ከስነ ልቦና ጋር የተያያዙ የአመጋገብ ችግሮች (Eating disorders)
የሚመገቡትን ምግብ መመጠን ተቸግረው ወይም አብዛኛውን ጊዜ በትንሹ ለመመገብ ወስነው ከቁጥጥርዎ ውጪ ብዙ የመመገብ ልማድ አለዎት? ወይም
የተመገቡትን ለማቃጠል ከተገቢው በላይ ምግብ በመቀነስ፣ አውቆ በማስመለስ፣ በዳይት ወይም ስፖርት በመስራት ለማካካስ ሞክረው ያውቃሉ?
እንግዲያውስ ከስነ ልቦና ጋር የተያያዘ የአመጋገብ ችግር ሊኖርብዎት ይችላል።
ለመሆኑ ከስነ ልቦና ጋር የተያያዘ የአመጋገብ ችግር ምን ማለት ነው?
በስነ ልቦና ሳይንስ ውስጥ ይህ አይነቱ የበሽታ ምልክት የተለያዩ የስነልቦና ችግሮች ላይ ሊገለጥ የሚችል እና በውስጡ ብዙ አይነት የአመጋገብ ችግሮችን የያዘ ክፍል ነው። ከነዚህ የአመጋገብ ችግሮች (በሽታዎች) ውስጥ በስፋት የሚታወቁት ሶስቱ ናቸው። እነሱም
- አኖሬክዚያ ነርቮሳ (Anorexia nervosa)
- ቡሌሚያ ነርቮሳ (Bulimia nervosa)
- ቤንጅ ኢቲንግ ዲስኦርደር (Binge-eating disorder)
የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?
ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱም በሽታዎች የየራሳቸው ምልክቶች ቢኖራቸውም የሚያመሳስላቸውም ነገሮች አሉ።
በአኖሬክዚያ ነርቮሳ (Anorexia nervosa) የሚሰቃዩ ሰዎች ክብደታቸው ከተገቢው በታች ቢሆን እንኳን ይበልጥ ለመቀነስ ፍላጎት ስላላቸው ምግብ ከመመገብ ይቆጠባሉ። ራሳቸውን የሚያስቡት ወፍራም እንደሆኑ እና መቀነስ እንዳለባቸው ነው። መወፈርን ከመጠን በላይ ስለሚፈሩ ምግብ መመገብ ያቅታቸዋል። እነዚህ በሽተኞች ክብደታቸው ከመጠን በታች ነው።
በተጨማሪም በአኖሬክዚያ ነርቮሳ የተጠቁ ሰዎች ለተያዩ የጤና እክሎች ይጋለጣሉ። ለምሳሌ
- የተዛባ የወር አበባ (የወር አበባ ላይኖራቸው) ይችላል።
- ምክነት
- የልብ፣ የጉበት እና የኩላሊት ችግሮች
- የአጥንት እና የጡንቻ መድከም
- የፀጉር መሳሳት እና የጥፍር መሰባበር
- የቆየ ድካም
በቡሌሚያ ነርቮሳ (Bulimia nervosa) የሚሰቃዩ ሰዎች ደግሞ ውፍረትን ምንም ቢጠሉም አለመመገብ ግን አይችሉም። በተቃራኒው ራሳቸውን ለመቆጣጠር ስለሚቸገሩ የሚመገቡትን ምግብ መመጠን ይቸገራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከመደበኛ ሰው ከሚመገበው የምግብ መጠን የበዛ ምግብ ስለሚመገቡ የሃፍረት እና የፀፀት ስሜት ይሰማቸዋል። በዚህ ምክንያት በብዛት ቶሎ ቶሎ ይመገቡና የተመገቡትን ለማቃጠል ራሳቸውን ያስርባሉ፤ አውቀው ያስመልሳሉ፣ በዳይት ወይም ስፖርት በመስራት ለማካካስ ይሞክራሉ። ይህ ሁኔታ በትንሹ በሳምንት ሁለቴ ለ ሶስት ሳምንታት ከቀጠለ ቡሌሚያ ነርቮሳ እንለዋለን። እነዚህ በሽተኞች መጠነኛ የሆነ የሰውነት ክብደት ቢኖራቸውም ጤነኛ የአመጋገብ ስርዐት ስለሌላቸው እንደ በሽታ ይቆጠራል።
ቢሌሚያ ነርቮሳ ከሌሎች የስነልቦና በሽታዎች ጋር ተያያዥነት ያለው በሽታ ነው። ለምሳኤ የቦርደር ላይን የስብዕና ችግር ከአለባቸው በሽተኞች ውስጥ 21 በመቶው ይህ ችግር አለበት። በተመሳሳይ የድባቴ በሽተኞች በዚህ ህመም ሊሰቃዩ ይችላሉ። ስለዚህም በቡሌሚያ ነርቮሳ የተጠቁ ሰዎች ከአንድ በላይ የስነልቦና ችግሮች የመሰቃየት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ቤንጅ ኢቲንግ ዲስኦርደር (Binge-eating disorder) የሚባለው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ (ቶሎ ቶሎ እና ብዙ) አመጋገብ ሲሆን ልክ እንደ ቡሌሚያ ነርቮሳ ህመምተኞች ሁሉ እነዚህም በሽተኞች የሚመገቡትን ምግብ መጠን መወሰን ይቸገራሉ።
ቤንጅ ኢቲንግ ዲስኦርደር ከ ቡሌሚያ ነርቮሳ የሚለየው ቤንጅ ኢቲንግ ዲስኦርደር በሽተኞች የሚበሉትን ለማቃጠል ለማስመለስ፣ ምግብ ለማቋረጥ ወይም በስፖርት ለመቀነስ ሙከራ አያረጉም። ስለዚህም እነዚህ በሽተኞች በብዛት ከመጠን ያለፍ ክብደት ይኖራቸዋል።
ከስነ ልቦና ጋር የተያያዙ የአመጋገብ ችግሮች የሚያጋልጡ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?
እስካሁን በተደረገው ጥናት መሰረት እነዚህ የአመጋገብ ችግሮችን የሚፈጠሩበት ምክንያት በእርግጠኝነት አይታወቅም። ነገር ግን ለዚህ በሽታ የሚያጋልጡ የተወሰኑ ነጥቦች ተለይተው ተቀምጠዋል።
እንደ አጠቃላይ ስናየው
- የዘረ መል ተጋላጭነት፣
- የስነልቦና ችግሮች፣
- የቤተሰብ ሁኔታ እንዲሁም
- የአካባቢያዊ እና ማህበረሰባዊ ተፅእኖዎች ለዚህ በሽታ ሊያጋልጡ ይችላሉ።
ለምሳሌ በተለያዩ ምክንያቶች በራስ መተማመኑ ዝቅተኛ የሆነ ሰው የተስተካከለ አቋም በመያዝ የጎደለውን በራስ መተማመን ማምጣት እንዳለበት ሊሰማው ይችላል።
በተያያዘ መልኩ በህፃንነታቸው የጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ሲያድጉ በቡሌሚያ ነርቮሳ የመጠቃት እድላቸው ከፍ ያለ ሆኖ ታይቷል።
በተጨማሪም የአመጋገብ በሽታ ያለበት የቤተሰብ አባል ካለ በበሽታው የመጠቃት እድልዎ ከ 6 እስከ 10 እጥፍ እንደሚጨምር ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በሽታው እንዳለብኝ እንዴት ማወቅ ይችላል?
በሽታው እንዳለ እና እንደሌለ የሚታወቀው ከስነልቦና ሐኪምዎ ጋር በመነጋገር ሲሆን ሐኪምዎ ዲሴኤም (DSM) የሚባል መስፈርት በመጠቀም በሽታው እንዳለ እና እንደሌለ ይመረምረዎታል። ስለዚህም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ካለዎት ከሐኪምዎ ጋር መነጋገር ይኖርብዎታል።
እንደአጠቃላይ ግን የሚከተሉትን 5 ጥያቄዎች በመጠየቅ ችግር እንዳለ መገመት ይችላሉ።
- ከመጠን በላይ በመጥገብዎ ምክንያት አለመመቸት (ቁንጣን) ኖሮዎት ያውቃል?
- የሚመገቡትን የምግብ መጠን መቆጣጠር ተቸግረው ያውቃሉ?
- በቅርቡ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ 6.35 ኪሎ በላይ ቀንሰዋል?
- ሌሎች ሰዎች ቀጭን እንደሆኑ ቢነግርዎትም ወፍራም እንደሆኑ ይሰማዎታል?
- ምግብ ተቆጣጥሮኛል ብለው ያስባሉ?
ከነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ቢያንስ ለሁለቱ አዎ የሚል መልስ ከሰጡ በበሽታው እየተሰቃዩ እንዳሉ ስለሚገልፅ ለማረጋገጥ እና ህክምና ለማግኘት ወደ ስነልቦና ሐኪምዎ መሄድ ይኖርብዎታል።
ከስነ ልቦና ጋር የተያያዙ የአመጋገብ ችግሮች እንዴት ይታከማሉ?
የበሽታው ክብደት እና አይነት ላይ በመወሰን የተለያዩ አይነት የሕክምና አማራጮች አሉ። ለምሳሌ ተጨማሪ የጤና እክሎች ካሉ እንዲሁም በሽተኛው ራሱን የማጥፋት ሀሳቦች ካሉት ሆስፒታል ተኝቶ መታከም ሊያስፈልገው ይችላል።
በአኖሬክዚያ ነርቮሳ የተጠቃ ሰው ከ ሳይኮቴራፒ ህክምና በተጨማሪ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ መደረግ አለበት። ምክንያቱም አብዛኞቹ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ራሳቸውን ስለሚያስርቡ ክብደታቸው ከመጠን በታች ነው።
እንደአጠቃላይ የአመጋገብ ችግር ላለባቸው ሰዎች የተለያየ የሳይኮቴራፒ አይነት ሊሰጣቸው ይችላል። ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ
- ኮግኒቲቭ ብሄቭየራል ቴራፒ (Cognitive-behavioral therapy) እና
- የቤተሰም ምክር አገልግሎት ናቸው።
በተጨማሪም እንደሚያሳዩት ምልክቶች የተለያዩ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።


