የሚያለቅስን ህፃን ዝም ለማስባል ነቅንቀው ያውቃሉ? ይህ በሕፃኑ ጭንቅላት ውስጥ ደም እንዲፈስ ሊያደርግ እንደሚችልስ?
በእንግሊዘኛ አጠራሩ Shaken baby syndrome ይባላል፡፡
ይህ በሽታ የሚከሠተው ሕፃናት ሲያለቅሱ ወይም ሲያስቸግሩ ወላጅ ንዴቱን እና ጭንቀቱን መቆጣጠር አቅቶት ሕፃኑን በሀይል በሚነቀንቅበት ጊዜ የሕፃኑ አንጐል ከራስ ቅሉ ጋር በመጋጨት በጭንቅላት ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች ላይ ጉዳትን በማስከተል ጭንቅላት ውስጥ ደም እንዲፈስ በማድረግ ነው። ይህ ደም ቀስ በቀስ ተጠራቅሞ ኦንጐልን በሚጫንበት ጊዜ ሕፃኑ የተለያዩ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል።
ምልክቶቹ
- ከወትሮው የበዛ እንቅልፍ እና ሕፃኑ ሲቀሰቅሱት አለመነሳት
- ማስመለስ - የሚገፈተር አይነት
- ከመጠን ያለፈ መነጫነጭ
- ለመተንፈስ መቸገር
- ጡት አለመጥባት እንዲሁም
- አንገትን ለመደገፍ መቸገር የመሳሰሉት ምልክቶች ይኖሩታል።
ተያይዘው የሚመጡ የረጅም ጊዜ ችግሮች
- የሚጥል በሽታ (seizure)
- የማየት እና የመስማት ችግር
- የሰውነት መስነፍ (Paralysis)
- የእድገት መዘግየት
- ቋሚ የሆነ የአእምሮ ጉዳት እንዲሁም
- ሞት ሊያስከትል ይችላል
እንዴት እንከላከለው?
- ህጻናት የሚያለቅሱት ፍላጐታቸው እንዲሟሉላቸው እንደሆነ መገንዘብ :: ይህም ተፈጥሮአዊ መሆኑን መረዳት።
- ሕፃናትን የሚንከባከቡ ከሆነ በተቻለ መጠን በቂ እረፍት ማድረግ። እንዲሁም በአቅራቢያዎ ቤተሰብ ካለ እርዳታ መጠየቅ
- ሕፃናትን ከመነቅነቅ መቆጠብ
- ስለ በሽታው ሌሎችን ማስተማር
ይህ በሽታ ሕፃኑ ህይወቱን ሊያበላሹ የሚችሉ ዘላቂ ጠባሳዎችን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትል ስለሚቻል ህፃናትን ከመነቅነቅ መቆጠብ ያስፈልጋል።



