ጨቅላ ልጅዎ እንደራበው ወይም እንደጠገበ የሚያውቁባቸው ምልክቶች
ልጅዎ ሲርበው እና ሲጠግብ የሚያሳየቸውን ምልክቶች መረዳት ልጅዎን መቼና ምን ያህል ጊዜ መመገብ እንዳለብዎ ለማወቅ ይረዳዎታል።
ልጅዎ መናገር ከመቻሉ በፊትም እንኳ ድምፆችንና እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም የረሃብ ወይም የጥጋብ ምልክቶችን ያሳያል። ማልቀስ ብዙውን ጊዜ ዘግይቶ የሚከሰት የረሃብ ምልክት ነው። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ሌሎች የረሃብ ምልክቶች በመመልከት ልጅዎ ገና ተረጋግቶ እያለ ጡት ወይም ጡጦ መስጣት ይችላሉ።
ህፃናት የረሃብ ስሜት ሲሰማቸው ከሚያሳዩአቸው የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
- የበለጠ ንቁ መሆን (ስለ ምግብ ማሰብ ሕፃናትን ያነቃቃቸዋል)
- ራሳቸውን ወደ ጎን ማዘንበል ፤ ምግብ እንደሚፈልግ ሰው ራሳቸውን ወደ ግራና ቀኝ ያዞራል ።
- አፉቸውን መክፈትና መዝጋት (ጎጆ ውስጥ ወላጆቻቸውን እንደሚጠብቁ ትንንሽ አእዋፋት አፋቸውን ይከፍታሉ ፣ ይዘጋሉ)
- ጭንቅላታቸውን ወደ ጡትዎ፣ደረትዎ ወይም ወደ ጡጦ ማዞር።
- በአፋቸው የመጥባት እንቅስቃሴ ማሳየት
- ከንፈራቸውን ማጣጣም (smacking)፣ ምራቃቸውን ማዝረብ ወይም ምላሳቸውን ማውጣት
- እጆቻቸውን ወደ አፋቸው መክተት ፣ ጣቶቻቸውን ወይም ልብሳቸውን መጥባት
- እጆቹን መጨበጥ ፤ ይህ መበሳጨት እንደጀመሩ እና ትዕግስት እያጡ እንደሆነ ያሳያል ።
- እርስዎን ትኩር ብሎ መመልከት ወይም በአይናቸው እንቅስቃሴዎን መከተል (በተለይ በዋነኝነት የሚመግቧቸው እርስዎ ከሆኑ)
- ግንባራቸውን በማጨማተር "መቼ ነው የምንበላው?" የሚል የሚመስል ጭንቀት የተሞላበት የፊት ገጽታ ማሳየት
- “ነህ!” (neh!) የሚል ድምፅ ማውጣት ፤ እንደ "ደንስተን የሕፃናት ቋንቋ" (Dunstan baby language) ጥናት መሰረት ህፃናት ከማልቀሳቸው በፊት ይህን ድምፅ ካሰሙ መራባቸውን ያመለክታል።
እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብዎት ነገር ሕፃናት ምንም እንኳ በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ቢሆኑም ሲርባቸው አብዛኛውን ጊዜ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ። ስለዚህ ልጅዎ ከተጠበቀው በላይ ረዘም ላለ ጊዜ የሚተኛ ከሆነ፣ ለእድሜው በቂ ምግብ እያገኙ መሆኑን ለማረጋገጥ ለእድሜው ምን ያህል ጊዜ እና ምን ያህል መጠን መመገብ እንዳለበት የሚያሳይ የመመገቢያ መመሪያን (feeding guide) ይጠቀሙ።
በአጠቃላይ አራስ ህፃናት ሳይመገቡ በአንድ ጊዜ ከ4 ሰዓት በላይ አዘውትረው መተኛት የለባቸውም። አልፎ አልፎ እንዲህ ረዘም ላለ ጊዜ መተኛታቸው ችግር የለውም ፤ በተለይም እርስዎ እንዲያርፉ የሚረዳዎት ከሆነ ። ነገር ግን ልጅዎ ብዙውን ጊዜ ከመመገብ ይልቅ መተኛትን የሚመርጥ ከሆነ፣ ቀስ አድርገው እየቀሰቀሱ ማጥባት እንዳለብዎ ለማወቅ የሕፃናት ሐኪምዎችን ማማከሩ የተሻለ ነው።
ልጅዎ መጥገቡን የሚያሳዩ ምልክቶች
ልጅዎ ጥቂት የጡት ወተት ጨምሮ እንዲመገብ ወይም ጡጦ ላይ የቀረውን ወተት እንዲጨርስ ፤ ከወትሮው ያነሰ ሲመገብ ደግሞ የበለጠ ቢበላ ብለው መመኘትዎ እና ልጅዎን እንዲመገብ ማበረታታትዎ ተፈጥሯዊ ነው ። ነገር ግን ሕፃናት ሲወለዱ የወሰዱት ምግብ በቂ እንደሆነ የሚያውቁበትን ተፈጥሯዊ ብቃት ይዘው ነው የሚወለዱት።
ሕፃናት ከጠገቡ በኋላ እንዲበሉ በምንገፋፋቸው ጊዜ የሰውነታቸውን የረሃብ እና የጥጋብ ተፈጥሯዊ ምልክቶች ችላ እንዲሉ እያስተማርናቸው ነው። ስለዚህ ልጅዎ ምን ያህል ምግብ እንደሚያስፈልገው እንደሚያውቅ በማመን በቃኝ ሲል መመገብ ማቆም ይኖርቦታል። ከዚህ በተጨማሪ የልጅዎ የምግብ ፍላጎት ከቀን ቀን እንዲሁም ከአንዱ የመመገቢያ ሰዓት ወደ ሌላኛው ሊቀያየር ይችላል ፤ ይህም ፍጹም የተለመደ ነው።
ልጅዎን ከመገቡ በኋላ መጥገቡን እና መርካቱን ለማወቅ የሚከተሉትን ምልክቶች ይመልከቱ፦
- ምግብ መመገብ እንደጀመሩ ብዙም ሳይቆይ ማልቀስ መጀመር
- የሚጠባበትን ፍጥነት መቀነስ ወይም ማቆም
- ጡትዎን ወይም ጡጦውን መልቀቅ ወይም መግፋት
- ጭንቅላታቸውን ከጡትዎ ወይም ከጡጦ ማዞር
- አፋን መዝጋት እና እንደገና እንዲጠባ ለሚደረግ ማበረታቻ ምላሽ አለመስጠት
- እጆቹን ፣ ክንዶቹን እና እግሮቹን ዘና ማድረግ
- ዙሪያቸውን መመልከት እና መጫወት ወይም ሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረታቸውን ማድረግ
- የመርካት ስሜት ማሳየት እና ፈገግ ማለት
- ማሸለብ መጀመር እና መተኛት



