ፕሮቲንን ጠዋት ላይ መመገብ ለምን ይጠቅማል?
በሳይንሱ አለም ውስጥ አከራካሪ ቢሆንም ቁርስ የቀኑ በጣም አስፈላጊ ምግብ ተብሎ ይጠራል። “ቁርስ ላይ ምን መመገብ አለብዎ?” የሚለው ጥያቄ “ቁርስ መበላት አለበት ወይስ የለበትም?” ከሚለው እኩል አስፈላጊ ነው። ብዙ ጊዜ የተለመደው ቁርስ በሃይል ሰጪ ምግቦች(ካርቦሃይድሬትስ) ብቻ የበለፀገ ቢሆንም ጥሩ የፕሮቲን ምንጭን ማከል ዘላቂ የጤና ጠቀሜታዎችን ይሰጣል።
ሃይልን ለማሻሻል፣ ክብደትን ለመቆጣጠር፣ ጤናማ እርጅናን ለመደገፍ ወይም በቀላሉ ጠግበው ለመቆየት ፕሮቲንን በያዘ አመጋገብ ቀንዎን መጀመር ብልህ ምርጫ ነው።
ፕሮቲን ምንድን ነው?
ፕሮቲን ሰውነታችን ከሚፈልጋቸው ሶስት ዋና ዋና ንጥረ ነገሮች አንዱ ሲሆን ለጡንቻ፣ ለአጥንት፣ ለቆዳ፣ ለሆርሞን፣ ለኢንዛይም እና ለሌሎች በርካታ ሕብረ-ሕዋሳት ስሪት አስፈላጊ በሆኑት አሚኖ አሲዶች የተገነባ የምግብ አይነት ነው። እንደ አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ሰውነትዎ ከፍተኛ መጠን ያለው ፕሮቲንን ባንዴ ማከማቸት ስለማይችል በቀን ውስጥ አዘውትሮ መውሰድ አስፈላጊ ነው።
ጠዋት ላይ ፕሮቲን የመመገብ ጥቅሞች
1. ረዘም ላለ ጊዜ የጥጋብ ስሜት እንዲሰማዎት ያደርጋል
ፕሮቲን ጥጋብን የሚያበረታቱ ሆርሞኖች እንዲለቀቁ ለማድረግ እና የምግብ መፈጨትን ለማዘግየት ይረዳል። ይህም ከቁርስ በኋላ የረሃብ ስሜት በድጋሚ እንዳይሰማዎት በማድረግ ከምሳ በፊት ተጨማሪ መክሰሶች የመመመገብ ዕድሎን ይቀንሳል።
2. ጤናማ የሰውነት ክብደትን ይደግፋል
ጠዋትን በፕሮቲን ምግብ መጀመር የምግብ ፍላጎትን ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ ማስቻሉ ከመደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የተመጣጠነ አመጋገብ ጋር በመሆን በጤናማ መንገድ ክብደትን ለመቀነስ እና ለመጠበቅ ይረዳል።
3. የጡንቻን መጠን ለመጠበቅ ይረዳል
በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ የጡንቻ ጤንነት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ጠዋት ላይ ፕሮቲንን መመገብ ሰውነታችን ጡንቻን ለመጠገን እና ለመገንባት የሚጠቀምበትን የጡንቻ የፕሮቲን ውህደት ሂደት ለማነቃቃት ይረዳል። የቁርስ ፕሮቲን በተለይ ለሚከተሉት ጠቃሚ ነው:-
- እድሜያቸው እየገፋ ላለ አዋቂዎች
- ከበሽታ ወይም ከቀዶ ጥገና ለሚያገግሙ ሰዎች
- አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ ግለሰቦች
4. ቋሚ ጉልበት ይሰጣል
በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠን በፍጥነት እንዲጨምር ከሚያደርጉ ስኳራማ ቁርስዎች በተቃራኒ የፕሮቲን ቁርስ የበለጠ ዘላቂ ኃይልን ይሰጣል። ፕሮቲንን ከጥራጥሬ እህሎች እና ጤናማ ቅባቶች ጋር በማጣመር መመገብ በጠዋት ሙሉ ጉልበት እንዲኖርዎ እና እንዲያተኩሩ ይረዳዎታል።
5. የደም ስኳር ቁጥጥርን ይደግፋል
ፕሮቲን የስኳራማ ምግቦች በአንጀት መመጠጥን በመቀነስ ከምግብ በኋላ በደም ውስጥ የሚኖር የስኳር መጠን ማሻቀብን ለማስቀረት ይረዳል። የቅድመ የስኳር ህመም፣ የስኳር ህመም ወይም የኢንሱሊን መቋቋም ህመም ያለባቸው ሰዎች ፕሮቲናማ ቁርስን መመገብ ከአጠቃላይ ጤናማ የአመጋገብ እቅድ ጋር በመጣመር የደም ስኳር ቀጥጥርን ያሻሽላል።
6. የአዕምሮ ትኩረትን ያሻሽላል
ፕሮቲንን የያዘ የተመጣተነ ቁርስ ለአእምሮ ስራ የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን በማቅረብ ትኩረትን ፣ ንቃትን እና ምርታማነትን በጠዋት ለማሻሻል ይረዳል።
ምን ያህል ፕሮቲን ቁርስ ላይ መመገብ አለብን?
አዋቂዎች ቁርስ ላይ ከ 20-30 ግራም ፕሮቲንን በመመገብ መጠቀም ሲችሉ የየግለሰቡ የፕሮቲን ፍላጎት እንደ እድሜ፣ የሰውነት መጠን፣ የእንቅስቃሴ ደረጃ እና ሌሎች የጤና ሁኔታዎች ይለያያል። የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎ ወይም የስነ-ምግብ ባለሙያዎ ለእርስዎ ትክክለኛውን መጠን ለመወሰን ሊረዳዎት ይችላል።
ከፍተኛ ፕሮቲን የያዙ ጤናማ የቁርስ ሀሳቦች
ከእነዚህ በፕሮቲን የበለፀጉ ምግቦች ውስጥ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ለማካተት ይሞክሩ፡-
- እንቁላል በእህል ዳቦ
- አይብ እና ፍራፍሬ
- ከወተት፣ ከለውዝ ወይም ከዘሮች ጋር የተቀላቀለ የአጃ ዱቄት
- የእህል ዳቦ በኦቾሎኒ ወይም በአልሞንድ ቅቤ
- ቶፉ ከአትክልት ጋር
- ባቄላ ወይም ምስር ከእህል ዳቦ ጋር
- የበሰለ አሳ ከአትክልት ጋር
ማን መጠንቀቅ አለበት?
ከፍተኛ ፕሮቲን ለብዙ ሰዎች ጠቃሚ ቢሆንም አንዳንድ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ወይም የሜታቦሊክ ሁኔታዎች ያለባቸው ሰዎች የፕሮቲን ምግቦችን መገደብ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የአመጋገብ ማሻሻያ የሚያስፈልገው የጤና ችግር ካለብዎ ሁልጊዜ የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎን ምክሮች ይከተሉ።
ጠዋት ላይ ፕሮቲን መብላት በጤናዎ ላይ ጠቃሚ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ቀላል ልማድ ነው። በፕሮቲን የበለፀገ ቁርስ የጡንቻ ጤንነትን ይደግፋል፣ የደም ስኳር ቁጥጥርን ያሻሽላል፣ ቋሚ ሃይልን ይሰጣል እንዲሁም ጤናማ ክብደትን ለመጠበቅ ያስችላል።




