እርግዝና እና ኤች አይ ቪ (MTCT & PMTCT)

Melat Geatchew
Feb 10, 2026
undefined

እርግዝና እና ኤች አይ ቪ (MTCT & PMTCT)

ለሕፃናት በኤች.አይ.ቪ. ኢንፌክሽን መያዝ ዋነኛ መንሥኤ ከእናት ወደ ልጅ የቫይረሱ መተላለፍ ሲሆን ይህም ከሚከተሉት በአንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል። 

በቅድመ ወሊድ፣ በምጥ እና በወሊድ ጊዜ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ በጡት ማጥባት ወቅት ሊሆን ይችላል። ያለ ምንም ሕክምና እርዳታ የመተላለፍ ዕድሉ ከ 15 - 45% ሲሆን ተገቢውን የሕክምና እርዳታ ከተደረገ ግን የመተላለፍ ዕድሉ ከ 5% በታች ሊቀንስ ይችላል፡፡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ እርግዝና  የኤች.አይ.ቪን ሕመም አያባብስም፤ ወይም በኤች አይ ቪ የመሞትን አደጋን አይጨምርም። እንዲሁም አብዛኞቹ የኤች. አይ. ቪ ሕክምናዎች በሚወለደው ሕፃን ላይ የሚያመጡት የጤና እክል አይኖርም። 

 

ቫይረሱ  ከእናት  ወደ  ልጅ  እንዲተላለፍ  የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  • የእናትየው ሁኔታ
  • በእናት ደም ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን ከፍተኛ መሆን (High viral load)
  • እናትየው በቫይረሱ የተያዘችው ወይም እንዳለባት ያወቀችው በቅርብ ከሆነ 
  • የእናት ዝቅተኛ የሲዲ 4 መጠን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት
  • የጡት ጫፎች፣ መቁሰል፣ መሰንጠቅ ወይም ኢንፌክሽን መኖር
  • የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒትን በአግባቡ አለመውሰድ
  • የሕፃኑ ሁኔታ 
  •  የክብደት መጠን ትንሽ መሆን
  • ጡት ረዘም ላለ ጊዜ መጥባት
  •  በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጡት እና ሌላ ምግብን አደባልቆ መስጠት
  •  የሕፃኑ አፍ አካባቢ ቁስል መኖር
  • በምጥ እና በወሊድ ጊዜ የሚፈጠሩ ሁኔታዎች
  • የሽንት ዉሃ ከአራት ሰዓታት በላይ መፍሰስ
  • እናትየው ብልት እና ማሕፀን አካባቢ ጉዳት ደርሶ ከነበረ
  • ወሊዱን ለማቅለል የሚደረጉ ነገሮች (Episiotomy, Assisted vaginal delivery)
  • ሕፃኑ ለእናትየው የማሕፀን ፈሳሽ መጋለጥ ናቸው።

ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ ምን መደረግ አለበት?

የጤና ባለሙያዎች በአጠቃላይ አራት መከላከያ መንገዶችን ይጠቀማሉ።

1. አስቀድሞ በመራቢያ ዕድሜያቸው ላይ ያሉትን ሴቶች በቫይረሱ እንዳይያዙ መከላከል፡፡

  • ይህም በሁለቱም ፆታዎች  ላይ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያግዙ የጠባይ ለውጦችን ማምጣት ያጠቃልላል።

2. ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ  በሆኑ ሴቶች ላይ ያልታቀደ እርግዝናን መከላከል፡፡

  • ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ለሆኑ ሴቶች ተገቢ የሆነ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን መስጠት 

3. ከእናት ወደ ልጅ ኤች አይ ቪ  እንዳይተላለፍ መከላከል እና

  • ይህም ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ  የሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች በቅድመ ወሊድ፣ በምጥ እና በወሊድ ጊዜ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ በጤና ተቋም ውስጥ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ስርጭቱን መከላከል ነው።

4. በኤች አይ ቪ ለተያዙ ሴቶች፣ ለጨቅላዎቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው አያያዝ እንክብካቤ እና ድጋፍ ማድረግ ናቸው።

 

ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ  ለሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች መደረግ ያለባቸው የጤና እንክብካቤዎች ምንድናቸው?

  • ከእርግዝና በፊት 
  •  ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ የሆኑ እናቶች ለማርገዝ ከመሞከራቸው በፊት በደማቸው ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን መታወቅ  ስለአለበት የጤና ባለሙያ ቢያነጋግሩ መልካም ይሆናል። በተጨማሪም ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ የሆነች ሴት ረዘም ላለ ጊዜ በኢንፌክሽን ሕመም ታማ ከነበረ ቢያንስ ለ 6 ወራት ያህል ባታረግዝ ይመከራል።
  •  አብዛኛዎቹ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቶች በእርግዝና ወቅት ደኅንነታቸው የተጠበቀ ስለሆኑ መድኃኒቶች መቀየር አያስፈልጋቸውም።
  • እንዲሁም የኤች አይ ቪ መድኃኒቶችዎን በመደበኛነት መውሰድ አስፈላጊ ነው።

- በደማቸው ውስጥ ዝቅተኛ የቫይረስ መጠን የአለባቸው ሴቶች  ኤች አይ ቪን ወደ ልጅ የማስተላለፍ ዕድላቸው አነስተኛ ነው።

  • በእርግዝና ወቅት
  •  በቅድመ ወሊድ ክትትል ጊዜ ለእናቶች የሚከተሉት የጤና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። 
  •  የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቶች  ቀድሞውኑ ከአልተጀመሩ እንዲጀመሩ ማድረግ። 
  • የደም ምርመራ (የሲዲ 4 ቆጠራ እና በደም ውስጥ ያለውን የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን ማወቅ) 
  • እንደ የሲዲ 4 መጠን ሌሎች መከላከያ መድኃኒቶች (Prophylaxis) ሊታዘዙ ይችላሉ።
  •  የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል ለእናትዬዋ የሥነ አመጋገብ ምክር ይሰጣታል፡፡
  • ስለ አባላዘር በሽታ ግንዛቤ እና መከላከያ መንገዶች ለእናትዬዋ ገለፃ ይደረግላታል፡፡ በተጨማሪም በሽታው ከአለ እንድትታከም ይደረጋል።
  • የወባ በሽታ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የወባ በሽታ መከላከያ መድኃኒት ሊሰጥ ይችላል።

በአጠቃላይ የጤና ባለሙያዎች ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚያስፈልገውን የጤና እንክብካቤ ያደርጋሉ።

 

የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቶች በእርግዝና ወቅት

  • በእርግዝና ወቅት መድኃኒቶቹ ከአልተጀመሩ እንዲጀመሩ ይደረጋል። ከተጀመሩ ግን  በእርግዝና እና ከወሊድ በኋላ እንዲቀጥሉ ይደረጋል።  መድኃኒቶችን እንደታዘዙት መጠንና ጊዜ በትክክል መውሰድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ 
  • ይህም ኤች አይ ቪን ወደ ሕፃኑ የማስተላለፍ አደጋን በእጅጉ ሊቀንሰው ይችላል፡፡
  • በወሊድ ጊዜ
  • የምጥ እና የወሊድ ጊዜ  በጣም ወሳኝ ወቅት ሲሆን 1/3ኛ የሚሆኑት ኢንፌክሽኖች የሚከሠቱት በዚህ ወቅት ነው።

 መውለድ ያለባት በምጥ ወይስ በኦፕሬሽን? (Vaginal delivery vs CS)

  • ይህ የሚወሰነው በእናትዬዋ ደም ውስጥ ባለው የቫይረስ መጠን ነው። 

- የቫይረሱ መጠን ከ1000/ሚሊ በታች ከሆነ እና መድኃኒቷን በአግባቡ የምትወስድ ከሆነ በምጥ መውለድ ትችላለች። 

- የቫይረሱ መጠን ከ1000/ሚሊ  በላይ ከሆነ በተለይም ከ 34-36 ሳምንቷ ላይ ከሆነ የተሠራው በ ኦፕሬሽን ብትወልድ ይመረጣል። 

  • ኦፕሬሽን አብዛኛውን ጊዜ በ38ኛው ሳምንት ላይ ይደረጋል።
  • ስለዚህም የጤና ባለሙያዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ የወሊድ አሠራሮችን ይተገብራሉ።                 
  •  በተጨማሪም በተቻለ መጠን ልጁ ለእናቲቱ ደም እና የማሕፀን ፈሳሽ እንዳይጋለጥ ይከላከላሉ፡፡
  • ከወሊድ በኋላ 
  • እናትዬዋ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቱን እንድትቀጥል ይደረጋል።
  • ስለሕፃኑ እና እናትዬዋ አመጋገብ እና ጤና አጠባበቅ ምክር ይሰጣታል። 
  • ኢንፌክሽኖች ካሉ ሕክምና ይደረጋል፡፡
  • ስለ ቤተሰብ ምጣኔ የምክር አገልግሎት ይሰጣታል። 

ኤች አይ ቪ እና ጡት ማጥባት

ጡት ማጥባት ኤች አይ ቪን ማስተላለፍ ይችላል። ነገር ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ይወሰናል፡፡

  • የጠባበት ቆይታ
  • የእናትየው የፀረ ኤች አይ ቪ  መድኃኒት አወሳሰድ
  • ከእናት ጡት ውጪ ሌላ ምግብ የሚወስድ ከሆነ እና
  • በአጠቃላይ በሕፃኑ ጤንነት ላይ ይወሰናል።

የአደጉት አገራት ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ የሆነች እናት ጡት ባታጠባ  ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን እንደኛ በማደግ ላይ ለአሉ አገሮች ንጹሕ ውሃ እና የእናት ጡት ወተትን የሚተካ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ እናቶች ከጥንቃቄ ጋር ጡት ማጥባታቸውን ቢቀጥሉ ይመከራል።

Comments (0)