በጨቅላ ህፃናት ላይ የሚከሰት የዐይን በሽታ  (Ophthalmia neonatorum)

Melat Geatchew
Feb 9, 2026
undefined

በጨቅላ ህፃናት ላይ የሚከሰት የዐይን በሽታ  (Ophthalmia neonatorum)

ኦፍታልሚያ ኒዮናቶረም (Ophthalmia Neonatorum) ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 28 ቀናት ውስጥ የሚከሰት ከባድ የአይን ኢንፌክሽን ነው። አብዛኞቹ በጤና ተቋማት ውስጥ የሚወለዱ ህፃናት ይህ የዓይን በሽታ እንዳያጋጥማቸው ሲባል በተወለዱ በሰዓታት ውስጥ የዓይን ጠብታ ይደረግላቸዋል።ይህ በሽታ በስርአት ካልታከመ የአይን ብርሃን እስከማጥፋት ይደርሳል። 

 

 የጨቅላ ህፃናት የዓይን በሽታ መንስዔዎች 

  • ባክቴሪያዎች  በአብዛኛው ጊዜ የጨቅላ ህጻናት ዓይን በሽታ ያስከትላሉ   
  •  ቫይረስ 
  •  ኬሚካሎችም መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ። 

    ባክቴሪያዎች

  • ክላሚዲያ ትራኮማቲስ (Chlamydia trachomatis) ይህ  ባክቴሪያ  የጨቅላ ህፃናት የዓይን በሽታ በማስከተል ቀዳሚ ሲሆን በዚህ ባክቴሪያ ከተያዘች እናት የተወለዱ ህጻናት ከ 25 እስከ 50% የጨቅላ ህፃናት የዓይን በሽታ የመያዝ እድላቸው ይጨምራል።በዚህ ባክቴሪያ የሚመጣው በሽታ ልጁ ከተወለደ ከ5 ቀን እስከ 12 ቀናት ውስጥ ሊጀመር ይችላል። 
  •  ኒዜሪያ ጎኖሪያ ( Neisseria gonorrhoeae) ይህ ባክቴሪያ በጣም አደገኛ እና ከባድ የሆነ የጨቅላ ህጻናት የአይን በሽታ አምጭ ባክቴሪያ  ሲሆን በፍጥነት ካልታከመ እይታን እስከማሳጣት ሊደርስ ይችላል። በዚህ ባክቴሪያ የሚመጣው በሽታ ልጁ ከተወለደ በ 24 እስከ 48 ሰአታት ውስጥ ሊጀምር ይችላል። 
  •  ሌሎች ግራም ፖዘቲቭ( gram-positive organism) እና ኔጌቲቭ ባቴሪያዎች ( gram-negative organisms)

            ቫይረስ 

  •   ኤች ኤስ ቪ (Herpes simplex virus HSV)  ብዙ ጊዜ የጨቅላ ህጻናት የአይን በሽታ አያስከትልም (<1%) ብዙ ጊዜ ይህ ቫይረስ የህን በሽታ ሲያስከትል የጠቅላላ የሰውነት የቫይረስ ኢንፌክሽን ያስከተላል ።   በሱ ምክኒያት የሚመጣው በሽታ ልጁ ከተወለደ በ 2 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊከሰት ይችላል። 

በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ የሚመጣው የዓይን በሽታ፣ ህፃናቱ ሲወለዱ በእናታቸው ብልት በኩል በሚወጡበት ጊዜ (በወሊድ ጊዜ) ተዋህሲያኑ (ባክቴሪያና ቫይረስ) ከእናታቸው ብልት አካባቢ ወደ ህፃናቱ ፊት (አይን) ይሸጋገራሉ።

 ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

  • እናትዮዋ ከርግዝና በፊት ወይም በእርግዝና ጊዜ ተገቢ ህክምና ያልተደረገለት የአባለዘር በሽታ ያለባት ከሆነ። 
  • ምጥ ከመጀመሩ በፊት የሽርት ውሃ መፍሰስ
  • ያለ ጊዜ የተወለዱ ህጻናት
  • ከ ኤች አይ ቪ ቫይረስ (HIV) ጋር የሚኖሩ እናቶች
  • ልጆች ከተወለዱ በኋላ ቅድመ ህመም መከላከያ መድሃኒቶችን በአግባቡ አለመስጠት
  • በወሊድ ወቅት የጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰት የአይን ጉዳት
  • ጥንቃቄ የጎደለው የጨቅላ ህጻናት እንክብካቤ

በባክቴሪያና በቫይረስ የሚመጣው የዓይን በሽታ ህፃኑ በተወለደ በ 5 ቀናት ውስጥ ምልክት የሚያሳይ ሲሆን፣ በኬሚካል (በአንዳንድ መዲሃኒቶች) ምክንያት ከሆነ ደግሞ በሰዓታት ውስጥ ምልክት ሊያሳይ ይችላል።

 

የበሽታው ምልክቶች

  • መነጫነጭ
  • የአይን መቅላት 
  • የዐይን ፈሳሽ፣
  • የህፃኑ የዓይን ቆብ በ ዓይናር (የዓይን ፈሳሽ) መያያዝና ህፃኑ አይኑን ለመግለጥ መቸገር
  • የዓይን ቆብ እና የዐይን ሽፋሽፍቶች  ማበጥ
  • እንደ መግል ያለ ፈሳሽ መፍሰስ 
  • አይንን ለመግለጥ መቸገር
  •  የዓይን ቆብ መቅላትና የመሳሰሉትን ሊያሳይ ይችላል። 

     

    ህክምናውና መከላከያ መንገዶቹ

  • በእርግዝና ጊዜ ወይም ከዛ በፊት እናቲቱ ላይ የአባለዘር በሽታ ካለ ተገቢ የሆነ ህክምና ማድረግ አለባት።
  • ማንኛውም ህፃን ወዲያው እንደተወለደ በጤና ባለሙያ አማካኝነት የዓይን ጠብታ መቀባት ይኖርበታል። ይህም ከላይ የተገለፀው የዓይን በሽታ በህፃኑ ላይ እንዳይከሰት የሚከላከል ሲሆን፣ ይህን ለማግኘት ሁሉም እናቶች ሲወልዱ ወደ ጤና ተቋም ሄደው መውለድ አለባቸው።
  • በሽታው በህፃኑ/ኗ ላይ ከተከሰተ ህፃኑ ወደ ጤና ተቋም ተወስዶ በጤና ባለሙያ በሚታዘዝ መድሃኒት ህክምና እንድያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል።
  •  በኬሚካል (አለርጅክ) ምክንያት የሚከሰተው የዓይን ህመም አብዛኛውን ጊዜ በራሱ ሊድን የሚችል ቢሆንም፣ ባለሙያ ማማከር ግን አስፈላጊ ነው።

     

    ህክምና 

    በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰት የአይን ህመም ሲከሰት የአይን ጠብታ መድሐኒቶችን መጠቀም እንዲሁም የአይን እና የመጠቀሚያ እቃዎችን እንደ ንጽህናቸዉን በአግባቡ መጠበቅ ተገቢ ነዉ፡፡  ህክምናውም በጠብታ መልክ ከሚሰጠው መድኃኒት በተጨማሪ በመርፌ መልክ የሚሰጥ ሲሆን ለተወሰኑ ቀናት ወይ ሳምንታት  መድኃኒቱን ወስዶ መጨረስ ይኖርበታል። 

በሽታው ካልታከመ ሊከሰቱ የሚችሉ ውስብስብ ችግሮች 

  • የኮርኒያ መቁሰል (Corneal ulceration)
  • የኮርኒያ መቦርቦር (Perforation)
  • ዘላቂ የአይን ብርሃንን ማጣት 
  • ኢንፌክሽኑ ወደ ደም መሰራጨት (gonococcal sepsis)

ለጨቅላ ሕፃናት በብዛት የታዘዙ አንቲባዮቲክ የዓይን ጠብታዎች

  • Erythromycin Ophthalmic Ointment
  • Ciprofloxacin
  • Ofloxacin

በጨቅላ ህጻናት ላይ ለሚከሰት የዓይን ሕመም (Conjunctivitis) አማራጭ በቤት ውስጥ የሚደረጉ እና ተፈጥሯዊ መፍትሄዎች

የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች በሽታውን ለማከም ውጤታማ ቢሆኑም አንዳንድ ወላጆች ከዘመናዊ ሕክምናዎች ጎን ለጎን የተፈጥሮ እና በቤት ውስጥ የሚደረጉ ማስታገሻኦችን እንዲያደርጉ ይመከራሉ ። ነገር ግን ማንኛውንም አማራጭ ሕክምና ከመሞከር በፊት ሁልጊዜ የህጻናት ስፔሻሊስት ወይንም የጤና ባለሙያ ያማክሩ ።

  • ሞቅ ያለ ፎጣ፡- ሞቅ ያለ ፎጣ ወይንም  ጨርቅ በቀስታ እብጠት ያለበት ዓይን ላይ ማድረግ የእብጠት መጠኑን እና በህመምን  ይቀንሳል።
  • የጡት ወተት ማፍሰስ ፡- የጡት ወተት የታመመው አይን ላይ ማፍሰስ ፣ የጡት ወተት በውስጡ ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪያት እንዳለው ይታመናል፣ ይህም በባክቴሪያ ምክኛት የተከሰተን እንፌክሽን ለማከም ያግዛል፣ ነገር ግን ይህንን ከማድረግ በፊት የህክምና ምክር መጠየቅ አለበት።
  • ሳላይን ሶሉሽን፡- ዓይንን በንጽሁ ውሃ ወይንም ሳላኡን ሶሉቲሽን ማጠብ  የአይኑን ንጽህናነ እና ያለውን ህመም ለማስታገስ ይረዳል።

የሕፃን የዓይን ኢንፌክሽኖችን እንዴት እንከላከል

አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰት የአይን ኢንፌክሽኖችን እንዳይፈጠሩ እና ለማስወገድ መከላከል ላይ መስራት ቁልፍ መፍትሄ ነው፡-

  • እጅን አዘውትረው ይታጠቡ፡ የልጅዎን ፊት ወይም አይን ከመንካትዎ በፊት ሁል ጊዜ እጅዎን በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ።
  • ንፁህ አካባቢን ይጠብቁ፡ የልጅዎ የመኖሪያ ቦታ ንጹህ እና ከበሽታ አምጪ ተህዋስያን  የፀዳ መሆኑን ያረጋግጡ።
  • በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነትን ያስወግዱ፡ ጨቅላ ልጅዎን ኮንኒንቲቫቲስ ወይም ሌሎች ኢንፌክሽኖች ካለባቸው ግለሰቦች ያርቁ።

 

Comments (0)