ብስክሌት መንዳት የሚሰጣቸው 10 የጤና ጥቅሞች
ብስክሌት መንዳት ለአካልም ሆነ ለአእምሮ ከፍተኛ ጥቅም ያለው በጣም አዝናኝ እና በመገጣጠሚያዎችዎ ላይ ጫና የማይፈጥር የኤሮቢክ (aerobic) ስፖርት ነው። የብስክሌት መንዳት አንዱ ምርጥ ባህሪ በተለያዩ መንገዶች ሊከናወን መቻሉ ነው። ለመዝናናት ፣ ከባታ ቦታ ለመጓጓዝ ወይም ጠንከር ያለ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የሰውነትዎ የብቃት ደረጃ ምን ይሁን ምን ብስክሌት መንዳትን ከእርስዎ ጋር እንዲስማማ ማድረግ የሚችሉበት መንገድ አለ።
የስፖርት ቁሳቁሶችን ለመግዛት አስበው የትኛው እንደሚሻልዎት መወሰን ካልቻሉ የዚችን ትህትና የተላበሰች ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ አስደናቂ ጥቅሞች ዳግም የሚፈትሹበት ጊዜ አሁን ሊሆን ይችላል። የተሻለ አቋም እንዲኖሮት እና ትኩረቶን ለመጨመር ከማስቻል በተጨማሪ ጤናማ እና ንቁ የአኗኗር ዘይቤን ለመከተል ብስክሌት መንዳት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ቀድሞውኑ ብስክሌት አለዎት? እንግዲያውስ አያመንቱ ፤ ሰንሰለቱን ዘይት ይቀቡ፣ ጎማውንም ይንፉ እና ዛሬውኑ ብስክሌት ለ ንዳት ይውጡ።
ብስክሌት መንዳት የአካል ብቃትዎን እና አጠቃላይ ጤናዎን የሚያሻሽልባቸውን በርካታ መንገዶች ለማወቅ ፅሁፉን ማንበብ ይቀጥሉ።
ብስክሌት የመንዳት ጥቅሞች
1. ብስክሌት መንዳት የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል
ብስክሌትን አዘውትሮ መንዳት በተለይም በከፍተኛ ፍጥነት መንዳት ፣ የሰውነትዎን የስብ መጠን ለመቀነስ ይረዳል፤ ይህም ጤናማ ክብደት እንዲኖርዎ ያደርጋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብስክሌትን በመደበኛነት ከመንዳት ጋር ፈጣን ሩጫን (sprint) እና ጥንካሬን የሚጨምሩ ስፖርቶችን ማድረግ የምግብ መፈጨት ሥርዓትን (metabolism) ለማፋጠን እና ጡንቻን ለመገንባት ያስችላል ። ይህ ደግሞ በእረፍት ሰዓትዎ እንኳን ሰውነትዎ ብዙ ካሎሪዎችን እንዲያቃጥል ያስችለዋል።
2. ብስክሌት መንዳት እግሮችዎን ለማጠንከር ይረዳል
ብስክሌት መንዳት በመገጣጠሚያዎችዎ ላይ ጫና ሳይፈጥር የእግሮቾች እና የታችኛው የሰውነት ክፍልዎን ጡንቻዎች ያጠነክራል። በተለይም የፊት ለፊት የጭን ጡንቻዎችን (quads)፣ መቀመጫን (glutes)፣ የጀርባ ጭን ጡንቻዎችን (hamstrings) እና ባትን (calves) ያጎለብታል ።
3. ብስክሌት መንዳት ለልብ ጤና እና የኮሌስትሮል መጠንዎ እንዲስተካከል ይረዳል
ብስክሌት መንዳት የልብ ጡንቻን እንዲጠነክር በማድረግ ልብ የሚመታበትን ፍጥነት ይቀንሳል ። ከዚህም በተጨማሪ በደም ውስጥ ያለውን የስብ መጠን ወይም ኮሌስትሮልን ያስተካክላል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አዘውትረው ብስክሌት የሚነዱ ሰዎች ለልብና የደም ዝውውር በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። በተጨማሪም "ጥሩ" የሚባለውን የኮሌስትሮል አይነት (HDL) በመጨመር የደም ቧንቧዎች እንዳይደፈኑ ይረዳል።
4. ብስክሌት መንዳት ለአእምሮ ጤና እና ለስሜት መነቃቃት እጅጉን ያግዛል
ብስክሌት መንዳት የውጥረት፣ የድብርት ወይም የጭንቀት ስሜቶችን ለመቀነስ ይረዳል። በሚነዱበት ወቅት በመንገዱ ላይ ወይም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ማድረጎ አጠቃላይ ነገሮች ላይ ያሎትን ትኩረት እና ግንዛቤ (awareness) እንዲያዳብሩ ይረዳዎታል ። ከዚህም በተጨማሪ አእምሮዎ ከዕለት ተዕለት ውጥረት እና ከሚረብሹ ሐሳቦች እንዲርቅ ያደርገዋል።
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከቤት ውጭ ብስክሌት መንዳት በዕድሜ ለገፉ ሰዎች የማሰብ ችሎታን እና ደህንነትን (well-being) ያሻሽላል። የመዛል፣ የመልፈስፈስ ወይም አእምሮዎ የዘገየ የመሰለ ስሜት ከተሰማዎት ቢያንስ ለ10 ደቂቃ ብስክሌት ይንዱ።
ከዚህ በተጨማሪ ብስክሌት መንዳት ጥሩ ስሜት የሚቀሰቅሱ ኢንዶርፊን የተባሉ ሆርሞኖች በሰውነት ውስጥ እንዲለቀቁ በማድረግ የጭንቀት መጠንዎ እንዲቀንስ እና የተሻለ ስሜት እንዲሰማዎት ይረዳዎታል ። ብስክሌት መንዳትን የዘወትር ልምድዎ ሲያደርጉም የበለጠ በራስ የመተማመን ስሜቶ እንዲጨምር ያደርጋል ።
5. ብስክሌት መንዳት የካንሰር ታማሚዎችን ሊረዳ ይችላል
ብስክሌት መንዳት በካንሰር ሕክምና ወቅት ወይም ከሕክምና በኋላ ታካሚዎችን ለመደገፍ አስተማማኝ እና ውጤታማ መንገድ ነው። እ.ኤ.አ. በ 2022 የአሜሪካ የክሊኒካል ኦንኮሎጂ ማኅበር (American Society of Clinical Oncology) የኤሮቢክ እና የጥንካሬ እንቅስቃሴዎች የካንሰር ታማሚዎች እንዲያደርጉ ያበረታታ ሲሆን ብስክሌት መንዳት ደግሞ ምርጥ ጫና የማይፈጥር (low-impact) አማራጭ ነው።
ይህ እንደ ድካም ያሉ የካንሰር ሕክምና የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንዲቀንሱ እና የሕይወት ጥራትዎ እንዲሻሻል ያደርጋል። በየቀኑ ያሎት የኃይል መጠን እና የህመም ስሜት ሊለያይ ይችላል ፤ ስለዚህ ሰውነትዎን በማዳመጥ እና ሐኪሞ የሰጥዎትን መመሪያ በመከተል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግዎን ያረጋግጡ።
ከዚህ በተጨማሪ ብስክሌት መንዳት ክብደትዎን እንዲቆጣጠሩ በማገዝ ለጡት ካንሰር እና ለአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ያሎትን ተጋላጭነት ይቀንሳል።
6. ብስክሌት መንዳት ለጥዋትዎ ጥሩ ጅማሮን ይሰጣል
ቀንዎን እንደ ብስክሌት መንዳት ባሉ ጤናማ ተግባራት መጀመር የደም ዝውውርዎን በማነቃቃት ከእንቅልፍዎ እንዲነቁ ይረዳዎታል ። ይህም ቀኑን የስኬት ስሜት እየተሰማዎት እንዲጀምሩ ያስችልዎታል።
በተጨማሪም ብስክሌት መንዳት የአእምሮዎን የውሳኔ አሰጣጥ እና የማቀድ ብቃትን (executive functioning) በማሻሻል በስራዎ ላይ ይበልጥ አዎንታዊ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ይረዳዎታል።
7.ብስክሌት መንዳት የጤና እክሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይረዳዎታል
የጤና እክሎች እንዳይከሰቱ ለመከላከልም ሆነ ያሉብዎትን በሽታ ለመቆጣጠር ፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ወሳኝ ነው ። አዘውትሮ ብስክሌት መንዳት እንቅስቃሴ አልባ ከሆነ የሕይወት ዘይቤ (sedentary lifestyle) እና ከእሱ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የጤና ችግሮች ለመራቅ ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ነው።
አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደ ስትሮክ (stroke)፣ የልብ ድካም እና ከፍተኛ የደም ግፊት ያሉ የልብና የደም ቧንቧ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል። ብስክሌት መንዳት ደግሞ ዓይነት 2 የስኳር በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።
እንዲያውም የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አዘውትሮ ብስክሌት የሚነዱ የስኳር በሽታ ታማሚዎች በበሽታው ምክንያት የሚከሰት ያለጊዜው የሞት እድልን በ 24% ይቀንሳል ። ይህን ልምድ ቢያንስ ለ5 ዓመት ሳያቋርጡ ከቀጠሉ ደግሞ የመሞት እድልን እስከ 35% ሊቀንስ እንደሚችል ይናገራሉ።
8. ብስክሌት መንዳት የሰውነትን ሚዛን፣ አቋም እና ቅንጅትን ያሻሽላል
የሰውነትዎን ሚዛን ለመጠበቅ እና ብስክሌቱን ቀጥ አድርገው ለመያዝ በሚጥሩበት ጊዜ፣ አጠቃላይ የሰውነትዎን ሚዛን (balance) እና ቅንጅት (coordination) ያሻሽላሉ ፤ አልፎ ተርፎም አረማመዶን ያስተካክልሎታል።
የሰውነት ሚዛን ከእድሜ መጨመር እና ከእንቅስቃሴ ማነስ ጋር ተያይዞ የመቀነስ ዝንባሌ ስላለው፣ ሁልጊዜም እንቅስቃሴ ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በእንቅስቃሴ የሰውነት ሚዛን ሲሻሻል ደግሞ የመውደቅ እና የአጥንት ስብራት አደጋን ለመከላከል ያግዛል።
9. የፍቅር ሕይወትዎን ያነቃቃል
የጤና ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት እንደ ብስክሌት መንዳት ያሉ እንቅስቃሴዎችን አዘውትሮ ማድረግ የደም ዝውውር ሥርዓትን ስለሚያሻሽሉ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፍላጎትን (sex drive) ያነቃቃሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሳምንት ቢያንስ ለሦስት ሰዓታት ብስክሌት የሚነዱ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች፣ እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ጋር ሲነፃፀሩ ለብልት መቆም ችግር (impotence) የመጋለጥ እድላቸው በ30% ያነሰ ነው። ለሴቶች ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ማረጥን (menopause) ሊያዘገይላቸው የሚችል ሲሆን የግብረ ስጋ ግንኙነት ፍላጎታቸውንም በሕይወት ዘመናቸው እንዳይቀንስ ለመከላከል ይረዳቸዋል።
10. የሰውነትዎን የበሽታ የመከላከል አቅም ያጎለብታል
ብስክሌት መንዳት ጉንፋን በተደጋጋሚ እንዳይዝዎ ሊከላከልሎት እንደሚችል ያውቃሉ? ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደ ብስክሌት መንዳት ያሉ የኤሮቢክ (aerobic) እንቅስቃሴዎች በህመም ምክንያት ከሥራ ወይም ከትምህርት የሚቀሩባቸውን ቀናት በ40% ሊቀንሱ ይችላሉ። ብስክሌት መንዳት አስፈላጊ የሆኑ ፕሮቲኖች እና ነጭ የደም ህዋስዎች በሰውነትዎ ውስጥ እንዲመረቱ በማነቃቃት በሽታ የመከላከል አቅምዎን (immune system) ጠንካራ ሆኖ እንዲቆይ ያደርጋል።
በየቀኑ ብስክሌት መንዳት ይቻላል?
አዎ በየቀኑ ብስክሌት መንዳት ይቻላሉ ፤ በተለይም ብስክሌትዎን ለትራንስፖርትነት የሚጠቀሙ ከሆነ ወይም በዝቅተኛ ፍጥነት የሚነዱ ከሆነ በየቀኑ መንዳት ይችላል።
ነገር ግን ሕመም፣ ከፍተኛ ድካም ወይም የጡንቻ መቆጣት ካጋጠመዎት ዕረፍት ይውሰዱ።
ብስክሌትዎን የሚነዱት ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ (fitness) ከሆነ፣ በሳምንት ቢያንስ 1 ቀን ዕረፍት ቢያደርጉ ይመከራል ፤ በተለይ ጉዞዎ ረጅም ወይም ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ከሆነ የዕረፍት ቀን ያስፈልጋል ። ባለሞያዎች እንደሚገልጹትም ብስክሌት የሚነዱ ሰዎች ጉዳትን ለመከላከል እና ብቃታቸውን ለማሻሻል የሰውነት ማገገሚያ ጊዜ (recovery period) ያስፈልጋቸዋል።
ብስክሌት መንዳት የሌለበት ማን ነው?
- ብስክሌት መንዳት ሊያባብሰው የሚችል ማንኛውም ዓይነት ጉዳት ካለብዎት ሙሉ በሙሉ እስኪያገግሙ ድረስ ብስክሌት ባይነዱ የተሻለ ነው።
- ብስክሌት መንዳት ሊያባብሰው የሚችል የጤና እክል ካለብዎ መንዳት ከመጀመርዎ በፊት ሐኪምዎን ማማከር ያስፈልጋል ። የሰውነት ሚዛን፣ የማየት ወይም የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች እነሱን ታሳቢ ተደርገው የተሰሩ ብስክሌት ቢጠቀሙ ይመረጣል።
በአጠቃላይ
ብስክሌት መግዛት ለጤናዎ እና ለደህንነትዎ ሊያደርጉት ከሚችሉ ምርጥ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ነው። ብስክሌት መንዳት በቀላሉ ከዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የሚዋሃድ ፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት አስደሳች ተግባር ነው ። ጥንካሬን ከመገንባትና የአካል ብቃትን ከማሻሻል ጀምሮ ለአእምሮ ጤና ድጋፍን በመስጠት እንዲሁም ከአካባቢዎ ጋር እንዲገናኙ በመርዳት ፤ ብስክሌት መንዳት በየቀኑ ጤናማ ሆነው እንዲኖሩ እና የተሻለ ስሜት እንዲሰማዎት የሚያደርግ ቀላል ግን ኃይል ያለው እንቅስቃሴ ነው።




