ከባድ የወር አበባ ህመም እና ኢንዶሜትሪዮሲስ (Endometriosis)

Elsabet Azezew
Jul 14, 2025
undefined

 

ከባድ የወር አበባ ህመም እና ኢንዶሜትሪዮሲስ (Endometriosis)

ከባድ ህመም ያለው የወር  አበባ  በህክምና አጠራር ዲስሜኖሬያ በመባል ይታወቃል።ብዙ ሴቶች የዚህ ህመም ተጠቂዎች ናቸው ። አብዛኛዎቹ ሴቶች ይህ ችግር የሚያጋጥማቸው በጉርምስና ወቅት ሲሆን  በብዛት  የወር አበባ ከጀመሩ ከአራት እስከ አምስት ዓመታት ባለው ጊዜ  ውስጥ ነው። ይህ ችግር እድሜ እየጨመረ በመጣ ቁጥር እየቀነሰ ይሄዳል።

በወር አበባ ወቅት ህመም የሚሰማቸው ሴቶች በታችኛው የሆድ ክፍል ውስጥ ቁርጠት ይኖራቸዋል።ቁርጠቱ እንደየሰው የሚለያይ ሲሆን  ቀላል ወይም ከባድ ሊሆን ይችላል። ከእዚህ ጋር በተያያዘ  የጀርባ ወይም የጭን ላይ ህመም አብሮ ሊኖር ይችላል። ህመሙ በአብዛኛው የሚኖረው በወር አበባ ጊዜ ወይም የወር አበባ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ቀናቶች ነው ።  

ከላይ ከጠቀስናቸው ምልክቶች  በተጨማሪ  አንዳንድ ሴቶችም የሚከተሉት ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል ፡

  • ማቅለሽለሽ 
  • ተቅማጥ
  • ከፍተኛ ድካም
  • ራስ ምታት
  • የሆድ መነፋት (በሆድ ውስጥ የመሞላት ስሜት) እና የመሳሰሉት 

ህመሙ እንዴት ይከሰታል ?

የወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ህመም የሚከሰተው ፕሮስታግላንዲን የሚባሉ ኬሚካሎች በወር አበባ ጊዜ በማህፀን ውስጥ ስለሚለቀቁ ነው ። እነዚህ  ኬሚካሎች በማህፀን ውስጥ የጡንቻ መኮማተር ያስከትላሉ ይህም ህመም እንዲሰማን ያደርጋል ከዚህ ጋር ተያይዞ የማህጸን ግድግዳ በሚኮማተርበት ገዜ ወደ ማህፀን የሚሄደውን የደም  እና ኦክሲጅን  አቅርቦትን ስለሚቀንስ ህመም እንዲኖረን ያደርጋሉ። አንዳንድ ሴቶች ላይ በተለይ  ልክ በወሊድ ግዜ እንደሚኖረው  ምጥ እነዚህ መኮማተሮች ከፍተኛ ህመም እና ምቾት መንሳት ያመጣሉ። ይህ ፕሮስጋንዲን የተባለው ኬሚካል  አንዳንድ ሴቶች ለሚያጋጥማቸው የማቅለሽለሽ እና ተቅማጥ ምልክቶችም  አስተዋጽኦም አለው።

አንዳንድ የሕክምና ሁኔታዎች በወር አበባዎ ወቅት ህመሙን ሊያባብሱት ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል በዋነኛነት ኢንዶሜትሪዮሲስ (endometriosis) ይጠቀሳል ። 

                               ኢንዶሜትሪዮሲስ (endometriosis)

ኢንዶሜትሪዮሲስ የሚከሰተው በተለምዶ በሴቷ ማህፀን ውስጥ የሚገኙ የሰውነት ህዋሳት ከማህፀን ውጭ ሲያድጉ ነው። ይህ ከማህፀን ውጭ የሚያድገው የሰውነት ህዋስ እንደ ማንኛውም በማህፀን ውስጥ እንደሚገኝ የሰውነት ህዋስ በወር አበባ ጊዜ ሊሰበር፣ ሊደማ እና የወር አበባ ምልክቶችን ሊያመጣ ይችላል። እነዚህ የሰውነት ህዋሳት ሊያድጉባቸው ከሚችሉባቸው ቦታዎች በዋነኝነት እንቁልጢ ፣ የማህፀን ቱቦዎች፣ አንጀት ፣ የማህፀን  በር ፤ እንደ ሳንባ እና የመሳሰሉት አካላት  ይጠቀሳሉ።

   ኢንዶሜትሪዮሲስ በምን ምክያት ሊከሰት ይችላል?

የኢንዶሜትሪዮሲስ መንስኤው ባይታወቅም ለምን ሊከሰት እንደሚችል በተመለከተ ግን የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች አሉ ። በዋነኝነት የሚጠቀሰው ሃሳብ በወር አበባ ጊዜ አነስተኛ መጠን ያለው የወር አበባ ደም ወደኃላ ከማህፀን ወደ የማህፀን ትቦዎች በመፍሰስ ወደ የዳሌ ወለል ሲገባ እና ያረፈበት ቦታ ላይ እነዚህ የሰውነት ህዋሳት ሲያድጉ ነው። ይህ ፅንሰ ሃሳብ በሕክምናው አለም ሪትሮ ግሬድ ሜንስትሬሽን ቲዮሪ (retrograde menstruation theory)  በመባል ይታወቃል።

 

   ኢንዶሜትሪዮሲስ ምን አይነት ምልክቶችን ያመጣል?

አንዳንድ ኢንዶሜትሪዮሲስ ችግር ያለባቸው ሴቶች ምንም አይነት ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ ።አንዳንዶች ደግሞ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያሉ። ኢንዶሜትሪዮሲስ ያለባቸው ሴቶች ሊያሳዩአቸው ከሚችሏቸው ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ ፦

 

   ከባድ ወይም ቀላል የሆነ የማህፀን ህመም 

    የማህፀን ህመም በሚከተሉት ወቅቶች ሊያጋጥመን  ይችላል

  • የወር አበባ ከማየታችን ከጥቂት ቀናት በፊት ወይም በወር አበባ ወቅት 
  • በወር አበባ ጊዜያት መካከል
  • በወሲብ ወቅት ወይም ከወሲብ በኋላ 
  • ሽንት ቤት በምንጠቀምበት ጊዜ በተለይም የወር አበባችን ላይ ሆነን ሽንት ቤት ስንጠቀም የማህፀን ህመም ሊያጋጥመን ይችላል።

 

    ለማርገዝ መቸገር 

  ኢንዶሜሪዮሲስ እርጉዝ መሆንን የበለጠ ከባድ ያደርግብናል።  ኢንዶሜትሪዮሲስ እንቁልጢ ወይም የማህፀን የሰውነት ህዋሳትን ሊጎዳ የሚችል ጠባሳ በመፍጠር ማርገዝን በጣም አዳጋች ሊያደርግብን ይችላል ። የኢንዶሜትሪዮሲስ ችግር ያለባቸው ሴቶች ጠባሳ ባይኖራቸውም ለማርገዝ ሊቸገሩ ይችላሉ። ኢንዶሜትሪዮሲስ  ያለባት ሴት ነፍሰጡር ብትሆን ግን እርግዝናውን አይጎዳውም። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ በእርግዝና ወቅት ከዚህ በፊት የነበሩባት የኢንዶሜትሪዮሲስ ምልክቶች ይቀንሳሉ።

 

    ኢንዶሜትሪዮማ ( ቸኮሌት እጢዎች) 

 

  ኢንዶሜትሪዮሲስ ባለባቸው ሴቶች እንቁልጢ ላይ ኢንዶሜትሪዮሲስን የያዙ እጢዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ይህንንም በሕክምናው አለም  ኢንዶሜትሪዮማ እንለዋለን። ብዙውን ጊዜ እነዚህ እጢዎች ቸኮሌት በሚመስል ደም ይሞላሉ ስለዚህም አንዳንድ ጊዜ በሕክምናው አለም የቸኮሌት እጢዎች ይባላሉ። እነዚህ እጢዎች አንዳንዴ የማህፀን(ፐልቪክ) አልትራሳውንድ በምናረግበት ወቅት ወይም በማህፀን ምርመራ ጊዜ ሊታዩ ይችላሉ ።

 

ለኢንዶሜትሪዮሲስ የምናደርጋቸው ምርመራዎች ምን ምን ናቸው?

  • ሙሉ አካላዊ ምርመራ 
  • የደም ምርመራ ፦ አጣዳፊ እና ዘላቂ ብግነት መኖሩን ለመለየት ይረዳናል
  • የሽንት ምርመራ ፦ ሌሎች የማህፀን ህመም የሚያመጡ ኢንፌክሽኖችን ለመለየት ይጠቅማል
  • ላፓሮስኮፒ (Laparoscopy) :- ኢንዶሜትሪዮሲስ መኖሩን በእርግጠኝነት ለማወቅ የሚያስችል አነስተኛ  የቀዶ ጥገና ስራ ሲሆን ሐኪማችን በቀጭን ካሜራ በመታገዝ  ማየትን እና ከተለመደው ውጪ የሰውነት ህዋስ ሲገኝ ደግሞ ናሙና( ባዮፕሲ) መውሰድን ያጠቃልላል።

 

የኢንዶሜትሪዮሲስ ሕክምና 

 

የኢንዶሜትሪዮሲስ ችግር ላለባቸው ሴቶች ብዙ የሕክምና አማራጮች አሉ። የሕክምና አማራጫችን የሚወሰነው በጣም በሚያስቸግረን የኢንዶሜትሪዮሲስ ምልክት አይነት እና ለወደ ፊት የማርገዝ እቅዳችን ላይ ነው።

 

ህክምናው የሚከተሉትን ሊያጠቃልል ይችላል ፡

 

  • (NSAIDs )ስቴሮይድ ያልሆኑ ፀረ ብግነት መድኃኒቶች ፦ በኢንዶሜትሪዮሲስ ምክንያት የሚከሰተውን ህመም ለማስታገስ የሚረዱ የህመም ማስታገሻ የመድሃኒት አይነቶች ናቸው። መድሃኒቱ በአጠቃላይ ለህመሙ መንስኤ የሆነውን ፕሮስታግላንዲን እንዳይመነጭ ያደርጋል። የወር አበባችን ከመጀመሩ ከአንድ እስከ ሁለት ቀናት በፊት እነዚህን መድሃኒቶች መጀመር የፕሮስታግላንዲን መመረትን ለመከላከል እና ህመምን ለመቀነስ ይረዳናል።
  • ሆርሞንያለው የወሊድ መቆጣጠሪያ ፦ሆርሞናል የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል፣ ፓች እና የሴት ብልት ቀለበቶች ከባድ የደም መፍሰስን በመቀነስ ህመምን ለማከም ይረዳሉ ። በመርፌ የሚወጉ እና እጅ ላይ የሚቀበሩ ሆርሞናል የወሊድ መቆጣጠሪያዎችም ህመምን በመቀነስ ውጤታማ ናቸው።  ይህ ሕክምና እርግዝና እንዳይፈጠር ስለሚከላከል ለማርገዝ ለሚሞክሩ ሴቶች ተገቢ አይደለም 
  • ጎናዶትሮፒን ሪሊዚንግ ሆርሞን አጎኒስት ፦ እነዚህ መድኃኒቶች ጊዜያዊ ማረጥን የሚያስከትሉ  ናቸው። ሕክምናው እንቁልጢ ኤስትሮጅን የሚባል ኬሚካል ማምረት እንዲያቆም በማድረግ የኢንዶሜትሪዮሲስ የሰውነት ህዋስ መጠን እንዲቀንስ ይረዳል። ይህ ህክምና ከ80 በመቶ በላይ በሚሆኑ ሴቶች ላይ በኢንዶሜትሪዮሲስ ምክንያት የሚመጣን ህመም ይቀንሳል ። ለማርገዝ እየሞከሩ ላሉ ሴቶች ግን ይህ ሕክምናም አይመከርም።
  • ቀዶ ጥገና ፦ የሚከተሉት ምልክቶች ካሉን የቀዶ ጥገና ሕክምና አማራጭ ሊሆንነን ይችላል 

     

                               - በኢንዶሜትሪዮሲስ ምክንያት የተከሰተብን የማህፀን ሕመም በጣም ከባድ ከሆነ

                               - ከላይ የተጠቀሱትን መድኃኒቶች ሞክረን ምንም አይነት ለውጥ ካላየንባቸው

                               - ማህፀን ውስጥ እጢ ካለ ቀዶ ጥገና የሕክምና አማራጫችን ሊሆን ይችላል። እጢውን ማስወገድ የሕመማችንን መንስኤ በትክክል ለመለየት ያግዘናል ምክንያቱም  ከኢንዶሜትሪዮሲስ ውጪ  የማህፀን ሕመምን የሚያመጡ ብዙ በሽታዎች ስላሉ እነሱን ለመለየት እና ለማከም ይረዳናል 

                               - ለማርገዝ ከተቸገርን እና የችግራችን መንስኤ ኢንዶሜትሪዮሲስ ሆኖ ከተገኘ ቀዶ ጥገና አማራጫችን ሊሆን ይችላል

 

በኢንዶሜትሪዮሲስ ምክንያት ለሚከስት የማርገዝ መቸገር ሕክምና አለው ?

 

በኢንዶሜትሪዮሲስ ምክንያት ለማርገዝ ብንቸገር ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚረዱ ብዙ የሕክምና አማራጮች አሉን። የሕክምና አማራጫችን እንደ ዕድሜያችን ፣ የሌሎች ተጓዳኝ የወሊድ ችግሮች መኖር እና በኢንዶሜትሪዮሲሱ ክብደት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። የሕክምና አማራጫችን የሚከተሉትን ያጠቃልላል ፦

  • የመካነንት መድሃኒቶች
  • የመካንነት  መድሃኒቶችን ከ ኢንትራዩትራይን ኢንስሚነሽን ጋር በአንድ ላይ በመጠቀም
  • ከላይ እንደጠቀስነው ኢንዶሜትሪዮሲስን በቀዶ ጥገና ማስወገድ እና
  • ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን (IVF) ናቸው።

Comments (0)