የአባላዘር በሽታ እና እርግዝና

Biruh Tesfaye
Nov 27, 2025
undefined

የአባላዘር በሽታዎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ናቸው። የአባላዘር በሽታዎች በአፍ፣ በፊንጢጣ ወይም በብልት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች አማካኝነት ሊተላለፉ ይችላሉ። በተጨማሪም በሰውነት ፈሳሾች አማካኝነትም ይተላለፋሉ።

ከተለመዱት የአባላዘር በሽታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • የብልት ኪንታሮት (Genital wart/human papillomavirus - HPV)
  • ጨብጥ (gonorrhea)
  • ክላሚዲያ (chlamydia)
  • ቂጥኝ (syphilis)
  • የብልት ሄርፒስ (genital herpes)
  • ኤች አይ ቪ/ኤድስ (HIV/AIDS)
  • የጉበት ቫይረስ (Hepatitis B)
  • ትሪኮሞኒያሲስ (Trichomoniasis)

እንደ አባላዘር በሽታ ባይመደቡም፣ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር ሊያያዙ የሚችሉ ሌሎች ኢንፌክሽኖችም አሉ፤ እነሱም፦

  • የብልት ፈንገስ ኢንፌክሽን (thrush)
  • ባክቴሪያል ቫጂኖሲስ (bacterial vaginosis)
  • የብልት ቅማል ('crabs'/pubic lice)
  • እከክ (scabies)

ነፍሰ ጡር ከሆኑ በአባላዘር በሽታ ሊያዙ ይችላሉ? አዎ፣ ነፍሰ ጡር ከሆኑ በአባላዘር በሽታ ሊያዙ ይችላሉ። እርግዝና ከአባላዘር በሽታ ምንም ዓይነት ተጨማሪ የመከላከል ሽፋን አይሰጥም። እንደውም፣ ነፍሰ ጡር ስለሆኑ ብቻ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት እንደ ኮንዶም ያሉ የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ካቆሙ፣ በአባላዘር በሽታ የመያዝ እድልዎን ሊጨምሩ ይችላሉ።

የአባላዘር በሽታዎች ነፍሰ ጡር ቢሆኑም ባይሆኑም ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ከባድ በሽታዎች ናቸው። ነገር ግን ነፍሰ ጡር ሲሆኑ፣ አደጋ ላይ ያለዎት እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ ለልጅዎ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ የአባላዘር በሽታዎች በእርግዝና ወቅት እና በጡት ማጥባት አማካኝነት ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፉ ይችላሉ። 

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?

አንዳንድ ጊዜ፣ የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ላይኖሩ ይችላሉ። ውስብስብ ችግሮችን እስኪያመጣ ወይም የግብረ ሥጋ አጋርዎ እስኪመረመር ድረስ እንዳለብዎ ላያውቁ ይችላሉ። ምልክቶች ከታዩ ግን የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፦

  • ሽንት በሚሸኑበት ጊዜ ህመም ወይም የማቃጠል ስሜት
  • ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት ወይም የሽንት ቀለም መቀየር 
  • የብልት ወይም የብልት አካባቢ ማሳከክ
  • ከብልት የሚወጣ ያልተለመደ ፈሳሽ መኖር
  • በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት የሚሰማ ህመም መኖር
  • በአፍ፣ በፊንጢጣ፣ በብልት አካባቢ እብጠቶች፣ ቁስሎች ወይም ኪንታሮቶች መኖር
  • የቆዳ ሽፍታ መኖር (ህመም ያለው ወይም የሌለው ሊሆን ይችላል)
  • ከወር አበባ ውጪ ከሴት ብልት ደም መፍሰስ።
  • ትኩሳት፣ ማላብ እና ብርድ ብርድ ማለት
  • የቆዳ ቢጫ መሆን 
  • የአይን ኢንፌክሽኖች መኖር
  • ክብደት መቀነስ

ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ብዙዎቹ በአጠቃላይ ከእርግዝና ጋር ሊዛመዱ ስለሚችሉ፣ መንስኤው ምን እንደሆነ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

በእርግዝና ወቅት የአባላዘር በሽታዎች እንዴት ይመረመራሉ?

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ቢኖርዎትም ባይኖርዎትም በእርግዝናዎ መጀመሪያ ላይ ሙሉ የአባላዘር በሽታ ምርመራ ሊያደርጉ ይችላሉ። የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል (CDC) በእርግዝና የመጀመሪያ ክትትል ላይ የአባላዘር በሽታ ምርመራ እንዲደረግ ይመክራል። በተጨማሪም፣ የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊ ከሆነ ወደ ወሊድ በሚጠጋ ጊዜ ምርመራውን ይደግማሉ።

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ካለብዎ ወይም በእርግዝናዎ ወቅት የአባላዘር በሽታ ሊይዝዎት ይችላል ብለው ከጠረጠሩ፣ በዚያን ጊዜም እንደገና ሊመረመሩ ይችላሉ። በሽታው ሊኖርበት ከሚችል ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ካደረጉ፣ በሚቀጥሉት ቀጠሮዎችዎ ላይም ምርመራ ተደርጎልዎት ሕክምና ያስፈልግዎታል። ለአባላዘር በሽታ እንደተጋለጡ ከጠረጠሩ፣ ወዲያውኑ ለሐኪምዎ መንገርዎን ያረጋግጡ። በእርግዝናዎ በማንኛውም ጊዜ ለአባላዘር በሽታ ምርመራ ማድረግ ይችላሉ።

የምርመራው ዓይነት በአባላዘር በሽታው ዓይነት የሚወሰን ቢሆንም፣ ምርመራዎች ብዙውን ጊዜ ከሚከተሉት አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ያካትታሉ፦

  • የደም ምርመራ 
  • የሽንት ምርመራ
  • ከብልት የሚወሰድ ናሙና
  • አካላዊ ምርመራ 

የአባላዘር በሽታ ልጅዎን እንዴት ሊጎዳ ይችላል?

አንዳንድ የአባላዘር በሽታዎች በእርግዝና ወቅት እና በጡት ማጥባት አማካኝነት ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፉ ይችላሉ። እንደ ቂጥኝ ያሉ፣ የእንግዴ ልጅን (placenta) አቋርጠው ማህፀን ውስጥ ያለውን ሕፃን ሊበክሉ ይችላሉ። እንደ ጨብጥ፣ ክላሚዲያ፣ የብልት ሄርፒስ፣ ሄፓታይተስ ቢ እና የብልት ኪንታሮት ያሉ ደግሞ ሕፃኑ በሚወለድበት ጊዜ/ በምጥ ጊዜ ከእናት ወደ ሕፃን ሊተላለፉ ይችላሉ።ኤች.አይ.ቪ በእርግዝና ወቅት የእንግዴ ልጅን አቋርጦ ሊያልፍ እና በወሊድ ጊዜ ሕፃኑን ሊበክል ይችላል።

የአባላዘር በሽታ ከእናት ወደ ሕፃን ሲተላለፍ በሕፃኑ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጎጂ ውጤቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • ሲወለዱ ዝቅተኛ ክብደት መኖር (ኪሎው ከ2.5 ኪ.ግ በታች መሆን)
  • የአይን ኢንፌክሽን
  • ዓይነ ስውርነት
  • የሳንባ ምች (Pneumonia)
  • በሕፃኑ ደም ውስጥ ኢንፌክሽን
  • የአእምሮ ጉዳት
  • መስማት አለመቻል
  • የማጅራት ገትር በሽታ (Meningitis)
  • ሥር የሰደደ የጉበት በሽታ፣ ይህም ወደ ጉበት ጠባሳ (ሲርሆሲስ/cirrhosis) ሊያመራ ይችላል
  • ከመወለዱ በፊት የልጁ ህይወት ማለፍ (Stillbirth) ወይም በጨቅላነት ጊዜ ሞት

በእርግዝናዎ ወቅት መደበኛ የሕክምና ክትትል ማግኘት እና ከሐኪምዎ ወይም ከአዋላጅዎ ጋር ስለ የአባላዘር በሽታዎች መወያየት በእርግዝና ወቅት በአባላዘር በሽታዎች ምክንያት የሚመጡ የችግሮችን አደጋ ለመቀነስ ይረዳል።

የአባላዘር በሽታ በእርግዝና ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

የአባላዘር በሽታዎች ነፍሰ ጡር በሆኑ ሴቶች ላይ፣ ነፍሰ ጡር ባልሆኑ ሴቶች ላይ እንደሚያደርሱት ሁሉ ተመሳሳይ የጤና ችግሮች ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም በእርግዝና ወቅት በአባላዘር በሽታ መያዝ የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል፦

  • ያለጊዜው መውለድ (Premature labor)፦ ከ37 ሳምንታት እርግዝና በፊት ምጥ ሲጀምር የሚከሰት ሲሆን የጨቅላ ሕፃናት ሞት ዋነኛው መንስኤ ሲሆን፣ በልጆች ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የእድገት እና የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።  
  • ከወሊድ በኋላ በማህፀን ውስጥ ኢንፌክሽን መከሰት

በተጨማሪም የአባላዘር በሽታ የመውለድ አቅም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

በእርግዝና ወቅት ለአባላዘር በሽታ የሚሰጠው ሕክምና ምንድነው?

በእርግዝና ወቅት ለአባላዘር በሽታ የሚሰጠው ሕክምና የሚወሰነው በኢንፌክሽኑ አይነት፣ ኢንፌክሽኑ ምን ያህል እንደገፋ እና እርግዝናው ምን ያህል እንደደረሰ ላይ ነው። 

  • ለባክቴሪያ የሚደረግ ሕክምና: እንደ ክላሚዲያ፣ ጨብጥ እና ቂጥኝ ያሉ በባክቴሪያ የተከሰቱ የአባላዘር በሽታዎች በመርፌ በሚሰጥ ወይም በአፍ በሚዋጥ ፀረ ባክቴሪያ ሊታከሙ ይችላሉ። ሐኪምዎ በእርግዝና ወቅት ለመውሰድ ደህንነታቸው የተጠበቁ ፀረ ባክቴሪያ ያዝዛሉ።
  • ለቫይረስ የሚደረግ ሕክምና: እንደ የብልት ሄርፒስ፣ ሄፓታይተስ ቢ ወይም ኤች.አይ.ቪ ያሉ ቫይረስ ያሉ የአባላዘር በሽታዎች ፈውስ የላቸውም። ሆኖም፣ ፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ምልክቶችን መቆጣጠር እና ኢንፌክሽኑ ወደ ልጅዎ የመተላለፍ አደጋን ሊቀንሱ ይችላሉ።

ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት የአባላዘር በሽታ ለማከም ከተሰጠዎ፣ ምልክቶቹ ቢጠፉም እንኳ ሁሉንም መድሃኒትዎን ወስዶ መጨረስ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም፣ በሽታዎን ለማከም የሌላ ሰው መድሃኒት በፍጹም መውሰድ የለብዎትም። ይህን ማድረግዎ ኢንፌክሽኑን ለማከም አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል። በተመሳሳይ፣ መድሃኒትዎን ለሌሎች ማጋራት የለብዎትም።

በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የአባላዘር በሽታዎች እና ተፅእኗቸው

በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የአባላዘር በሽታ እንደ ኢንፌክሽኑ ዓይነት እርስዎንና እያደገ ያለውን ልጅዎን ሊጎዱ ይችላሉ።

1. ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ (HIV/AIDS)

ውጠታማ መድሃኒቶች በመፈጠራቸው ምክንያት ኤች.አይ.ቪ ወደ ልጅዎ የመተላለፍ እድሉ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ወይም ሊከላከል ይችላል። ነገር ግን በሽታው ወደ ሕፃኑ ሲተላለፍ የሚያስከትለው ውጤት ከባድ ነው፣ ሕፃኑ ኤች.አይ.ቪ ሊይዘው ይችላል።  የኤች.አይ.ቪ የመያዝ ዕድል በተለይ ከመፀነስ በፊት ፣ በእርግዝና ወቅት እና ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ነው። 

ሕክምና: የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠንን በጣም ዝቅተኛ ደረጃ (undetectable viral load) ድረስ ለመቀነስ የሚረዱ መድሃኒቶችን በመውሰድ ቫይረሱ ወደ ሕፃኑ እንዳይተላለፍ መከላከል ይቻላል።ፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ኤች.አይ.ቪ ወደ ልጅዎ የመተላለፍ እድልን ከ1% በታች እንዲቀንስ ያደርጋሉ። በተጨማሪም እንደ ቫይረስ መጠኑ በቀዶ ጥገና እንዲወልዱ ሊደረግ ይችላል።

2. የብልት ሄርፒስ (Herpes)

በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ የሄርፒስ ኢንፌክሽን እስከሚወልዱበት ጊዜ ድረስ ወደ ልጂ የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ ነው። በብልት ላይ የሚታዩ የሄርፒስ ቁስሎች በጣም ተላላፊ በመሆናቸው ሕፃኑ ሲወለድ ሊበክሉት ይችላሉ። ከሄርፒስ ጋር ንክኪ ያላቸው ሕፃናት በአይናቸውና በማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓታቸው ላይ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። በአራስ ሕፃን ውስጥ ያለ የሄርፒስ ኢንፌክሽን ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል።

ሕክምና: ሐኪምዎ ቁስሎችን ለማከም የፀረ-ቫይረስ ክኒኖችን ሊያዝል ይችላል። በወሊድ ጊዜ የሄርፒስ ቁስሎች ያለባቸው ሴቶች ኢንፌክሽኑ ወደ ሕፃኑ እንዳይተላለፍ ለመከላከል በቀዶ ጥገና (C-section) የመውለድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። 

3. ጨብጥ (Gonorrhea)

ጨብጥ በጣም የተለመደ የአባላዘር በሽታ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ከብልት ፈሳሽ ናሙና በመውሰድ ይመረመራል። በእርግዝና ወቅት ከያዘ፣ ኢንፌክሽኑ የብልት ፈሳሽ፣ በሚሸኑበት ጊዜ የማቃጠል ስሜት ወይም የሆድ ህመም ሊያስከትል ይችላል። ጨብጥ ያለበት ነፍሰ ጡር ሴት የፅንስ መጨንገፍ ወይም ያለጊዜው መውለድ የመጋለጥ እድሏ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሕፃኑ ዓይነ ስውርነት፣ የመገጣጠሚያ ኢንፌክሽን ወይም ለሕይወት አስጊ የሆነ የደም ኢንፌክሽን ሊያጋጥመው ይችላል።

ሕክምና: ነፍሰ ጡር ሴቶች በፀረ ባክቴሪያ ይታከማሉ። ጨብጥ ብዙውን ጊዜ ምልክት ስለማያሳይ፣ ኢንፌክሽኑ በአይን ላይ እንዳይከሰት ለመከላከል ሁሉም አዲስ የተወለዱ ሕፃናት በተወለዱበት ጊዜ በአይናቸው ውስጥ መድኃኒት ይሰጣቸዋል።

4. የብልት ኪንታሮት (Genital Warts)

የብልት ኪንታሮት ብዙ ጊዜ እንደ አበባ ጎመን ቅርጽ ያላቸው እብጠቶች በብልት ላይ የሚታዩ ሲሆን ሊያቃጥሉ ወይም ሊያሳክኩ ይችላሉ። አልፎ አልፎ፣ የእርግዝና ሆርሞኖች ኪንታሮቱ እንዲያድግ ያደርጉና የወሊድ ትቦን ሊዘጉ ይችላሉ። ከዘጋ፣ ሕፃኑ በቀዶ ጥገና እንዲወለድ ሊያስፈልግ ይችላል።

ሕክምና: በእርግዝና ወቅት የብልት ኪንታሮት ከያዘ፣ ሕክምናው እስከሚወልዱ ድረስ ሊዘገይ ይችላል። ቫይረሱ ሰውነትን ባይለቅምም፣ ኪንታሮቶቹ በቀዶ ጥገና ወይም በመድሃኒት ሊታከሙ ይችላሉ። ትናንሽ ኪንታሮቶች ሕክምና ባያስፈልጋቸውም፣ ትልልቅና የሚያስቸግሩት በአሲድ ኬሚካል በመጠቀም በማቃጠል ወይም በመቁረጥ ሊወገዱ ይችላሉ። ነገር ግን የወሊድ ትቦን ከዘጋ፣  በቀዶ ጥገና እንዲወለድ ሊያስፈልግ ይችላል።

5. ክላሚዲያ (Chlamydia)

ክላሚዲያ የፅንስ መጨንገፍ እና ያለጊዜው መውለድ የመጋለጥ እድልን ሊጨምር ይችላል። ኢንፌክሽኑ ለተጋለጡ አራስ ሕፃናት ከባድ የአይን ኢንፌክሽኖች እና የሳንባ ምች (pneumonia) ሊያጋጥማቸው ይችላል። ኢንፌክሽኑ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ከ3 ወራት በኋላ እንደገና መመርመርዎን ያረጋግጡ።

ሕክምና: በእርግዝና ወቅት እናቶች በፀረ ባክቴሪያ ይታከማሉ። አራስ ሕፃናት ላይ የሚከሰተውን የአይን ኢንፌክሽን ለመከላከል የአይን መድሃኒት ይደረገታል፤ ሆኖም ግን በኋላ ላይ ሊከሰት የሚችለውን የሳንባ ምች መከላከል አይችልም። doxycycline የተባለው ፀረ ባክቴሪያ የሕፃኑን ጥርስ ቀለም ሊቀይር ስለሚችል በእርግዝና ወቅት መጠቀም የለብዎትም።

6. ቂጥኝ (Syphilis)

ቂጥኝ ብዙ ጊዜ በደም ምርመራ ይታወቃል። ቂጥኝ ወደ ልጅዎ በቀላሉ ይተላለፋል እና ለሕፃኑ ገዳይ ሊሆን የሚችል ከባድ ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል። እነዚህ ህጻናት ብዙውን ጊዜ ያለጊዜው ይወለዳሉ። በሕይወት የሚተርፉ ያልታከሙ ሕፃናት እንደ አንጎል፣ አይኖች፣ ጆሮዎች፣ ልብ፣ ቆዳ፣ ጥርሶች እና አጥንቶች ባሉ በርካታ የአካል ክፍሎች ላይ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ሕክምና: ኢንፌክሽኑ ወደ ልጅዎ የመተላለፍ ስጋትን ለመቀነስ እና ቂጥኙ በእርስዎ ውስጥ እንዳይባባስ ለመከላከል ሐኪምዎ በእርግዝናዎ ወቅት ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት ያዝልዎታል።

7. ሄፓታይተስ ቢ (Hepatitis B)

ሄፓታይተስ ቢ በቫይረስ የሚመጣ የጉበት ኢንፌክሽን ነው። ነፍሰ ጡር ሴቶች በሄፓታይተስ ቢ ከተያዙ፣ 40% ያህሉ ኢንፌክሽኑን በእንግዴ ልጅ በኩል ወደ ሕፃናቸው ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ከዚያም ልጁ በሄፓታይተስ ቢ ሊያዝ ይችላል፣ ይህም ወደ ጉበት በሽታ እና ለሞት ሊያመራ ይችላል። 

ሕክምና: ሄፓታይተስ ቢ ካለብዎ፣ ሕፃኑ ኢንፌክሽን እንዳይይዘው ለመከላከል እና እርሶም ላይ የቫይረሱን መጠን ለመከነስ ሐኪምዎ የፀረ ቫይረስ መድሃኒት ይሰጥዎታል። አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ከወሊድ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ሄፓታይተስ ቢ ለመከላከል የሚሰጡ መድኃኒቶችም/ክትባቶች አሉ።

8. ትሪኮሞኒየስ (Trichomoniasis)

ትሪኮሞኒየስ ቢጫ ወይም አረንጓዴ የብልት ፈሳሽ እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም በሚሸኑበት ጊዜ ህመም ሊያስከትል የሚችል ኢንፌክሽን ነው። ያለጊዜው የመውለድ አደጋን ሊጨምር ይችላል። አልፎ አልፎ፣ አዲስ የተወለደ ሕፃን በወሊድ ጊዜ በኢንፌክሽኑን ሊያዝ እና ከተወለደ በኋላ የብልት ፈሳሽ ሊኖረው ይችላል። 

ሕክምና: ነፍሰ ጡር ሴቶች ኢንፌክሽኑን የሚፈውስ መድሃኒት ይሰጣቸዋል። በድጋሚ እንዳይያዙና በሽታው እንዳይሰራጭ ለመከላከል ባልደረባዎም በተመሳሳይ ጊዜ መታከም አለበት። ኢንፌክሽኑ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ከታከሙ በኋላ በ3 ወር ውስጥ እንደገና ምርመራ ያድርጉ።

የአባላዘር በሽታዎችን እንዴት መከላከል ይችላሉ?

ከአባላዘር በሽታዎች እራስዎን ለመጠበቅ መውሰድ የሚችሏቸው መሠረታዊ እርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው፦

  • የግብረ ሥጋ ግንኙነት አለማድረግ፦ የግብረ ሥጋ አጋሮችዎ የአባላዘር በሽታ ምርመራቸው ነጻ መሆኑን እስኪረጋገጥ ድረስ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከመፈጸም ይቆጠቡ
  • ኮንዶም ይጠቀሙ፦ በተለይም ከአንድ በላይ የግብረ ሥጋ አጋር ካለዎት በየጊዜው ኮንዶም ይጠቀሙ።
  • የግብረ ሥጋ አጋሮችን ይገድቡ፦ የግብረ ሥጋ አጋሮችዎን ቁጥር መገደብ የአባላዘር በሽታ የመያዝ እድልዎን ይቀንሳል። ይህ ማለት ከአንድ ሰው ጋር ብቻ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ማለት ነው። አደጋውን ለመቀነስ ያ ሰውም ከእርስዎ ጋር ብቻ ግንኙነት ማድረግ አለበት።
  • የግብረ ሥጋ አጋሮችን በጥንቃቄ ይምረጡ፦ የአባላዘር በሽታ ሊኖረው ይችላል ብለው ከጠረጠሩት ወይም ብዙ የግብረ ሥጋ አጋሮች ካሉት ሰው ጋር ግንኙነት አያድርጉ።
  • ለአባላዘር በሽታ ምርመራ ያድርጉ፦ በእርግዝና መጀመሪያ ላይ ምርመራ ማድረጎት በኋላ ላይ ሌላ ኢንፌክሽን አይይዝዎትም ማለት አይደለም። ከመጨረሻው የአባላዘር በሽታ ምርመራዎ በኋላ ከአንድ በላይ አጋር ካለዎት እንደገና ምርመራ ማድረግ ያስፈልግዎታል።
  • አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ አይጠቀሙ፦ በስካር ጊዜ ወይም አደንዛዥ ዕፅ በሚወሰዱ ጊዜ ደህንነቱ የተጠበቀ ወሲብ የመፈፀም ዕድልዎ ሊቀንስ ይችላል። በተጨማሪም አልኮል እና አደንዛዥ ዕፅ እየተፈጠረ ያለውን ልጅዎን ሊጎዳ ይችላል።
  • የአባላዘር በሽታ ምልክቶችን ይወቁ፦ በራስዎ እና በግብረ ሥጋ አጋሮችዎ ላይ ምልክቶችን ይከታተሉ። የበለጠ ባወቁ ቁጥር፣ እራስዎን በተሻለ ሁኔታ መከላከል ይችላሉ።
  • ህክምና በአግባቡ ያድርጉ፦ሐኪምዎ ያዘዘልዎትን ሕክምና በአግባቡ ይከተሉ።
  • ክትባት ይውሰዱ፦ በኤች.ፒ.ቪ (HPV) እና በሄፓታይተስ ክትባት ይውሰዱ።
  • ግርዛት (ለወንዶች)፦ ወንድ ከሆኑ፣ መገረዝ በአንዳንድ የአባላዘር በሽታዎች የመያዝ እድልዎን ሊቀንስ ይችላል።

 

Comments (0)