ልጅዎ በትክክል ማደግ አለማደጉን ለመመዘን የልጅዎ የሕፃናት ሐኪም (Pediatrician) በየጊዜው በሚደረጉ የጤና ክትትል ወቅት የልጅዎን የእድገት ደረጃ ያጠናል፡፡ ይህን ሐኪምዎ የእድገት ደረጃን ለማጥናት የሚጠቀምበት ዝርፍ ዲቨሎፕመንታል ማይል እስቶን (Developmental milestones) ይባላል።
የሕፃናት እድገት ደረጃዎች (Developmental milestones) አብዛኞቹ ሕፃናት በተወሰነ ዕድሜ ላይ ሊያደርጓቸው የሚገባቸው ዕድሜ ተኮር ችሎታዎች ናቸው። እነዚህ ደረጃዎች ልጅዎ እንደሚጠበቀው እያደገ እና እየተለወጠ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። ሐኪምዎ የአካል ምርመራ የሚያደርግ ሲሆን ልጅዎ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ፣ እንደሚጫወት እና ድምፅ እንደሚያወጣ ለማየት ከልጁ ጋር ግንኙነት ይፈጥራል።
እ.ኤ.አ. በ2022 ባለሙያዎች ቢያንስ ከ4 ሕፃናት ውስጥ 3ቱ (75%) ሊያደርጓቸው የሚችሏቸውን ነገሮች ለማካተት የእድገት ደረጃዎችን ዝርዝር አዘምነዋል። ልጅዎ በተጠበቀው ዕድሜ ላይ የተወሰኑ ደረጃዎችን ካላሳየ፣ የሕፃናት ሐኪምዎ የእድገት መዘግየት (developmental delays) መኖሩን ለማረጋገጥ ምርመራዎችን ሊጠቁም ይችላል። እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንደ የአካል (physical)፣ የንግግር (speech) እና የተለያዩ ሕክምናዎችን ሊያዝልዎት ይችላል።
የእድገት ደረጃዎች ዓይነቶች
ለሕፃናት እና ለልጆች የሚቀመጡ የእድገት ደረጃዎች በአራት ዋና ዋና ቡድኖች ይከፈላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንዱ ደረጃ ከሌላው ጋር ሊደራረብ ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህን ቡድኖች ማወቅ ደረጃዎቹን ለመከታተልና ከሐኪምዎ ጋር ለመወያየት ይረዳዎታል።
- ጉልህ ክሂሎቶች (ግሮስ ሞተር/Gross motor):- ለመቀመጥ፣ ለመቆም፣ ለመራመድ፣ ለመሮጥ፣ ወዘተ የመሳሰሉ በጉልህ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን ጡንቻዎችን በመጠቀም የሚደረግ ጥረት
- ረቂቅ ክሂሎቶች (ሶፍት ሞተር/Fine motor) :- ልጅዎ ለመብላት፣ ለመሣል፣ ለመልበስ፣ ለመጫወት፣ ለመጻፍ እና ሌሎች ቴክኒካዊ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያደርገው ጥረት
- የቋንቋ፣ ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታዎች :- መናገር፣ የሰውነት ቋንቋን (Body Language) እና የእጅ ምልክቶችን በመጠቀም መግባባት እና ሌሎች የሚናገሩትን መገንዘብ መቻል እና ልጅዎ ስሜቱን እንዴት እንደሚያሳይ እና ከቤተሰብ፣ ከጓደኞች እና ከመምህራን ጋር ግንኙነት እንዴት እንደሚፈጥር (ለምሳሌ ሲስቁለት መልሶ መሳቅ ወይም ስሙን ሲጠሩት ወደ እርስዎ ማየት)።
- የዕውቀት (cognitive) ችሎታዎች :- ልጅዎ እንዴት እንደሚያስብ፣ እንደሚማር እና ችግሮችን እንደሚፈታ (ለምሳሌ ስለ አንድ ነገር ለማወቅ ወደ አፉ ማስገባት)።
ሕፃኑ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እስከ 1 ዓመቱ ድረስ የምንጠብቀው እድገት ምንድን ነው?
አዲስ የተወለደ ሕፃን በመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ከሰውነቱ የሚወጣ ትርፍ ፈሳሽ እና ገና በመጀመር ላይ ያለ የአመጋገብ ሂደት ምክንያት፣ ክብደቱ ከ10% (በማህፀን በር የተወለደ) እስከ 12% (በቀዶ ጥገና የተወለደ) ሊቀንስ ይችላል። ይሁን እንጂ ሕፃኑ ጡት በአግባቡ መጥባትን ሲለምድ እና እናቱም አመጋገቡን ስትለማመደው የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦቱ እየተሻሻለ ይሄዳል። ሕፃናት ሁለት ሳምንት ሲሞላቸው የተወለዱበትን ክብደት መልሰው የሚያገኙ ወይም የሚበልጡ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ወር ውስጥም በቀን በአማካይ 30 ግራም ያህል ክብደት እንዲጨምሩ ይጠበቃል።
ከ3 እስከ 4 ወር ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ፣ የሕፃናት የዕድገት ፍጥነት በትንሹ በመቀነስ በቀን ወደ 20 ግራም እንዲጨምሩ ይጠበቃል። በመቀጠልም ከ 4 እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የሕፃኑ ክብደት በተወለደበት ጊዜ ከነበረው ክብደት በእጥፍ እንዲጭምር ይጠበቃል።
የሕፃናት እድገት ፍጥነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢሄድም፣ እስከ መጀመሪያው ዓመት ልደት ድረስ ትልቅ ለውጥ ይታያል። ልጅዎ አንድ ዓመት ሲሞላው፣ ሲወለድ የነበረው ክብደት በሦስት እጥፍ ያድጋል፤ ቁመቱ በ50% ይጨምራል፤ እንዲሁም የጭንቅላት ዙሪያው በ10 ሴ.ሜ (4 ኢንች) ያህል ይጨምራል። በአጠቃላይ በ12 ወሩ በአማካይ 10 ኪ.ግ. ይመዝናል፤ ቁመቱ ደግሞ 75 ሴ.ሜ. አካባቢ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በ 3 ወር ዕድሜው ሕፃኑ ጭንቅላቱን መደገፍ ይጀምራል፡፡ በ 6 ወሩ ደግሞ ያለ ድጋፍ ይቀመጣል፡፡ በ12 ወሩ ያለ ድጋፍ ይቆማል፡፡ ከ 3 እሰከ 4 ወር ባለው ዕድሜ ሕፃኑ ነገሮችን በእጁ መያዝ ይጀምራል፡፡ ከ 5 እስከ 6 ወሩ ደግሞ ዕቃዎችን ከእጅ ወደ እጅ ማስተላለፍ ይጀምራል፡፡
ማኅበራዊ እድገቱን ስናይ ደግሞ በ 6 እሰከ 8 ሳምንቱ ፈገግታ ይጀምራል፡፡ በ 4 ወሩ መሳቅ፣ ከ6 እስከ 8 ወሩ ደግሞ እንግዳ ሰው ሲያይ መጨነቅ ይጀምራል፡፡ የቋንቋ ችሎታን በተመለከተ በ 9 ወሩ 'ባባ' እና 'ማማ' ማለት ይጀምራል፤ በ 12 ወሩ ደግሞ ጥቂት ቃላትን መጠቀም ይጀምራል፡፡
የሕፃናት አንጎል በመጀመሪያው የሕይወት ዓመት ውስጥ መጠኑን በእጥፍ በመጨመር እጅግ ፈጣን እድገት የሚያሳይ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ተጨማሪ የ15% ጭማሪ ያደርጋል። ይህንን እድገት ከአዋቂ ሰው የአንጎል መጠን ጋር ስናነጻጽረው፣ የአንድ ወር ሕፃን አንጎል የአዋቂን 36% ያህል ብቻ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ዕድሜው ግን ወደ 72% ያድጋል። ልጅዎ ሁለት ዓመት ሲሞላው ደግሞ የአንጎሉ መጠን የአዋቂን 83% ያህል ይደርሳል፤ ይህም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የሚከናወነው የአንጎል እድገት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል።
እነዚህ የሕፃናት የዕድገት ደረጃዎች ልጅዎ እያደገ ሲሄድ የሚያሳያቸውን አስገራሚ ለውጦች ለመከታተል ይረዱዎታል። ከታች በየወሩ የተከፋፈሉ ዋና ዋና የዕድገት ምልክቶች ተዘርዝረዋል፦
እስከ 2 ወር
ይህ ወቅት ከተወለዱ በኋላ እጅግ ፈጣን የሆነ የዕድገት ሂደት የሚታይበት ጊዜ ነው።
- ጉልህ እንቅስቃሴዎች፦ በሆዳቸው ሲተኙ ራሳቸውን ቀና ያደርጋሉ፣ ጭንቅላታቸውንም ወደ ጎን ማዞር ይችላሉ።። እጆቻቸው ወደ ጎን ተዘርግተው ይያዛሉ። የእጅና እግር እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ የመንፈራገጥ ሁኔታዎች ሲሆኑ፣ እጆችን ያለምንም ዓላማ የመክፈትና የመዝጋት ድርጊቶች ይታዩባቸዋል።በእጃቸው መዳፍ ላይ ጣትዎን ሲያስቀምጡ ጠበቅ አድርገው ይይዙታል።
- ረቂቅ ክሂሎቶች፡ በሁለቱም ዓይኖቻቸው ዕቃዎችን ወይም ሰዎችን መከታተል ይችላሉ
- የእውቀት ደረጃ፡ እንደ ፈገግታ ያሉ የፊት ገጽታዎችን መለየት የሚችሉ ሲሆን፣ እነዚህ ገጽታዎች በተለያዩ ሰዎች ፊት ላይ ቢታዩም እንኳ ተመሳሳይ መሆናቸውን የመገንዘብ ችሎታ አላቸው። አንድ ዕቃ ከዓይናቸው ስር ሲሰወር፣ ዕቃው በነበረበት ቦታ ላይ ለጥቂት ጊዜ በትኩረት ይመለከታሉ።
- የቋንቋ፣ ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታዎች፡ ልጅዎ የሰዎችን ድምፅ ሲሰማ ዞር ብሎ በመመልከት እና ሆን ብሎ የዓይን ግንኙነትን መጠበቅ ይጀምራል። ሲያናግሩት ወይም ሲስቁለት በፈገግታ ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፣ እንደ “አአአ”፣ “ጋህ” እና “ኦኦኦ” ያሉ ለስላሳ ድምፆችን በማውጣት የቋንቋ እድገቱን ያሳያል። በተለይም እርስዎ ሲያናግሩት በተራው ድምፅ በመመለስ የሁለትዮሽ ተግባቦት ለመፍጠር ይሞክራል። እንዲሁም ፍላጎቱን ለመግለጽ ሲርበው፣ ሲደክመው፣ ዳይፐር ሲርሰው ወይም መታቀፍ ሲፈልግ በለቅሶ ስሜቱን ይገልጻል።
4 ወር
- ጉልህ እንቅስቃሴዎች፦ በዚህ ወቅት በሆዱ በሚተኛበት ጊዜ በክርኑ በመደገፍ እና ጭንቅላቱን ቀጥ አድርጎ በመያዝ በዙሪያው ያለውን አካባቢ በንቃት መመልከት የሚችል ሲሆን፣ በጀርባው ሲተኛ ደግሞ ሁለቱን እጆቹን በደረቱ ላይ በማምጣት ጣቶቹን ማነካካት ይጀምራል። በሰው ወይም በትራስ ድጋፍ ሲቀመጥ ጭንቅላቱን ሳይወዘወዝ ቀጥ አድርጎ መያዝ ከመቻሉም በላይ፣ በአቅራቢያው ያለን መጫወቻ ለመያዝ እጁን መዘርጋት ይጀምራል።
- ረቂቅ ክሂሎቶች፡ ሕፃናት መጫወቻን በእጃቸው መያዝ፣ መመልከት፣ ማወዛወዝ እና ለማኘክ መሞከር ይጀምራሉ። ዕቃዎችን መጨበጥ ብቻ ሳይሆን፣ በራሳቸው ፍላጎት መልቀቅን ይማራሉ።
- የእውቀት ደረጃ፡ ድምፅ ወደሚሰማበት አቅጣጫ ራሳቸውን ያዞራሉ። በአመጋገብ ወቅት፣ ሕፃናት ትኩረታቸውን በእናታቸው ላይ ብቻ ማድረጋቸውን ያቆማሉ፤ ይልቁንም በአካባቢያቸው ባሉ ነገሮች መሳብ ይጀምራሉ። በእናታቸው እቅፍ ውስጥ ሳሉ፣ ወደ ውጭ ዞር ብለው አካባቢውን መመልከትን በመምረጥ ሰውነታቸውን ሊያዞሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ጡት ወይም ጡጦ ሲያይ አፉን ይከፍታል።
- የቋንቋ፣ ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታዎች፡ ልጅዎ በዚህ የእድገት ደረጃ ላይ በማኅበራዊ ግንኙነት ረገድ ትልቅ መነቃቃት የሚያሳይ ሲሆን፣ በተለይም በመስተዋት ፊት በሚሆንበት ጊዜ ድምጽ እያወጣ ለራሱ ፈገግ ይላል። በደስታ ከትክት ብሎ መሳቅ የሚጀምርበት ወቅት ከመሆኑም ባለፈ፣ የተለያዩ ድምፆችን በማውጣት ከራሱ ጋር ይጫወታል። ከዓይኑ ርቀው ቆይተው ሲመለሱ እርስዎን ሲያይ በፈገግታ የታጀበ ከፍተኛ መነቃቃት ያሳያል። ከእርስዎ ውጭ ያለ ሌላ ሰው ድምፅ ሲሰማ ማልቀስም ያቆማል። መጫወቻዎችን ወይም ሰዎችን ሲመለከት ድምፅ ያወጣል፣ አልፎ አልፎም ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው የደስታ ጩኸቶችን ያሰማል።
6 ወር
- ጉልህ እንቅስቃሴዎች፦ ልጅዎ ወደ ስድስት ወር ዕድሜው ሲቃረብ የአካል ብቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር ሲሆን፣ በተለይም ከጀርባው ወደ ሆዱ መገልበጥ ይጀምራል። በጀርባው ተኝቶ እያለ እግሮቹን በማንቀሳቀስ ይጫወታል። በሆዱ በሚተኛበት ጊዜ መላ ደረቱን ከመሬት ላይ በማንሳት ሁለቱን እጆቹን ቀጥ አድርጎ በመደገፍ ጥንካሬውን ያሳያል። እንዲሁም ያለ ምንም ድጋፍ ወይም በጥቂት ድጋፍ ብቻ መቀመጥ ይችላል። መሬት ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ ሚዛኑን ለመጠበቅ በእጆቹ ወደ ፊት ይደገፋል። በተጨማሪም ሰውነቱን ወደ ፊት ለማንቀሳቀስ መነሻ የሚሆነውን የዳዴ መሄጃ (crawling) አቀማመጥ መለማመድ ይጀምራል።
- ረቂቅ ክሂሎቶች፡ ሕፃናት መጫወቻን በሁለቱም እጆቻቸው በአንድ ጊዜ ይይዛሉ። ትናንሽ ነገሮችን በጣቶቻቸው አማካኝነት በመንካት በአውራ ጣታቸውና በሌሎች ጣቶቻቸው ሰብሰብ አድርገው ያነሳሉ። ትንሽ መጫወቻን በአንድ እጃቸው አንስተው ወደ ሌላኛው እጃቸው ያዛውራሉ። የሚፈልጓቸውን መጫወቻዎች ለመያዝ እጃቸውን ይዘረጋሉ።
- የእውቀት ደረጃ፡ የስድስት ወር ሕፃን እጆቹን በሚገባ የተረዳበት ደረጃ ላይ ሲሆን፣ በቅርቡም ዕቃዎችን እንደፈለገ የማንቀሳቀስና የመጠቀም (manipulate) ብቃትን ይለምዳል። ስለ ነገሮች ምንነት ይበልጥ ለመረዳት እና ለመማር ዕቃዎችን ወደ አፋቸው ይከታሉ። ይህ ድርጊት ሕፃናት በአፋቸው አማካኝነት የነገሮችን ቅርፅ፣ ልስላሴ ወይም ጥንካሬ፣ እና ሙቀት የሚገነዘቡበት ዋነኛው የመመርመሪያ መንገዳቸው ነው።
- የቋንቋ፣ ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታዎች፡ ልጅዎ በዚህ ወቅት የተግባቦት አድማሱን በማስፋት እንዲያነሱት እጆቹን ወደ ላይ የሚዘረጋ ሲሆን፣ እንደ "ባ"፣ "ዳ"፣ "ጋ" እና "ካ" ያሉ የተለያዩ ድምፆችን ማውጣት ይጀምራል። በድምፆች በሚጫወትበት ጊዜ እንደ ማጉረምረም እና ማቃሰት ያሉ ጥልቅ ድምፆችን ከመጠቀም ባለፈ፣ የእርስዎን ድምፆች የመድገም እና በከፍተኛ ሁኔታ የመሳቅ ዝንባሌ ያሳያል። በማኅበራዊ ረገድ በመስተዋት ፊት መቆየት የሚወድ ሲሆን፣ አዳዲስ ሰዎችን ሲያይ በትኩረት በመመልከት፣ ፊት በማኩሰተር ወይም በማልቀስ ከሚያውቃቸው ሰዎች የመለየት ብቃቱን ያሳያል።
9 ወር
- ጉልህ እንቅስቃሴዎች፦ ራሱን ችሎ ይቀመጣል። ያለ ምንም ድጋፍ መቀመጥና ተኝቶ ከነበረበት በራሱ ጥረት ወደ መቀመጥ መሸጋገር ይጀምራል። በዚህ ወቅት አንዳንዶች ዳዴ መሄድ (crawling) የሚጀምሩ ሲሆን፣ ድጋፍ በመጠቀም ወይም የቤት እቃዎችን በመያዝ ራሳቸውን ወደ ላይ በመሳብ መቆም ይችላሉ። በቆሙበት ጊዜም የሰውነታቸውን ክብደት በእግሮቻቸው ላይ መሸከም ከመቻላቸውም በላይ፣ የቤት እቃዎችን ለድጋፍ በመጠቀም መሬት ላይ ያሉ መጫወቻዎችን ለማንሳት ጎንበስ ማለት ይጀምራሉ።
- ረቂቅ ክሂሎቶች፡ ልጅዎ በዚህ የእድገት ደረጃ ላይ እጆቹን የመጠቀም ብቃቱ (fine motor skills) በከፍተኛ ሁኔታ ይሻሻላል። በተለይም የአውራ ጣቱን እና የሌሎች ጣቶቹን ጫፎች በመጠቀም ትናንሽ መጫወቻዎችን በአንድ እጁ ማንሳት ይጀምራል። እንዲሁም የጣት ጫፎቹን እና አውራ ጣቱን በማቀናጀት ቀጭን ክር ወይም ተመሳሳይ ነገሮችን ከጥቂት ሙከራዎች በኋላ መልቀም ይጀምራል። ሁለት መጫወቻዎችን በማጋጨት ወይም በማጨብጨብ ድምፅ ማውጣትም ይጀምራል። ዕቃዎችን ከአንድ እጅ ወደ ሌላኛው በደንብ ያዛውራል።
- የእውቀት ደረጃ፡ በዘጠኝ ወር ዕድሜ ላይ የሚታየው ዋነኛው የዕድገት ምዕራፍ ሕፃናት አንድ ነገር ከዓይን ቢሰወርም እንኳ መኖሩ እንደማያበቃ የሚረዱበት ነው። ከአራት እስከ ሰባት ወር ባለው ዕድሜ ላይ ያሉ ሕፃናት የወደቀን ነገር ለማግኘት ወደ ታች ይመለከታሉ፤ ነገር ግን ዕቃው ወዲያው ካልታያቸው ፍለጋቸውን ያቆማሉ። በአንፃሩ ዘጠኝ ወር የሆናቸው ሕፃናት፣ አንድ ነገር ቢሰወርባቸውም መፈለጋቸውን ይቀጥላሉ፤ ይህም በጨርቅ የተሸፈኑ ወይም በሰው ጀርባ የተደበቁ ዕቃዎችን ፈልገው እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
- የቋንቋ፣ ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታዎች፡ ልጅዎ በዚህ ዕድሜ ላይ አዋቂዎች የሚያወጡትን ቀላል ድምፆችን የማስመሰል ብቃት የሚያሳይ ሲሆን፣ እንደ "ዳ"፣ "ጋ"፣ "ካ" እና "ባ" ያሉ የተለያዩ ድምፆችን በማቀላቀል ማውራት (babbling) ከመቻሉም ባለፈ እንደ "ባባ"፣ "ዳዳ" ወይም "ማማ" ያሉ ቃላትን በግልጽ መናገር ይጀምራል። "እባክህን ስጠኝ" ወይም "መልሰው" የሚሉ ቀላል ትዕዛዞችን ተረድቶ ዕቃዎችን የመስጠት ወይም የመመለስ ተግባርን ያከናውናል። እንደ "አየሁህ" ወይም ማጨብጨብ ያሉ ቢያንስ አንድ የልጆች ጨዋታዎችን መጫወት የሚወድ ሲሆን፣ የቤተሰብ አባላትን የመለየትና ከሚያውቋቸው አዋቂዎች ጋር መሆንን የመምረጥ ጠንካራ ማኅበራዊ ስሜት ያሳያል። አዳዲስ ሰዎችንም ይፈራል። በተጨማሪም ስሙ ሲጠራ ምላሽ ይሰጣል እናም ስሜቱን በፊቱ እንቅስቃሴ ያሳያል።
12 ወር (1 ዓመት)
- ጉልህ እንቅስቃሴዎች፦ ልጅዎ ወደ አንድ ዓመት ዕድሜው ሲቃረብ የአካል ብቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሻሻል ሲሆን፣ ያለምንም ድጋፍ በተስተካከለ ሁኔታ ከመቀመጡም ባለፈ ከተኛበት ወይም ካለበት ቦታ በራሱ ጥረት ወደ መቀመጥ አቀማመጥ መሸጋገር ይችላል። ተቀምጦ ከነበረበት ራሱን ወደ ላይ በመሳብ መቆም የሚችል ሲሆን፣ በቆመበት ቦታም መልሶ የመቀመጥ ብቃት ይኖረዋል። በዚህ ወቅት የቤት እቃዎችን ለድጋፍ በመጠቀም ዙሪያውን መዞር (cruising) የሚጀምር ሲሆን፣ በአማራጭም በዳዴ (crawling) ወይም ተቀምጦ በመንሸራተት (bottom shuffle) ሊንቀሳቀስ ይችላል፤ እንዲሁም አንዳንዶች ያለምንም ድጋፍ ለብቻቸው መቆም የሚጀምሩበት ወቅት ነው።
- ረቂቅ ክሂሎቶች፡ ልጅዎ በዚህ የእድገት ደረጃ ላይ የእጆቹን ጥቃቅን እንቅስቃሴዎች (fine motor skills) በሚገባ ማቀናጀት የሚችል ሲሆን፣ በተለይም የመጽሐፍ ገጾችን ለማገላበጥ መርዳት እና ትናንሽ ኳሶችን መወርወር ይጀምራል። የአውራ ጣቱን እና የጠቋሚ ጣቱን ጫፎች በመጠቀም ቀጭን ክር ወይም ትናንሽ ነገሮችን በንክኪ የመልቀም ብቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይዳብራል።
- የእውቀት ደረጃ፡ ልጅዎ ወደሚፈልገው እቃ ጣቶቹን ይጠቁማል። ቻው ለማለት እጁን ያውለበልባል። የሆነ እቃ የት እንዳለ ስትጠይቋቸው ወደሱ ይመለከታሉ። የተደበቀ ዕቃን ይፈልጋል፤ ትናንሽ ዕቃዎችን በትልቅ ዕቃ ውስጥ ይከታል።
- የቋንቋ፣ ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታዎች፡ ከ“ማማ” ወይም “ዳዳ” በተጨማሪ ቢያንስ አንድ ሌላ ትርጉም ያለው ቃል መናገር ይችላል።"አይሆንም" (No) የሚለውን ቃል ትርጉም ይረዳል። ስሙ ሲጠራ በትኩረት በመመልከት ምላሽ መስጠት ይጀምራል። ልብስ በሚለብስበት ጊዜም እጁን ወይም እግሩን ወደ ፊት በመዘርጋት ትብብር ያደርጋል። በምልክት የታጀቡ ቀላል ትዕዛዞችን ይከተላሉ (ለምሳሌ፡ እጅዎን እየዘረጉ "ስጠኝ" ሲሉዎት ዕቃውን መስጠት)፣ ነገር ግን ወዲያውኑ መልቀቅ ሊያስቸግረው ይችላል። ለስላሳ አሻንጉሊቶችን በማቀፍ ይጫወታሉ።
ልጄ ጊዜዉን ጠብቆ እያደገ አይደለም፣ ምን ላድርግ?
ልጅዎ በዕድሜው ልክ ወደሚጠበቀዉ ወደ መደበኛዎቹ የእድገት ደረጃዎች ላይ ካልደረሰ ከሐኪምዎ ጋር ይነጋገሩ። ነገር ግን እያንዳንዱ ልጅ በተለየ ፍጥነት እንደሚያድግ ልብ ይበሉ፡፡
ልጅዎ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎችን ወይም ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ከሆነ፤ ወይም ከሌሎች ጋር በተለይም እንክብካቤ ከሚያደርጉለት ሰዎች ጋር በደንብ የማይገናኝ ከሆነ ሐኪምዎን ያነጋግሩ። እንዲሁም ሰዎች ሲጠሩት፣ ሲያናግሩትም ሆነ ሲያጫውቱት በአግባቡ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ የመስማት ችግር ሊኖር ስለሚችል የሕፃናት ሐኪም ያነጋግሩ፡፡
መደበኛ የሕክምና ጉብኝቶች ለምን ያስፈልጋሉ? መደበኛ የህክምና ክትትል በሚያደርግበት ወቅት ሐኪሙ ልጅዎ እንደተጠበቀው እያደገ መሆኑን ለማወቅ ተገቢውን ምርመራ ያደርጋል፡፡ ልጅዎ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ክትባት ያገኛል፡፡ በተጨማሪም ሐኪሙ ልጅዎን እንደ ኦቲዝም ያሉ የእድገት ችግሮች ምልክቶች እንዳሉ ይፈትሻል፡፡ ስለዚህም ለልጅዎ የሕክና ክትትል ወይም ምርመራ መደበኛ ቀጠሮዎች መቼ እንደሚያደርጉ ከልጅዎ ሐኪም ጋር ይነጋገሩ፡፡
ሕፃናት በዕድሜያቸው ልክ እንዲያድጉ ከወላጆች ምን ይጠበቃል?
- ትክክለኛ አመጋገብ ፡- ሕፃኑ እስከ 6 ወሩ የእናት ጡት ብቻ መጥባት አለበት (ውሃ ሳይቀላቀል)። ከ 6 ወር ጀምሮ ተጨማሪ ምግብ መጀመር፤ እንዲሁም እስከ 12 ወሩ የእናቱን ጡት ማጥባት መቀጠል፡፡
- ከአመመው ቶሎ ወደ ጤና ጣቢያ መውሰድ፡፡
- ጠዋት ጠዋት ከ 15 – 30 ደቂቃ፣ ዐይኑን እና የዘር ፍሬውን በጨርቅ ሸፍኖ፣ ምንም ዓይነት ቅባት ሳይቀባ ፀሐይ መሞቅ አለበት።
- ክትባት ጊዜውን ጠብቆ መከተብ አለበት።
- ወቅቱን ጠብቆ በሚገባ የሐኪም ክትትል ማድረግ።



