ስትሬቺንግ ወይም መንጠራራት አስፈላጊ ነው?
ስትሬቺንግ የጡንቻና የመገጣጠሚያ እንቅስቃሴ ክልልን ለማሻሻል የሚደረግ የመንጠራራት የአካል ልምምድ ነው። በትክክል ከተሰራ ይህ መንጠራራት እንቅስቃሴዎችን በየዕለቱ በቀላሉ ለማከናወን፣ ሰውነትን ተለዋዋጭ ለማድረግ እና ጥሩ የእንቅስቃሴ ብቃትን ለመጠበቅ ይረዳል።
ለምን አስፈላጊ ነው?
1. የሰውነት ተለዋዋጭነትን ያሻሽላል
መደበኛ ስትሬቺንግ ጡንቻዎችንና መገጣጠሚያዎችን በተሻለ የእንቅስቃሴ ክልል እንዲንቀሳቀሱ ሊረዳ ይችላል። ይህም እንደ መራመድ፣ መታጠፍ፣ መዘርጋት እና የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን ይጠቅማል።
2. የጡንቻ መጨናነቅን ሊቀንስ ይችላል
ረጅም ሰዓት ተቀምጦ መስራት፣ ተመሳሳይ እንቅስቃሴን ደጋግሞ ማድረግ ወይም ከባድ ልምምድ ጡንቻዎች እንዲጨናነቁ ሊያደርግ ይችላል። ስትሬቺንግ የጡንቻ መጨናነቅ ስሜትን ለመቀነስና ተለዋዋጭነትን ለማሻሻል ሊረዳ ይችላል።
3. የእንቅስቃሴ ጥራትን ያሻሽላል
በቂ የእንቅስቃሴ ክልል መኖር በስፖርትም ሆነ በዕለት ተዕለት ሥራ የሰውነት እንቅስቃሴን በተሻለ መንገድ ለማከናወን ይረዳል። ለምሳሌ የእግር ጡንቻዎችን መዘርጋት በመራመድ፣ በመሮጥ ወይም በሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚፈለገውን የእንቅስቃሴ ክልል ለማሻሻል ይረዳል።
4. ለዝግጅት ይረዳል
ከስፓርታዊ ልምምድ በፊት የሚደረግ ቀላል የሆነ የስትሬቺንግ ማሟሟቂያ ሰውነትን ለእንቅስቃሴ ለማዘጋጀት ይረዳል። ለምሳሌ እግርን ወደ ፊትና ወደ ኋላ በቀስታ ማንቀሳቀስ ወይም እጆችን በቁጥጥር ማዞር ይቻላል።
5. ከልምምድ በኋላ ለመረጋጋት
ከልምምድ በኋላ የሚደረግ ቀላል ስትሬቺንግ የጡንቻ መጨናነቅ ስሜትን ለመቀነስና ሰውነትን ለማረጋጋት ሊረዳ ይችላል።
ስትሬቺንግን እንዴት መስራት አለብን?
- ከመንጠራራትዎ በፊት ሰውነትዎን በቀላል እንቅስቃሴዎች ያሙቁ
- እጅ እና እግርዎችዎን በቀስታ ይዘርጉ
- በስትሬቺንግ ጊዜ መደበኛ አተነፋፈስን ይቀጥሉ
- ህመም እስኪሰማዎ ድረስ አይንጠራሩ። ቀላል የመሳብ ስሜት ሊሰማዎ ይችላል፣ ነገር ግን ህመም ከተሰማዎ ያቁሙ።
- እያንዳንዱን የስትሬቺንግ አቀማመጥ ለተመጣጣኝ ጊዜ በመያዝ በቀስታ ይመለሱ
- አንዴ ለረጅም ጊዜ ከመስራት በየጊዜው ትንሽ እና በቂ መስራት ይሻላል
ማን ተጨማሪ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል?
- በቅርቡ ጉዳት የደረሰባቸው
- የመገጣጠሚያ ችግር ያላቸው
- በልምምድ ጊዜ ህመም የሚሰማቸው ወይም
- የሰውነት እንቅስቃሴ ገደብ ያለባቸው ሰዎች ልምምድ ከመጀመራቸው ከፊዚዮቴራፒስት ወይም ሌሎች ጤና ባለሙያዎች ምክር ማግኘት ይገባቸዋል።
ስትሬቺንግ ሰውነትን የበለጠ ተለዋዋጭ ለማድረግ፣ የእንቅስቃሴ ክልልን ለማሻሻል እና በዕለት ተዕለት ሕይወት የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚረዳ የእንቅስቃሴ አይነት ነው። በቀስታ፣ በቁጥጥር እና ያለ ህመም እንቅስቃሴውን ማድረግ ዋናው መርህ ነው።




