከፍተኛ መጠን ያለው ቤታ-አሚሎይድ (Beta-Amyloid) ፕሮቲን ያመርታል። ይህ ፕሮቲን በአንጎል ውስጥ ተከማችቶ "ፕላክስ" (Plaques) የሚባሉትን የአልዛይመር መለያ ምልክቶችን ይፈጥራል።
2. የበሽታው መጀመሪያ ዕድሜ፡-በ40 ዓመት አካባቢ: ዳውን ሲንድሮም ካላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በ40 ዓመት ዕድሜያቸው ገደማ የአልዛይመር በሽታ መለያ የሆኑትን የአንጎል ለውጦች (ፕላክስ እና ታንግልስ) ማሳየት ይጀምራሉ።
የበሽታው ምልክቶች: የአልዛይመር ምልክቶች (እንደ የመርሳት እና የአስተሳሰብ ችግር) የሚጀምሩት በአብዛኛው በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ ነው። ይህ በአጠቃላይ ህዝብ ላይ አልዛይመር ከሚታይበት ዕድሜ (ከ65 ዓመት በላይ) በጣም ቀደም ያለ ነው።
3. የምርመራ ፈተናዎች፡-የዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ከመጀመሪያውም የአእምሮ ዝግመት (Intellectual Disability) ስለሚኖራቸው፣ የአልዛይመር በሽታ መጀመሩን መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ቡድን ውስጥ የአልዛይመር የመጀመሪያ ምልክቶች የማስታወስ ችሎታ ከመጥፋት ይልቅ በባህሪ ለውጥ፣ በማኅበራዊ ተሳትፎ መቀነስ እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ችሎታ ማጣት ሊገለጡ ይችላሉ።
የዲመንሻና የአልዛይመር ህመም በህክምና እንዴት ይለያል ?
• ህክምናው የሚጀምረው ታማሚው ወይም በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች (ባለቤት፣ ልጆች : ዘመድ ፣ የስራ ባልደረባ...) በፊት ያልነበረ የባህሪ፣ የአስተሳሰብ ፣ የቋንቋና የማስታወስ ችሎታ ለውጥ በግለሰቡ ላይ በሚያዩበትና ወደ ህክምና በሚመጡበት ጊዜ ነው።
•የጤና ባለሙያውም የህመሙን ምልክቶችና አጋላጭ መንስኤዎቹን በዝርዝር በመጠየቅ ፣ የስነ-ኣእምሮ፣የማስታወስና የቋንቋ ችሎታ ፈተናዎች፣ የጠቅላላና የነርቭ የአካል ምርመራ በማድረግ በሽታዉ መኖሩን ለማወቅ ይሞክራል።
• በተጨማሪም የደም ናሙና፣የአንጎን ምስል (MRI, CT, PET) ፣ ከአከርካሪ የሚወሰድ ፈሳሽ (CSF analysis) ፣ የአልዛይመር መንስኤ ፕሮቲኖች (bio markers) እና የዘረመል ምርመራ በማድረግ የአልዛይመር ህመምና መሰል የዲመንሻ በሽታ መኖሩንና መንስኤውን ለማረጋገጥ ይቻላል።
•በነኚህ ውጤቶች መሰረት የጤና ባለሙያው አስፈላጊውን የመድሀኒት፣ የስነልቦናና የጤና ክትትል ይጀምራል።
የአልዛይመር በሽታ ሕክምናው ምንድነው?
የአልዛይመር በሽታ ሕክምናዎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡ በመድኃኒቶች (Medications) እና በድጋፍ ሰጪ እንክብካቤ (Supportive Care)።
1. የምልክት ማስታገሻ መድኃኒቶች (Symptom-Managing Drugs):-እነዚህ መድኃኒቶች በአንጎል ውስጥ ያሉትን የመማር እና የማስታወስ ችሎታን የሚቆጣጠሩ ኬሚካሎችን (ኒውሮትራንስሚተሮችን) ሚዛን በማስተካከል ይሰራሉ።
ሀ. ኮሊንኤስተሬዝ መከላከያዎች (Cholinesterase Inhibitors)
•እነዚህ መድኃኒቶች መለስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ ለሚገኝ የአልዛይመር ህመም ተጠቂዎች ሲሆን የምንጠቀማቸዉ : እነዚህ መድኃኒቶች ስራቸው ለአንጎል አስፈላጊ የሆነው አሴቲልኮሊን (Acetylcholine) የተባለውን ኬሚካል ተግባር እንዳይስተጓጎል በማድረግ መጠኑን መጨመር ሲሆን። ይህ ደግሞ የአስተሳሰብ እና የማስታወስ ችሎታን ለጊዜው እንዲሻሻል ወይም እንዳይባባስ ሊያደርግ ይችላል።
ለምሳሌ ያህል: እንደ ዶኔፔዚል (Donepezil)፣ ሪቫስቲግሚን (Rivastigmine)፣ ጋላንታሚን (Galantamine)....
ለ. NMDA ተቀባይ ተቃዋሚ (NMDA Receptor Antagonist)
•እነዚህን መድኃኒቶች ለመካከለኛ እና ለከፋ ደረጃ የአልዛይመር በሽታ እንጠቀማቸዋለን::
•እነዚህ መድኃኒቶች (ለምሳሌ:-ሜማንታይን Memantine) ከመጠን በላይ የሆነ ግሉታሜት (Glutamate) የተባለ ኬሚካል በነርቭ ሴሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በመከላከል ይሰራሉ።አንዳንድ ጊዜ ሜማንታይን ከኮሊንኤስተሬዝ መከላከያ ጋር ተደምሮ ይሰጣል።
2. የበሽታውን ሂደት የሚያዘገዩ መድኃኒቶች (Disease-Modifying Therapies - አዲስ ሕክምናዎች)
እነዚህ ሕክምናዎች የአልዛይመር በሽታ ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ በሚታሰበው ቤታ-አሚሎይድ (Beta-Amyloid) ፕሮቲን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።
አሚሎይድ-ተኮር ፀረ እንግዳ አካላት (Anti-amyloid monoclonal antibodies):
እነዚህ መድኃኒቶች (ለምሳሌ፦ Lecanemab(Leqembi) እና Donanemab) በአንጎል ውስጥ የተከማቹትን አሚሎይድ ፕላኮች (Plaques) በማስወገድ ወይም እንዳይከማቹ በመከላከል የበሽታውን እድገት ሊያዘገዩ ይችላሉ። በአብዛኛው የሚሰጡት መለስተኛ የግንዛቤ እክል (MCI) ወይም በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ላሉ የአልዛይመር ታካሚዎች ነው።
3.ከመድሐኒት ውጪ ያሉ ህክምናዎች እና ድጋፍ ሰጪ እንክብካቤዎች
እነዚህ እንክብካቤዎች በመድሐኒት ከሚሰጡት ህክምናዎች ጎን ለጎን የዕለት ተዕለት ኑሮን ለማሻሻል ይረዳሉ።
•የዕውቀት ማነቃቂያ ሕክምና (Cognitive Stimulation Therapy): አእምሮን የሚያነቃቁ እንቅስቃሴዎችን (እንደ ጨዋታዎች፣ እንቆቅልሾች፣ ውይይቶች) መጠቀም።
•የባህሪ አስተዳደር (Behavioral Management): ግራ መጋባት፣ ድብርት፣ ጭንቀት ወይም ጠበኛነት ሲከሰት መንስኤዎችን ለይቶ በመረዳት እና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ባህሪን ማስተዳደር።
•አካባቢያዊ ማሻሻያ (Environmental Modifications): ግራ መጋባትን የሚቀንሱ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተደራጀ የቤት አካባቢ መፍጠር (ለምሳሌ የቀን መቁጠሪያዎችን ወይም አስታዋሾችን መጠቀም)።
•ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ: መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ሚዛናዊ አመጋገብ እና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን መጠበቅ ለአንጎል ጤና ወሳኝ ናቸው::
አስፈላጊ ማሳሰቢያ: እነዚህ ሕክምናዎች በአንዳንድ ሰዎች ላይ የአንጎል እብጠት (swelling) ወይም ደም መፍሰስ የመሰሉ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትሉ ስለሚችሉ በጥንቃቄ ክትትል ያስፈልጋቸዋል።
የአልዛይመርና የዲመንሻ ህመምን በጋራ እንከላከል፣ ህሙማንንና ቤተሰቦቻቸው እናግዝ እንንከባከብ።


