የካንሰር ህመም እራሱ የምግብ ፍላጎትን እና አመጋገብን ጨምሮ እያንዳንዱን የጤናዎን ክፍል ላይ ተጸኖ ሊያሳድር ይችላል። ከበሽታው በተጨማሪም ለካንሰር ተብለው የሚሰጡ እንደ ኪሞቴራፒ እና አንዳንድ የጨረር ሕክምና (radiation therapy) ያሉ ሕክምናዎች የሚከተሉትን የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትሉ ይችላሉ፦
- የሆድ ድርቀት፦ ይህም ምቾት ማጣትን ሊያስከትል እና የመመገብ ፍላጎትዎን የበለጠ ሊቀንስ ይችላል።
- ተቅማጥ፦ ይህም ከሰውነትዎ ውስጥ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ሊያጠፋ ይችላል።
- ድካም፦ ይህም እንቅስቃሴዎ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ጥቂት ካሎሪዎችን ብቻ ያቃጥላሉ፣ በዚህም ምክንያት ቀኑን ሙሉ የራብ ስሜት አይሰማዎትም።
- የጣዕም መጥፋት እና የምግብ ጣዕም መለወጥ፦ ይህም ምግቦች ማራኪ እንዳይሆኑ ሊያደርግ ይችላል።
- ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ፦ ይህም የምግብ ፍላጎትዎን ሊቀንስ እና የክብደት መቀነስን ሊያስከትል ይችላል።
- የአፍ መድረቅ
አንዳንድ ሰዎች ከጡት ካንሰር ወይም ከማህፀን (endometrial) ካንሰር ኪሞቴራፒ በኋላ የሆርሞን ሕክምና ያገኛሉ። እነዚህ መድኃኒቶች ለሰውነት ሜታቦሊዝም (ምግብን ወደ ኃይል የመለወጥ ሂደት) ወሳኝ የሆነውን ኢስትሮጅን የተባለ ሆርሞን ምርትን ያግዳሉ። የሜታቦሊዝም ፍጥነት ከቀነሰ ክብደት ሊጨምሩ ይችላሉ። የጣፊያ (pancreatic) ካንሰር ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ክብደታቸውን ለመጠበቅ ይቸገራሉ። ጣፊያ በሚፈለገው መጠን ሥራውን ካልሠራ፣ ምግቦችን በአግባቡ መፍጨት ላይችሉ ይችላሉ። ይህም ለክብደት መቀነስ ወይም ለሥርዓተ-ምግብ መጓደል (malnourishment) ሊዳርግ ይችላል።
የካንሰር ሕክምና የምግብ ፍላጎት እና የሰውነት ክብደት መለዋወጥን ሊያስከትል ስለሚችል፣ ለአመጋገብዎ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው። የሰውነትዎ ተግባር በትክክል እንዲቀጥል ጤናማ እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አስፈላጊ ነው። ጣዕማቸው መጠነኛ የሆኑ፣ ለጨጓራ የማይከብዱ እና ንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦች ምርጥ አማራጮች ናቸው። በኪሞቴራፒ ወይም በጨረር ሕክምና ወቅት የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ጤናማ ክብደትን ለመጠበቅ ከመረዳቱም በላይ የሕክምና የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቆጣጠር ይረዳል፣ ኃይልን ይጨምራል፣ የጡንቻ ጥንካሬን ይጨምራል፣ የበሽታ መከላከል አቅምን ይጠብቃል እና የሰውነት መቆጣትን ወይም ብግነትን (inflammation) ይቀንሳል።
አመጋገብዎ የካንሰር ሕክምና የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቆጣጠር እንዴት ይረዳል?
ሕክምና ከጀመሩ በኋላ አንዳንድ የአመጋገብ ለውጦችን ማድረግ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቆጣጠር ይረዳዎታል። እነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የምግብ ፍላጎት ማጣት፦ በቀን ሦስት ትላልቅ ምግቦችን ከመመገብ ይልቅ፣ በአጫጭር ሰዓት ልዪነት አነስተኛ መጠን ያላቸውን ምግቦች ወይም መክሰሶች (snacks) ይመገቡ።
- የሆድ ድርቀት፦ በቂ ውሃ ይጠጡ፣ እንዲሁም በምግብዎ ውስጥ አትክልቶችን እና ባቄላዎችን ይጨምሩ።
- ተቅማጥ፦ ሶዲየም ያለባቸውን ምግቦች ወይም መጠጦች (እንደ ሾርባ ወይም መረቅ) እና ፖታሺየም ያላቸውን (እንደ ሙዝ እና ተፈጥሯዊ የፍራፍሬ ጭማቂዎች) ይምረጡ።
- የጣዕም መጥፋት፦ በተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ወይም እንደ ሎሚ ባሉ ቆምጣጣ ፍራፍሬዎች የተሰሩ ምግቦችን ይሞክሩ። በተጨማሪም ካቻፕ፣ ሰናፍጭ (Mustards)፣ ሶይ ሶስ (Soy sauce)፣ ፣ቆምጣጤ (Vinegar) ወይም ወይን (Wine) መጨመር ምግቡ ጣዕም እንዲኖረው ይረዳል።
- ማቅለሽለሽ፦ የሎሚ ቁራጭ መምጠጥ፣ የዝንጅብል ሻይ መጠጣት ወይም የዝንጅብል ከረሜላዎችን (ginger chews) መመገብ ይችላሉ።
በካንሰር ህክምና ወቅት ተስማሚ የሆኑ 10 ምግቦች
1. አጃ (Oatmeal)
አጃ በኪሞቴራፒ ወቅት ሰውነትዎን ሊረዱ የሚችሉ በርካታ ንጥረ ነገሮችን ያቀርባል። በውስጡ ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲን እና ፀረ ቲኦክሲዳንት (antioxidants) የያዘ ሲሆን፣ ከሌሎች እህሎች ይልቅ ጤናማ ቅባቶች አሉት። የአጃ የማይረብሽ ጣዕም እና ለስላሳ ባህሪ እንደ አፍ መድረቅ ወይም የአፍ ቁስለት ያሉ የተለመዱ የኪሞቴራፒ የጎንዮሽ ጉዳቶች እያጋጠሙዎት ከሆነ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም ፍራፍሬዎችን፣ ማርን ወይም ለውዝ በላዩ ላይ መጨመር ይችላሉ። ማቅለሽለሽ ወይም የአፍ ቁስለት ካለብዎ ምንም ነገር ሳይጨምሩ ወይም በትንሽ ጨው ብቻ መመገብ ይችላሉ።
2. አቮካዶ
የምግብ ፍላጎትዎ ከቀነሰ፣ አቮካዶ አስፈላጊ የሆኑ ካሎሪዎችን እና ንጥረ ነገሮችን በአመጋገብዎ ውስጥ ሊያካትት ይችላል። ይህ ፍራፍሬ በጤናማ ቅባቶች የበለፀገ ሲሆን፣ ይህም መጥፎ ኮሌስትሮልን (LDL) ለመቀነስ እና ጥሩ ኮሌስትሮልን (HDL) ለመጨመር ይረዳል። ግማሽ አቮካዶ (75 ግራም) ጥሩ የመመገቢያ መጠን ሲሆን፣ 5 ግራም ፋይበር ይይዛል። አቮካዶ ሆድን የሚሞላ፣ ለተለያዩ አዘገጃጀቶች የሚሆን እና ጣዕሙ የማይረብሽ በመሆኑ፣ የአፍ መድረቅ፣ የሆድ ድርቀት፣ የአፍ ቁስለት ወይም የክብደት መቀነስ እያጋጠመዎት ከሆነ በጣም ጥሩ ምርጫ ነው። በዳቦ ላይ ቀብተው ወይም እንደ ጥራጥሬ፣ ባቄላ እና ሾርባ ባሉ ምግቦች ላይ ከትፈው መመገብ ይችላሉ።
3. እንቁላል
ድካም የኪሞቴራፒ የተለመደ የጎንዮሽ ጉዳት ነው። እንቁላል በውስጡ ባለው ከፍተኛ የፕሮቲን እና የቅባት መጠን ምክንያት ድካምን ሊቀንስ ይችላል። በአንድ ትልቅ እንቁላል (50 ግራም) ውስጥ 6 ግራም ገደማ ፕሮቲን እና 5 ግራም ቅባት ይገኛል። ቅባት ለሰውነትዎ ኃይል ሲሰጥ፣ ፕሮቲን ደግሞ የጡንቻን መጠን ለመጠበቅ እና ለመገንባት ይረዳል፤ ይህም በተለይ በኪሞቴራፒ ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው። የእንቁላል ለስላሳ ባህሪ የአፍ ቁስለት ላለባቸው ሰዎች ተመራጭ ያደርገዋል። እንቁላልን ቀቅለው ወይም ደግሞ ወጥ ሰርተው መመገብ ይችላሉ። የምግብ መመረዝን ለመከላከል የእንቁላሉ አስኳል መወፈርና ነጩ ክፍል መድረቅ እስኪጀምር ድረስ በደንብ መብሰሉን ያረጋግጡ።
4. ሾርባ/መረቅ
በኪሞቴራፒ ወቅት የጣዕም ለውጦች መከሰታቸው የተለመደ ነው። ውሃ እራሱ ጣዕሙ እንደሚቀየር ይነገራል። በእነዚህ አጋጣሚዎች፣ የሰውነት ፈሳሽን ለመጠበቅ መረቅ (broth) ታላቅ አማራጭ ነው። መረቅ የሚዘጋጀው ውሃን ከአትክልቶች፣ ከቅመማ ቅመሞች እና ከተፈለገ ከሥጋ ወይም ከዶሮ እንዲሁም ከአጥንት ጋር በማፍላት ነው። የምግብ ፍላጎት ካለዎት፣ በውስጡ ዶሮን፣ ቶፉን ወይም አትክልቶችን መጨመር ይችላሉ። ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት፣ በተለይም የአፍ መድረቅ ወይም የምግብ ፍላጎት ማጣት ሲኖር፣ ጣዕም የሌለው የፕሮቲን ዱቄት (እንደ ኮላጅን ዱቄት ያለ) መጨመር ይችላሉ።
5. ለውዝ
እንደ አልሞንድ (almonds) እና ካሼው ያሉ የለውዝ አይነቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ጤናማ ቅባቶች፣ ቪታሚኖች እና ማዕድናት እንዲሁም ትንሽ ፕሮቲን ይይዛሉ። ለውዝ ለማንጋኒዝ እና ለኮፐር የበለፀገ ምንጭ ነው። እነዚህ ማዕድናት በሰውነት ውስጥ እጅግ ኃይለኛ ከሆኑት ፀረ ኦክሲዳንቶች አንዱ የሆነውን "ሱፐርኦክሳይድ ዲስሙታሴስ" ይፈጥራሉ። ፀረ ኦክሲዳንቶች ሕዋሳትዎን የሚጎዱ ንጥረ ነገሮችን ለመዋጋት ይረዳሉ። ለውዝን በአጃ ወይም በሌሎች ምግቦች ላይ መጨመር ይችላሉ። ሆኖም የአፍ ቁስለት ካለብዎ እነሱን መብላት ሊከብድ ስለሚችል፣ በምትኩ የለውዝ ቅቤን (nut butters) መምረጥ ይችላሉ።
6. የዱባ ፍሬ
የዱባ ፍሬዎች በቅባት፣ በፕሮቲን እና እብጠትን ለመዋጋት በሚረዳው እንደ ቪታሚን ኢ ባሉ ፀረ ኦክሲዳንቶች የበለፀጉ ናቸው። ከዚህም በላይ ጥሩ የአይረን (iron) ምንጭ ናቸው። ጣፋጭና ጨዋማ የሆነ ጣዕም እንዲኖረው፣ የዱባ ፍሬዎችን ከሌሎች የደረቁ ፍራፍሬዎችና ለውዝ ጋር በማቀላቀል የራስዎን ድብልቅ ማዘጋጀት ይችላሉ።
7. ብሮኮሊ እና ሌሎች ጎመን መሰል አትክልቶች
እንደ ኬል (kale)፣ ብሮኮሊ፣ አበባ ጎመን እና ጥቅል ጎመን ያሉ አትክልቶች አስደናቂ የሆነ የንጥረ ነገር ይዘት አላቸው። በተለይም ብሮኮሊ ከፍተኛ መጠን ያለው ቪታሚን ሲ ይይዛል። ይህ ቪታሚን ለበሽታ መከላከል ስርዓትዎ ወሳኝ ነው። እነዚህን አትክልቶች በወይራ ዘይትና በትንሽ ጨው በእንፋሎት አብስሎ ወይም ጠብሶ መመገብ ይቻላል። የጣዕም ለውጥ ካጋጠመዎት እና የአፍ ቁስለት ወይም ማቅለሽለሽ ከሌለብዎት ጥቂት ሎሚ በመጭመቅ ጣዕሙን መቀየር ይችላሉ።
8. የቤት ውስጥ ፍራፍሬ ጭማቂ (Homemade Smoothies)
ጠንካራ ምግብ ማኘክ ለሚከብዳችሁ ወይም በአመጋገብዎ ውስጥ በቂ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት ለሚቸገሩ ሰዎች የቤት ውስጥ ጭማቂዎች (smoothies) በጣም ጥሩ አማራጭ ናቸው። እንደ ምልክቶችዎ ወይም እንደ ጣዕም ምርጫዎ ግብአቶቹን በመቀየር ማዘጋጀት ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ትኩስ ወይም በረዶ የሆኑ ፍራፍሬዎችን ከወተት ወይም ከእርጎ ጋር በመቀላቀል፣ ከዚያም የታጠቡ የቆስጣ ቅጠሎችን ይጨምሩ። ለቅባት የሚሆን የተልባ ፍሬ እና ለፕሮቲን የሚሆን የለውዝ ቅቤ በመጨመር ማዘጋጀት ይቻላል። በአጠቃላይ አዘገጃጀቱ የሚከተለው ነው፦
- 1–2 ኩባያ (240–475 ml) ፈሳሽ
- 1.5–3 ኩባያ (225–450 ግራም) አትክልት እና/ወይም ፍራፍሬ
- 1 የሾርባ ማንኪያ (15 ግራም) ፕሮቲን
- 1 የሾርባ ማንኪያ (15 ግራም) ቅባት
9. ዳቦ ወይም ብስኩት (Crackers)
ተቅማጥ ወይም ማቅለሽለሽ እያጋጠመዎት ከሆነ፣ ነጭ ዳቦ ወይም ብስኩት በቀላሉ ስለሚፈጩ ጥሩ ምርጫ ናቸው። ሆድዎ በማይረበሽበት ጊዜ ደግሞ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን የያዙትን ሙሉ እህል (whole-grain) ዳቦዎችን መመገብ ይመረጣል። ምንም ነገር ሳይጨምሩባቸው መብላት ወይም ደግሞ ተጨማሪ ጣዕምና ንጥረ ነገር ከፈለጉ በለውዝ ቅቤ፣ በአቮካዶ ወይም ቺዝ ቀብተው መመገብ ይችላሉ።
10. ዓሳ
የባሕር ምግቦችን የሚወዱ ከሆነ፣ በኪሞቴራፒ ወቅት ቅባት ያላቸው ዓሳዎችን መመገብ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ዓሳ ፕሮቲን እና ኦሜጋ-3ን ያቀርባል። ኦሜጋ-3 በአመጋገብዎ ውስጥ ሊያገኟቸው የሚገቡ ጠቃሚ ቅባቶች ናቸው፤ እነሱም ለአንጎል ጤና ይረዳሉ እንዲሁም ብግነትን የመከላከል ባህሪ አላቸው። እንደ ሳልመን (salmon)፣ ማክሬል (mackerel) እና ሰርዲን ያሉ ዓሳዎች በእነዚህ ቅባቶች በጣም የበለፀጉ ናቸው። ዓሳውን በእንፋሎት በመቀቀል ወይም በመጥበስ መመገብ ይችላሉ። በሚሰሩበት ጊዜ ዓሳው በደንብ መብሰሉን ያረጋግጡ።
በኪሞቴራፒ ወቅት ሊወገዱ የሚገቡ ምግቦች ምንድን ናቸው?
ኪሞቴራፒ ፈጣን እድገት ያላቸውን የካንሰር ሕዋሳት የሕይወት ኡደት ለማስተጓጎል ኃይለኛ ኬሚካሎችን የሚጠቀም የሕክምና ዓይነት ነው። ይህ ሕክምና መላ ሰውነትን የሚነካ እንደመሆኑ መጠን፣ ከካንሰር ሕክምናው ባለፈ በአጠቃላይ ጤናዎ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም (Immune suppression) በኪሞቴራፒ የጎንዮሽ ጉዳቶች ረገድ የተለመደ ስጋት ነው። ኪሞቴራፒ ኢንፌክሽንን ለመከላከል የሚረዱዎትን ነጭ የደም ህዋሳት የመመረት አቅምን ሊለውጠው ይችላል። በሕክምናዎ ወቅት በሽታ የመከላከል አቅምዎ የቀነሰበት ደረጃ ላይ ከሆኑ፣ የሚመገቡትን ነገር መከታተል አደገኛ ለሆኑ ከምግብ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ እድልዎን ለመቀነስ ይረዳል።
በኪሞቴራፒ ወቅት አንዳንድ ምግቦች ከምግብ የሚመጡ በሽታዎችን (foodborne illnesses) የመያዝ እድልዎን ሊጨምሩ ይችላሉ። የትኞቹ ምግቦች ከፍተኛ ስጋት ሊኖራቸው እንደሚችል ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የሚከተሉት ምግቦችን መመገብ ቢቀንሱ ይመከራል፡
1. ያልተፈላ/ ፓስቸራይዝድ ያልሆነ (Unpasteurized) ወተት እና የወተት ተዋጽኦዎች
ፓስቸራይዜሽን (Pasteurization) በሙቀት አማካኝነት ጀርሞችን የማጥፋት ሂደት ሲሆን፣ ለብዙ በፋብሪካ ለታሸጉ ምግቦች ጥቅም ላይ ይውላል፤ ከእነዚህም መካከል፦
- የወተት ተዋጽኦዎች
- ጭማቂዎች
- ሳንድዊች ውስጥ የሚገቡ ስጋዎች
- የእንቁላል ውጤቶች
- የለውዝ ቅቤዎች
በኪሞቴራፒ ወቅት ያልተፈላ ወይም ፓስቸራይዝድ ያልሆነ ወተት እና ተዋጽኦዎቹን (ለምሳሌ እርጎ ወይም አይብ) ማስወገድ ያስፈልጋል።
2. ክፍት በሆኑ ቦታዎች የሚቀመጡ እና በጅምላ የሚሸጡ ዕቃዎች
በሱፐርማርኬት ማቀዝቀዣዎች ውስጥ ለቀኑ ተቀምጠው የሚውሉ ሰላጣዎች እና ስጋዎች ቀዝቃዛ ሆነው ሊቆዩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ሰራተኛው በሩን በከፈተ ቁጥር ለበሽታ አምጪ ተሕዋስያን የመጋለጥ እድል አላቸው። እንደ ጥራጥሬ ያሉ በጅምላ ከሚቀመጡ እቃዎች ላይ ራስዎ የሚቀዱባቸው ነገሮችም ተመሳሳይ ናቸው። ከእርስዎ በፊት የነበረው ሰው እቃውን ሲከፍት ምግቡ ለምን ነገር እንደተጋለጠ ላያውቁ ይችላሉ።
3. ያልታጠቡ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች
ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በኪሞቴራፒ ወቅት ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን እርስዎን ሊያሳምሙ የሚችሉ የውጭ ንክኪዎችን ለማስወገድ ከመመገብዎ በፊት ሁል ጊዜ መታጠብ ወይም መብሰል አለባቸው።
4. በደንብ ያልበሰሉ ሥጋዎች
ሥጋን በተገቢው የሙቀት መጠን ማብሰል በኪሞቴራፒ ወቅት ከሚደረጉ በጣም ደህንነታቸው የተጠበቀ የአመጋገብ ልምዶች አንዱ ነው። ከፍተኛ ሙቀት በሥጋው ውጭም ሆነ ውስጥ ያሉ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን ይገድላል። ሆን ተብለው በጥሬነታቸው የሚቀርቡትን እንደ ቁርጥ ስጋ ወይም ሱሺ (sushi) ያሉ ምግቦችን ያስፈልጋል።
5. ያልበሰለ እንቁላል
ያልበሰለ እንቁላሎች፣ ሳልሞኔላ (Salmonella) የተባለ ባክቴሪያን ሊሸከሙ እንደሚችሉ ይታወቃል። ያልበሰለ እንቁላል ሊይዙ የሚችሉ ነገሮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ስሙዝዎች (smoothies)
- በቤት ውስጥ የሚሰራ ማዮኔዝ
- ያልተጋገረ የኩኪስ ሊጥ
- አንዳንድ የሰላጣ ማጣፈጫዎች
ያልበሰለ እንቁላል ወይም እሱን የያዙ ምግቦችን በኪሞቴራፒ ወቅት ባይመገቡ ይመከራል።
6. ክሬም የተሞላባቸው የተጋገሩ ምግቦች
ክሬም የተሞላባቸው የተጋገሩ ምግቦች ብዙውን ጊዜ የወተት ተዋጽኦን እንደ መነሻ ይጠቀማሉ፣ ይህም ከምግብ የሚመጡ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን ለማደግ ተስማሚ ቦታ ሊሆን ይችላል።
7. የተወሰኑ የውሃ አይነቶች
ውሃን በቀጥታ ከጉድጓድ፣ ከምንጭ ወይም ከወንዝ መጠቀም እንደ ኢ-ኮላይ (E. coli)፣ ክሪፕቶስፖሪዲየም (Cryptosporidium) እና ሌጂዮኔላ (Legionella) ለመሳሰሉ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን ሊያጋልጥዎት ይችላል።
በካንሰር ሕክምና ወቅት የምግብ ደህንነት እንዴት መጠበክ ይቻላል?
በካንሰር ሕክምናዎ ወቅት፣ ሰውነትዎ ራሱን በሚገባ መከላከል የማይችልባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ይህ የሚሆነው ኢንፌክሽንን የሚዋጉ ነጭ የደም ሴሎች ለተወሰነ ጊዜ በበቂ መጠን ስለማይኖሩዎት ነው። ስለዚህም ሰውነትዎ ኢንፌክሽንን እና በሽታን እንደ ጤናማ ሰው መከላከል አይችልም። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ ምግቦች ውስጥ ሊገኙ ከሚችሉ ኢንፌክሽን አምጪ ጀርሞች ጋር ያለውን ንክኪ ለማስወገድ ጥረት እንዲያደርጉ ሊነገርዎት ይችላል።
እንደ ስታፊሎኮከስ (staph)፣ ኢ-ኮላይ (E coli) እና ሳልሞኔላ (Salmonella) ያሉ ጀርሞች በሚከተሉት ላይ ሊገኙ ይችላሉ፦
- በአግባቡ ሳይቀዘቅዙ ለረጅም ጊዜ ውጭ የቆዩ ምግቦች
- በቆሸሹ ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ምግቦች
- በቆሸሸ እጅ የተነኩ ምግቦች
- ያልበሰሉ ወይም ጥሬ ሥጋዎች
የበሽታ መከላከል ሥርዓትዎ በማገገም ላይ በሚሆንበት ወቅት ምግብን ስለመግዛት፣ ስለማከማቸት እና ስለማዘጋጀት የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች እነሆ፦
የምግብ አያያዝ
- ምግብ ከማዘጋጀትዎ በፊት እና በኋላ፣ እንዲሁም ከመመገብዎ በፊት እጅዎን በሞቀ ውሃ እና በሳሙና ለ20 ሰከንድ ይታጠቡ።
- የምግብ ማዘጋጃ ጠረጴዛዎችን እና መክተፊያዎችን በሙቅ ውሃ እና በሳሙና ያጽዱ።
- የወጥ ቤቶትን በንጹህ ፎጣ ወይም ስፖንጅ በአግባቡ ያፅዱ
- የታሸጉ ምግቦችን (ቆርቆሮዎችን) ከመክፈትዎ በፊት የላይኛውን ክፍላቸውን በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ።
- ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ከመላጥዎ ወይም ከመክተፍዎ በፊት በሚፈስ ውሃ በደንብ ይጠቡ። ሳሙና፣ አጃክስ፣ ክሎሪን ወይም የአትክልት ማጠቢያዎችን አይጠቀሙ።
- ወፍራም እና ሻካራ ቅርፊት ያላቸውን ምርቶች (እንደ ድንች) ወይም አፈር ያለባቸውን ማናቸውንም ምርቶች ለማጽዳት ንጹህ የአትክልት መፋቂያ (scrubber) ይጠቀሙ።
- የቅጠላቅጠል አትክልቶችን ቅጠሎች አንድ በአንድ በሚፈስ ውሃ ስር ያለቅልቁ።
- ሥጋን፣ የዶሮ ሥጋን እና ዓሳን በቀዝቃዛ በሚፈስ ውሃ ካለቀለቁ በኋላ በወረቀት ፎጣ ጠርገው ያድርቁ።
በምግብ ዝግጅት ጊዜ
- ለእያንዳንዱ ምግብ መቁረጫ ንጹህ ቢላዋ ይጠቀሙ።
- ምግብ በሚያበስሉበት ወቅት ለማማሰል እና ለመቅመስ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይጠቀሙ።
- ምግቡን ሲቀምሱ (ወይም ሌሎች እንዲቀምሱ ሲያደርጉ) ወደ ምግቡ ተመልሶ የሚገባ ማንኛውንም ቁሳቁስ አይጠቀሙ።
- ምግቦችን በጠረጴዛው ላይ ለይተው ያስቀምጡ።
- የተለያዩ ምግቦችን በሚያዘጋጁበት ወቅት (ለምሳሌ ከአትክልት ወደ ሥጋ ሲቀይሩ) እጅዎን፣ መክተፊያውን እና የተጠቀሙባቸውን ዕቃዎች በድጋሚ በሳሙና እና በሙቅ ውሃ መታጠብዎን ያረጋግጡ።
- የበሰለ ምግብ ለማቅረብ ንጹህ ሰሃኖችን ይጠቀሙ። ጥሬ ሥጋ ወይም ዓሳ የተቀመጠበትን ሰሃን በሳሙና እና በሞቀ ውሃ በደንብ ሳይታጠብ በድጋሚ ለማንኛውም አገልግሎት በፍጹም አይጠቀሙ።
- ሥጋው ቀይነቱ እስኪጠፋና የሚወጣው ፈሳሽ ጥራት ያለ (clear) እስኪሆን ድረስ ያብስሉት።
- የተከተፉ ሥጋዎች እስከ 145° ፋራናይት፣ የተፈጩ ሥጋዎች (ጥጃ፣ በሬ፣ በግ፣ ፍየል) እስከ 160° ፋራናይት፣ እና የዶሮ ሥጋ እስከ 165° ፋራናይት መብሰል አለባቸው።
- በማይክሮዌቭ ውስጥ ምግብ ሲያበስሉ የሚሽከረከርበት ጠረጴዛ (turntable) ከሌለው፣ ምግቡን አንድ አራተኛ እያዞሩ አንዴ ወይም ሁለቴ ያብስሉት። ይህ ባክቴሪያዎች ሊተርፉባቸው የሚችሉ ቀዝቃዛ ቦታዎች እንዳይኖሩ ይረዳል።
- በማይክሮዌቭ ውስጥ የተረፈ ምግብን ለማሞቅ ክዳን ወይም ቀዳዳ ያለው የፕላስቲክ መጠቅለያ በመጠቀም በደንብ እንዲሞቅ ያድርጉ።
- ምግብ በሚያሞቁበት ወቅት ደጋግመው ያማስሉት።
- እንቁላል አስኳሉ እና ነጩ ክፍል ጠንካራ እስኪሆን ድረስ መብሰል አለበት፤ ፈሳሽ መሆን የለበትም።
የምግብ አቀማመጥ
- ምግቦችን በ40° ፋራናይት (4° ሴልሺየስ) ወይም ከዚያ በታች ባለው የሙቀት መጠን ያቀዝቅዙ።
- ትኩስ ምግቦችን ከ140° ፋራናይት በላይ፣ ቀዝቃዛ ምግቦችን ደግሞ ከ40° ፋራናይት በታች በሆነ የሙቀት መጠን ያቆዩ።
- የቀዘቀዘ ሥጋን፣ ዓሳን ወይም የዶሮ ሥጋን ለማሟሟት በማይክሮዌቭ ወይም በማቀዝቀዣ ውስጥ ፈሳሹን የሚቀበል ሰሃን በመጠቀም ያሟሟቸው። በክፍል ሙቀት ውስጥ በፍጹም አያሟሟቸው።
- በማቀዝቀዣ ውስጥ ጥሬ ሥጋን በደንብ አሽገው ወዲያውኑ ለምግብነት ከሚውሉ (ready-to-eat) ምግቦች ለይተው ያስቀምጡ።
- የቀዘቀዙ ምግቦች ከሟሙ በኋላ ወዲያውኑ ይጠቀሙባቸው፤ በድጋሚ አያቀዝቅዟቸው።
- ቶሎ ሊበላሹ የሚችሉ ምግቦችን ከገዙ ወይም ካዘጋጁ በኋላ በ2 ሰዓት ውስጥ በማቀዝቀዣ ውስጥ ያስገቡ።
- የእንቁላል ምግቦች እንዲሁም ክሬም፣ ማዮኔዝ እና መሰል ግብዓቶች ያለባቸው ምግቦች ከአንድ ሰዓት በላይ ሳይቀዘቅዙ ውጭ መቆየት የለባቸውም።
ምግብ በሚገዙበት ጊዜ
- የመጠቀሚያ (use-by) ቀናትን ያረጋግጡ። የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች (ሥጋን፣ የዶሮ ሥጋን ወይም የባሕር ምግቦችን ጨምሮ) አይግዙ። በጣም ትኩስ የሆኑ ምርቶችን ብቻ ይምረጡ።
- የተበላሹ፣ ያበጡ፣ የዛጉ ወይም በጣም የተጨፈለቁ ቆርቆሮዎችን አይጠቀሙ። የታሸጉ እና በሳጥን ውስጥ ያሉ ምግቦች በአግባቡ መታሸጋቸውን ያረጋግጡ። እንዲሁም የአገልግሎት ማብቂያ ቀናቸውን ይፈትሹ።
- ያልተጎዱ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ይምረጡ።
- በላስቲክ ታሽገው የሚሸጡ ምግቦችን (የተከተፉ ሥጋዎች፣ አይብ እና ሰላጣዎች) አይመገቡ።
- በመጋገሪያ ቤቶች ውስጥ ሳይቀዘቅዙ የተቀመጡ ክሬም እና ካስተርድ ያለባቸውን ጣፋጮች ያስወግዱ።
- ከማሽኖች የሚወጡ እርጎ እና አይስክሬም ምርቶችን አይመገቡ።
- ነፃ የምግብ ሳምፕሎችን አይመገቡ።
- የቀዘቀዙ እና ማቀዝቀዣ ውስጥ የሚገቡ ምግቦችን ከገበያ ከመውጣትዎ ጥቂት ቀደም ብሎ ይግዙ፤ በተለይም በበጋ ወራት።
- የገዟቸውን ምግቦች ወዲያውኑ ማቀዝቀዣ ውስጥ ያስገቡ። ምግብን በሙቅ መኪና ውስጥ በፍጹም አይተዉ።
ውጪ በሚመገቡበት ጊዜ
- ውጭ በሚመገቡበት ጊዜ ካልበሰሉ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ይራቁ
- የሰላጣ ገበታዎች፣ ቡፌዎች እና የመንገድ ላይ ምግቦች ከመመገብ ይቆጠቡ
- ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ (single-serving) የታሸጉ የሰላጣ ማጣፈጫዎችን፣ ሶሶችን እና ሳልሳዎችን ብቻ ይጠቀሙ።
- ምግብ ቤቶች ብዙ ሰው በማይበዛባቸው ሰዓታት ይሂዱ።
- ፈጣን ምግብ ቤቶች (fast food restaurants) ውስጥ ምግብዎ ትኩስ ሆኖ እንዲዘጋጅልዎ ሁልጊዜ ይጠይቁ።


